ሉቃስ 7:18-35
ሉቃስ 7:18-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህንም ሁሉ ደቀ መዝሙርቱ ለዮሐንስ ነገሩት። ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ፥ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ?” ብሎ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ላካቸው። መልእክተኞችም ወደ እርሱ ደርሰው፥ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ? ብሎ መጥምቁ ዮሐንስ ወደ አንተ ልኮናል” አሉት። ያንጊዜም ብዙዎችን ከደዌአቸውና ከሕመማቸው ከክፉዎች አጋንንትም ፈወሳቸው፤ ለብዙዎች ዕውራንም እንዲያዩ ብርሃንን ሰጣቸው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶችም ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል። በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው።” የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ከሄዱ በኋላ ለሕዝቡ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንዲህ ይላቸው ጀመር፥ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ከነፋስ የተነሣ የሚወዛወዝ ሸንበቆን ነውን? ወይስ ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ቀጭን ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? እነሆ፥ በክብር ልብስ ያጌጡስ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ነቢይን ነውን? አዎን፥ እላችኋለሁ፤ ከነቢይም ይበልጣል። እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፥ ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈለት ይህ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም አልተነሣም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን የሚያንሰው ይበልጠዋል።” ሕዝቡም ሁሉ ቀራጮችም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን ጻድቅ ነው አሉት፤ የዮሐንስን ጥምቀት ተጠምቀው ነበርና። ፈሪሳውያንና የሕግ ጻፎች ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቃወሙ፤ በእርሱ አልተጠመቁምና። “እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን እመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? በገበያ ተቀምጠው ባልንጀሮቻቸውን ጠርተው፥ “አቀነቀንላችሁ፥ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾም አወጣንላችሁ፥ አላለቀሳችሁምም የሚሉአቸው ልጆችን ይመስላሉ። መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላ ወይንም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና ጋኔን አለበት አላችሁት። የሰው ልጅም እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እናንተ ግን እነሆ፥ በላተኛና ወይን ጠጪ ሰው፥ የኃጥኣንና የቀራጮች ወዳጅ አላችሁት። ጥበብም ከልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች።”
ሉቃስ 7:18-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሁሉ ለዮሐንስ ነገሩት። እርሱም ከመካከላቸው ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ “ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ? በሉት” ብሎ ወደ ጌታ ላካቸው። ሰዎቹም ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ “መጥምቁ ዮሐንስ፣ ‘ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ብሎ ወደ አንተ ልኮናል” አሉት። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን ከበሽታ፣ ከደዌና ከርኩሳን መናፍስት ፈወሳቸው፤ የብዙ ዐይነ ስውራንንም ዐይን አበራ። ከዮሐንስ ተልከው የመጡትንም እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቈሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔ የማይሰናከል ሁሉ ብፁዕ ነው።” የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፤ “ወደ በረሓ የወጣችሁት ምን ልታዩ ነው? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸንበቆ? እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? ባማረ ልብስ የሚሽሞነሞኑና በድሎት የሚኖሩ በቤተ መንግሥት አሉላችሁ። ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ልታዩ? አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ከነቢይም የሚበልጠውን ነው። እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ “ ‘መንገድህን በፊትህ የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ።’ እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ይህን የሰሙ ሁሉ፣ የዮሐንስን ጥምቀት በመጠመቅ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር ሰጡ፤ ፈሪሳውያንና ሕግ ዐዋቂዎች ግን በዮሐንስ እጅ ባለመጠመቃቸው፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዐላማ አቃለሉ። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን ልመስላቸው? ምንስ ይመስላሉ? በገበያ ቦታ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ እንዲህ የሚባባሉ ልጆችን ይመስላሉ፤ “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም።’ ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ጋኔን አለበት አላችሁት፤ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፣ ‘በልቶ የማይጠገብና ጠጪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አላችሁት። ጥበብ ግን ትክክለኛ መሆኗ በልጆቿ ሁሉ ዘንድ ተረጋገጠ።”
ሉቃስ 7:18-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደቀ መዛሙርቱም ለዮሐንስ እነዚህን ሁሉ አወሩ። ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ወደ እርሱ ጠርቶ፦ የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ ኢየሱስ ላከ። ሰዎቹም ወደ እርሱ መጥተው፦ መጥምቁ ዮሐንስ፦ የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ አንተ ላከን አሉት። በዚያች ሰዓት ከደዌና ከሥቃይ ከክፉዎች መናፍስትም ብዙዎችን ፈወሰ፥ ለብዙ ዕውሮችም ማየትን ሰጠ። ኢየሱስም መልሶ፦ ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አወሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ፥ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ፥ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ፥ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው አላቸው። የዮሐንስ መልክተኞችም ከሄዱ በኋላ፥ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር እንዲህም አለ፦ ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰውን ሰውን? እነሆ፥ ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱና በቅምጥልነት የሚኖሩ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው። እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። የሰሙትም ሕዝብ ሁሉ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ በዮሐንስ ጥምቀት ተጠምቀው እግዚአብሔርን አጸደቁ፤ ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ስለ አልተጠመቁ የእግዚአብሔርን ምክር ከራሳቸው ጣሉ። እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን አስመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ፦ እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም ይላል። መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና፦ ጋኔን አለበት አላችሁት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቶአልና፦ እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት። ጥበብም ለልጆዋ ሁሉ ጸደቀች።
ሉቃስ 7:18-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ እነዚህ ነገሮች ይህን ሁሉ ለእርሱ አወሩለት፤ እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ፥ “ያ ይመጣል የተባለው መሲሕ አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ? ብላችሁ ጠይቁት፤” ሲል ወደ ጌታ ኢየሱስ ላካቸው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ ሄደው “ ‘ያ ይመጣል የተባለው መሲሕ አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ብላችሁ ጠይቁት ሲል መጥምቁ ዮሐንስ ወደ አንተ ልኮናል፥” አሉት። ኢየሱስ በዚያኑ ሰዓት ሰዎችን ከልዩ ልዩ በሽታና ደዌ ፈወሰ፤ ርኩሳን መናፍስትንም አስወጣ፤ የብዙ ዕውሮችን ዐይን አበራ። ኢየሱስ መልእክተኞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ተመልሳችሁ ሂዱና ለዮሐንስ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ንገሩት፤ እነሆ፥ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ቀጥ ብለው ይሄዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል። በእኔ የማይሰናከል የተባረከ ነው።” የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ለሕዝቡ እንዲህ እያለ ይናገር ጀመር፦ “ምን ልታዩ ወደ በረሓ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸንበቆ ለማየት ነውን? ደግሞስ ምን ለማየት ወጣችሁ? የተዋበ ልብስ የለበሰውን ሰው ለማየት ነውን? የተዋበ ልብስ የሚለብሱና በድሎት የሚኖሩማ በነገሥታት ቤት ይገኛሉ፤ ታዲያስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይ ለማየት ነውን? አዎ፥ እላችኋለሁ፤ እንዲያውም ከነቢይ የሚበልጠውን ለማየት ነው። እርሱ ‘እነሆ! እፊት እፊትህ እየሄደ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥’ ተብሎ የተጻፈለት ነው። ሴቶች ከወለዱአቸው ሰዎች መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” ይህን በሰሙ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቀራጮችም እንኳ ሳይቀሩ በዮሐንስ እጅ ተጠምቀው ስለ ነበር የእግዚአብሔር ሥራ ትክክል መሆኑን ተገነዘቡ። ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ግን በዮሐንስ እጅ አንጠመቅም በማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ተቃውመው ነበር። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? ምንስ ይመስላል? በአደባባይ ተቀምጠው የሚጫወቱ ልጆችን ይመስላል፤ እነርሱም እርስ በእርሳቸው እየተጠራሩ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ እናንተ ግን አላለቀሳችሁም፥’ የሚሉ ናቸው። እንዲሁም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላና የወይን ጠጅም ሳይጠጣ ቢመጣ ‘ጋኔን አለበት፤’ አላችሁት። የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፥ ‘እነሆ፥ ይህ መብልና መጠጥ የሚወድ ነው፤ የቀራጮችና የኃጢአተኞችም ወዳጅ ነው፥’ አላችሁት። የጥበብ ትክክለኛነት በልጆችዋ ይረጋገጣል።”
ሉቃስ 7:18-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር ሁሉ አወሩለት። ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ “የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ወደ ጌታ ላካቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉ፦ “መጥምቁ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ወደ አንተ ላከን፦ ‘የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ” በዚያች ሰዓት ኢየሱስ ከደዌና ከሚያሠቃይ በሽታ፥ ከክፉዎች መናፍስትም ብዙዎችን ፈወሰ፤ ለብዙ ዐይነ ስውሮችም የማየትን ጸጋ ሰጠ። እርሱም መልሶ ለተላኩት እንዲህ አላቸው፦ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውሮች ያያሉ፤ የሚያነክሱ ይራመዳሉ፤ በለምጽ የተጠቁ ይነጻሉ፤ መስማት የተሳናቸውም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው።” የዮሐንስ መልክተኞችም ከሄዱ በኋላ፥ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰውን? እነሆ፥ ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱና በቅምጥልነት የሚኖሩ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፤ ከነቢይም የሚበልጠውን። “እነሆ፥ መንገድህን አስቀድሞ የሚያዘጋጅ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ” ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው። ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። የሰማውም ሕዝብ ሁሉ፥ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ፥ በዮሐንስ ጥምቀት በመጠመቃቸው የእግዚአብሔርን ጻዲቅነት ተቀበሉ፤ ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ባለመጠመቃቸው ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ዕቅድ አልተቀበሉም። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን እመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፤ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ እንዲህ የሚሉትን እንቢልታ ነፋንላችሁ፤ አላሸበሸባችሁምም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁምም። መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበር፥ እናንተም “ጋኔን አለበት፤” አላችሁ። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እናንተም “እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፤ የቀራጮችና የኀጢአተኞች ወዳጅ ነው፤” አላችሁ። ነገር ግን የጥበብ መጽደቅ በልጆችዋ ሁሉ ተረጋገጠ።