ሉቃስ 7:18-35

ሉቃስ 7:18-35 NASV

የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሁሉ ለዮሐንስ ነገሩት። እርሱም ከመካከላቸው ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ “ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ? በሉት” ብሎ ወደ ጌታ ላካቸው። ሰዎቹም ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ “መጥምቁ ዮሐንስ፣ ‘ይመጣል የተባለልህ አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ብሎ ወደ አንተ ልኮናል” አሉት። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን ከበሽታ፣ ከደዌና ከርኩሳን መናፍስት ፈወሳቸው፤ የብዙ ዐይነ ስውራንንም ዐይን አበራ። ከዮሐንስ ተልከው የመጡትንም እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቈሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔ የማይሰናከል ሁሉ ብፁዕ ነው።” የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፤ “ወደ በረሓ የወጣችሁት ምን ልታዩ ነው? ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸንበቆ? እኮ! ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? ባማረ ልብስ የሚሽሞነሞኑና በድሎት የሚኖሩ በቤተ መንግሥት አሉላችሁ። ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ልታዩ? አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ከነቢይም የሚበልጠውን ነው። እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ “ ‘መንገድህን በፊትህ የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ።’ እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከዮሐንስ የሚበልጥ የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።” ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ይህን የሰሙ ሁሉ፣ የዮሐንስን ጥምቀት በመጠመቅ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር ሰጡ፤ ፈሪሳውያንና ሕግ ዐዋቂዎች ግን በዮሐንስ እጅ ባለመጠመቃቸው፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ዐላማ አቃለሉ። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን ልመስላቸው? ምንስ ይመስላሉ? በገበያ ቦታ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ እንዲህ የሚባባሉ ልጆችን ይመስላሉ፤ “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም።’ ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ጋኔን አለበት አላችሁት፤ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፣ ‘በልቶ የማይጠገብና ጠጪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አላችሁት። ጥበብ ግን ትክክለኛ መሆኗ በልጆቿ ሁሉ ዘንድ ተረጋገጠ።”