የሉቃስ ወንጌል 7
7
ኢየሱስ የመቶ አለቃውን አገልጋይ መፈወሱ
(ማቴ. 8፥5-13)
1እርሱም ለአድማጩ ሕዝብ ንግግሩን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። 2አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባርያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። 3ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ልኮ ባርያውን መጥቶ እንዲያድን ለመነው። 4እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው እንዲህ እያሉ አጥብቀው ለመኑት፦ “ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ 5ሕዝባችንን ይወዳልና፤ ምኵራብም የሠራልን እርሱ ነው።” 6ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ መቶ አለቃው ወዳጆቹን ወደ እርሱ ልኮ እንዲህ አለው፦ “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና ራስህን አታድክም፤ 7ወደ አንተም ለመምጣት እንኳ ራሴን የተገባሁ አድርጌ አልቆጠርሁትም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል። 8እኔ በእርግጥ ከሌሎች ሥልጣናት በታች የተሾምሁ ሰው ነኝ፤ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱንም ‘ሂድ!’ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ብለው ይመጣል፤ ኣገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ!’ ብለው ያደርጋል።” 9ኢየሱስም ይህንን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፤ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ እንዲህ አለ፦ “እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።” 10የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ኣገልጋዩን በመልካም ጤንነት ላይ ሆኖ አገኙት።
ኢየሱስ የአንዲት መበለትን ልጅ ከሞት ማስነሣቱ
11በማግስቱም ናይን ወደምትባል ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱና ብዙ ሕዝብም ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። 12ወደ ከተማይቱም በር በቀረበ ጊዜ፥ እነሆ፥ አንድ የሞተ ሰው ተሸክመው እያወጡ ነበር፤ እርሱም ለእናቱ አንድ ነበረ፤ እርሷም መበለት ነበረች፤ የከተማይቱም ብዙ ሕዝብ ከእርሷ ጋር አብረው ነበሩ። 13ጌታም ባያት ጊዜ ራራላትና፦ “አታልቅሽ፤” አላት። 14ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙትም ቆሙ፤ እርሱም፦ “አንተ ወጣት! ተነሥ እልሃለሁ!” አለ። 15የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ፥ ይናገርም ጀመረ፤ ኢየሱስም ጐልማሳውን ለእናቱ ሰጣት። 16ሁሉንም ፍርሃት ያዛቸው፤ እግዚአብሔርንም እንዲህ እያሉ አመሰገኑ፦ “ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል!” “እግዚአብሔርም ሕዝቡን ጐብኝቶአል!” 17ስለ እርሱም የተነገረው ይህ ነገር በመላው ይሁዳ በዙሪያውም ባለው አገር ሁሉ ተሰራጨ።
ከመጥምቁ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ የተላኩ መልእክተኞች
(ማቴ. 11፥2-19)
18የዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር ሁሉ አወሩለት። ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ 19“የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ወደ ጌታ ላካቸው። 20ሰዎቹም ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉ፦ “መጥምቁ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ወደ አንተ ላከን፦ ‘የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ” 21በዚያች ሰዓት ኢየሱስ ከደዌና ከሚያሠቃይ በሽታ፥ ከክፉዎች መናፍስትም ብዙዎችን ፈወሰ፤ ለብዙ ዐይነ ስውሮችም የማየትን ጸጋ ሰጠ። 22#ኢሳ. 35፥5፤6፤ ኢሳ. 61፥1።እርሱም መልሶ ለተላኩት እንዲህ አላቸው፦ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውሮች ያያሉ፤ የሚያነክሱ ይራመዳሉ፤ በለምጽ የተጠቁ ይነጻሉ፤ መስማት የተሳናቸውም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ 23በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው።”
24የዮሐንስ መልክተኞችም ከሄዱ በኋላ፥ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸምበቆን? 25ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰውን? እነሆ፥ ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱና በቅምጥልነት የሚኖሩ በነገሥታት ቤት አሉ። 26ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፤ ከነቢይም የሚበልጠውን።
27 #
ሚል. 3፥1። “እነሆ፥ መንገድህን አስቀድሞ የሚያዘጋጅ
መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ”
ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው። 28ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። 29#ማቴ. 21፥32፤ ሉቃ. 3፥12።የሰማውም ሕዝብ ሁሉ፥ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ፥ በዮሐንስ ጥምቀት በመጠመቃቸው የእግዚአብሔርን ጻዲቅነት ተቀበሉ፤ 30ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ባለመጠመቃቸው ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ዕቅድ አልተቀበሉም።
31ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን እመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? 32በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፤ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ እንዲህ የሚሉትን
እንቢልታ ነፋንላችሁ፤ አላሸበሸባችሁምም፤
ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁምም።
33መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበር፥ እናንተም “ጋኔን አለበት፤” አላችሁ። 34የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እናንተም “እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፤ የቀራጮችና የኀጢአተኞች ወዳጅ ነው፤” አላችሁ። 35ነገር ግን የጥበብ መጽደቅ በልጆችዋ ሁሉ ተረጋገጠ።
አንድ ፈሪሳዊ እና አንዲት ኀጢአተኛ ሴት
36ከፈሪሳውያንም አንዱ ኢየሱስን ከእርሱ ጋር እንዲበላ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። 37#ማቴ. 26፥7፤ ማር. 14፥3፤ ዮሐ. 12፥3።እነሆም፥ በዚያች ከተማ ኀጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፥ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ አምጥታ ነበር። 38በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ፥ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፤ በራስ ጠጉርዋም ታብሰው፥ እግሩንም ትስመው፥ ሽቶም ትቀባው ነበረች። 39የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ፦ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች፥ እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና፤” ሲል በልቡ አሰበ። 40ኢየሱስም መልሶ፦ “ስምዖን ሆይ! አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ፤” አለው። እርሱም፦ “መምህር ሆይ! ተናገር፤” አለ። 41“አንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት፤ አንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት፤ ሌላው ደግሞ አምሳ። 42የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ዕዳቸውን ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?” 43ስምዖንም ሲመልስ፦ “ብዙ የተወለትን ይመስለኛል፤” አለ። እርሱም፦ “በትክክል ፈረድህ፤” አለው። 44ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ውሃ እንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርሷ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጉርዋም አበሰች። 45አንተ አልሳምኸኝም፤ እርሷ ግን ከገባሁ ጊዜ ጀምሮ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። 46አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርሷ ግን እግሬን ሽቶ ቀባች። 47ስለዚህም እጅግ ወዳለችና ብዙ ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል እልሃለሁ፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።” 48እርሷንም፦ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል፤” አላት። 49ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው፦ “ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው?” ይሉ ጀመር። 50ሴቲቱንም፦ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤” አላት።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 7: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ