የዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር ሁሉ አወሩለት። ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ “የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ወደ ጌታ ላካቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉ፦ “መጥምቁ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ወደ አንተ ላከን፦ ‘የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?’ ” በዚያች ሰዓት ኢየሱስ ከደዌና ከሚያሠቃይ በሽታ፥ ከክፉዎች መናፍስትም ብዙዎችን ፈወሰ፤ ለብዙ ዐይነ ስውሮችም የማየትን ጸጋ ሰጠ። እርሱም መልሶ ለተላኩት እንዲህ አላቸው፦ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውሮች ያያሉ፤ የሚያነክሱ ይራመዳሉ፤ በለምጽ የተጠቁ ይነጻሉ፤ መስማት የተሳናቸውም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው።” የዮሐንስ መልክተኞችም ከሄዱ በኋላ፥ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ያማረ ልብስ የለበሰውን ሰውን? እነሆ፥ ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱና በቅምጥልነት የሚኖሩ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፤ ከነቢይም የሚበልጠውን። “እነሆ፥ መንገድህን አስቀድሞ የሚያዘጋጅ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ” ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው። ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። የሰማውም ሕዝብ ሁሉ፥ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ፥ በዮሐንስ ጥምቀት በመጠመቃቸው የእግዚአብሔርን ጻዲቅነት ተቀበሉ፤ ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ባለመጠመቃቸው ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ዕቅድ አልተቀበሉም። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ እንግዲህ የዚህን ትውልድ ሰዎች በምን እመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፤ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ እንዲህ የሚሉትን እንቢልታ ነፋንላችሁ፤ አላሸበሸባችሁምም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁምም። መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበር፥ እናንተም “ጋኔን አለበት፤” አላችሁ። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እናንተም “እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፤ የቀራጮችና የኀጢአተኞች ወዳጅ ነው፤” አላችሁ። ነገር ግን የጥበብ መጽደቅ በልጆችዋ ሁሉ ተረጋገጠ።
የሉቃስ ወንጌል 7 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 7:18-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች