ይህንም ሁሉ ደቀ መዝሙርቱ ለዮሐንስ ነገሩት። ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ፥ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ?” ብሎ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ላካቸው። መልእክተኞችም ወደ እርሱ ደርሰው፥ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ? ብሎ መጥምቁ ዮሐንስ ወደ አንተ ልኮናል” አሉት። ያንጊዜም ብዙዎችን ከደዌአቸውና ከሕመማቸው ከክፉዎች አጋንንትም ፈወሳቸው፤ ለብዙዎች ዕውራንም እንዲያዩ ብርሃንን ሰጣቸው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶችም ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል። በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው።” የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ከሄዱ በኋላ ለሕዝቡ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንዲህ ይላቸው ጀመር፥ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ከነፋስ የተነሣ የሚወዛወዝ ሸንበቆን ነውን? ወይስ ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ቀጭን ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? እነሆ፥ በክብር ልብስ ያጌጡስ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ነቢይን ነውን? አዎን፥ እላችኋለሁ፤ ከነቢይም ይበልጣል። እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፥ ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈለት ይህ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም አልተነሣም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን የሚያንሰው ይበልጠዋል።” ሕዝቡም ሁሉ ቀራጮችም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን ጻድቅ ነው አሉት፤ የዮሐንስን ጥምቀት ተጠምቀው ነበርና። ፈሪሳውያንና የሕግ ጻፎች ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቃወሙ፤ በእርሱ አልተጠመቁምና። “እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን እመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? በገበያ ተቀምጠው ባልንጀሮቻቸውን ጠርተው፥ “አቀነቀንላችሁ፥ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾም አወጣንላችሁ፥ አላለቀሳችሁምም የሚሉአቸው ልጆችን ይመስላሉ። መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላ ወይንም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና ጋኔን አለበት አላችሁት። የሰው ልጅም እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እናንተ ግን እነሆ፥ በላተኛና ወይን ጠጪ ሰው፥ የኃጥኣንና የቀራጮች ወዳጅ አላችሁት። ጥበብም ከልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች።”
የሉቃስ ወንጌል 7 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 7:18-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች