ዘሌዋውያን 4:1-26
ዘሌዋውያን 4:1-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፤ “ ‘የተቀባውም ካህን በሕዝቡ ላይ በደል የሚያስከትል ኀጢአት ቢሠራ፣ ስለ ሠራው ኀጢአት እንከን የሌለበት አንድ ወይፈን ለእግዚአብሔር የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫን፤ በእግዚአብሔርም ፊት ይረደው። የተቀባው ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ ከመቅደሱ መጋረጃ ትይዩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። ካህኑ ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለውንና ሽታው ጣፋጭ የሆነ ዕጣን የሚታጠንበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ። የተረፈውን የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። ለኀጢአት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ይኸውም፦ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብና ከሆድ ዕቃው ጋራ የተያያዘውን ሥብ፣ ሁለቱንም ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጕበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋራ ዐብሮ አውጥቶ ያቅርብ፤ ለኅብረት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን እንዳወጣ ሁሉ ሥቡን ያውጣ፤ ካህኑም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለው። ነገር ግን የወይፈኑን ቈዳና ሥጋውን ሁሉ፣ ጭንቅላቱንና እግሮቹን፣ ሆድ ዕቃውንና ፈርሱን፣ የወይፈኑን ብልት ሁሉ ከሰፈር ውጭ ዐመድ ወደሚፈስስበት በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነው ስፍራ ይውሰደው፤ በተቈለለው ዐመድ ላይ ዕንጨት አንድዶ ያቃጥለው። “ ‘መላው የእስራኤል ሕዝብ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አታድርጉ ብሎ እግዚአብሔር ካዘዘውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ ይህ ሕዝብ ጥፋቱ ባይታወቀውም በደለኛ ነው። የሕዝቡ ጉባኤ ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን በመገናኛው ድንኳን ፊት ያቅርብ። የሕዝቡም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ፊት እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫኑ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር ፊት ይታረድ። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ። ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ በመጋረጃው ትይዩ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለውን የመሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። ከወይፈኑም ሥቡን ሁሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ለኀጢአት መሥዋዕት ባቀረበው ወይፈን ላይ እንዳደረገው ሁሉ፣ በዚህኛውም ወይፈን ያድርግ፤ በዚህም መሠረት ካህኑ ስለ ሕዝቡ ያስተሰርያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። ወይፈኑንም ከሰፈር ውጭ ያውጣው፤ የመጀመሪያውን ወይፈን እንዳቃጠለው ሁሉ ይህኛውንም ያቃጥል፤ ይህም ስለ ሕዝቡ የሚቀርብ የኀጢአት መሥዋዕት ነው። “ ‘አንድ የሕዝብ መሪ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አምላኩም እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ እርሱ በደለኛ ነው። ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ እንከን የሌለበትን ተባዕት ፍየል የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበትም ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። ካህኑም ከመሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍስሰው። የኅብረት መሥዋዕቱን እንዳቃጠለ ሁሉ ሥቡንም በሙሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።
ዘሌዋውያን 4:1-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ማናቸውም ሰው ሳያውቅ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ የተቀባውም ሊቀ ካህናት በሕዝቡ ላይ በደል እንዲቈጠርባቸው ኀጢአት ቢሠራ፥ ስለ ሠራው ስለ ኀጢአቱ ከመንጋው ነውር የሌለበትን ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኀጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል። ወይፈኑንም ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፤ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል። ተቀብቶ የተሾመው ካህን ከወይፈኑ ደም በእጁ ወስዶ ወደ ምስክሩ ድንኳን ያመጣዋል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። ካህኑም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ጣፋጭ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የወይፈኑንም ደም ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። ለኀጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር፥ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ወይፈን እንደ ተወሰደው ይወስዳል፤ ካህኑም ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ያቀርበዋል። የወይፈኑን ቍርበት፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ ፈርሱንም፤ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አመድ ወደሚፈስስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስዱታል፤ በዕንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥሉታል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። “የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከማኅበሩ ዐይን ቢሸሸግ፥ እግዚአብሔርም አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፉ፤ ከዚህም በኋላ፥ የሠሩት ኀጢአት ቢታወቃቸውና ንስሓ ቢገቡ ማኅበሩ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ ምስክሩም ድንኳን ፊት ያመጡታል። የማኅበሩም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርዱታል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ ምስክሩ ድንኳን ያመጣል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ባለው በዕጣን መሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል። እንዲህም በወይፈኑ ያደርጋል፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት በታረደው ወይፈን እንደ አደረገ እንዲሁ በዚህ ያደርጋል፤ ካህኑም ኀጢአታቸውን ያስተሰርያል፤ ኀጢአቸውም ይሰረይላቸዋል። ወይፈኑንም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ይወስዱታል፤ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠሉ ያቃጥሉታል፤ የማኅበሩ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና። “መኰንንም ኀጢአትን ቢሠራ፥ ሳያውቅም እግዚአብሔር አምላኩ፦ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ እንዲህም ቢበድል፥ የሠራው ኀጢአት ቢታወቀውና ንስሓ ቢገባ፥ ከፍየሎች ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቍርባኑ ያቀርባል፤ በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና። ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። ስቡንም ሁሉ እንደ ደኅንነት መሥዋዕት ስብ፥ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። ካህኑም ኀጢአቱን ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል።
ዘሌዋውያን 4:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ የተቀባውም ካህን በሕዝቡ ላይ በደል እንዲቈጠርባቸው ኃጢአት ቢሠራ፥ ስለ ሠራው ስለ ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል። ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፥ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ጣፋጭ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የተረፈውንም የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። ለኃጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር፥ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ወይፈን እንደ ተወሰደው ይወስዳል። ካህኑም ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ያቃጥለዋል። የወይፈኑን ቁርበት፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ ፈርሱንም፥ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አመድ ወደሚፈስስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስደዋል፥ በእንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥለዋል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከጉባኤው ፊት ቢሸሸግ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፉ፥ እንዲህም ቢበድሉ፥ የሠሩት ኃጢአት ሲታወቅ ጉባኤው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ መገናኛውም ድንኳን ፊት ያመጡታል። የጉባኤውም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመጋረጃው ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። በመገናኛውም ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ባለው በዕጣን መሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። እንዲህም በወይፈኑ ያደርጋል፤ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት በታረደው ወይፈን እንዳደረገ እንዲሁ በዚህ ያደርጋል፤ ካህኑም ስለ እነርሱ ያስተሰርያል፥ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። ወይፈኑንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ ይወስደዋል፥ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠለ ያቃጥለዋል፤ ይህ የማኅበሩ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። አንድ መኰንንም ኃጢአትን ሲሠራ፥ ሳያውቅም እግዚአብሔር አምላኩ፦ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ሲተላለፍ፥ እንዲህም ሲበድል፥ የሠራው ኃጢአት ቢታወቅ፥ ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቍርባኑ ያቀርበዋል፤ በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ያደርገዋል፤ የተረፈውንም ደም ለሚቃጠል መሥዋዕት ከሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። ስቡንም ሁሉ እንደ ደኅንነት መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።
ዘሌዋውያን 4:1-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ይህ ነው፦ ማንም ሰው ተሳስቶ ኃጢአት ቢሠራ ወይም ባለማወቅ ከእግዚአብሔር ትእዛዞች አንዱን ቢተላለፍ ከዚህ የሚከተለውን ሥርዓት ይጠብቅ፦ “ተቀብቶ የተሾመው ካህን ኃጢአት ሠርቶ ሕዝቡን እንደ በደለኛ የሚያስቈጥር ሆኖ ቢገኝ፥ ምንም ነውር የሌለበትን አንድ ወይፈን ያምጣ፤ ስለ ኃጢአቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ያቅርበው። ኰርማውንም ወደ ድንኳኑ ደጃፍ አምጥቶ እጁን በእንስሳው ራስ ላይ በመጫን በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይረደው። ከዚያም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ከኰርማው ደም ጥቂት ወስዶ ወደ ድንኳኑ በማስገባት፥ በቤተ መቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሆኖ ደሙን በጣቱ እያጠቀሰ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። ከዚያም ደግሞ ጥቂት ደም ወስዶ በድንኳኑ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው አራት ማእዘን ጒጦች ላይ ያኑር፤ የተረፈውን ደም ግን በድንኳኑ መግቢያ በኩል የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ሥር ያፍስሰው። ከዚህም ኰርማ ስቡን ሁሉ፥ ኲላሊቶቹን፥ እነርሱም የተሸፈኑበትን ስብና እንዲሁም እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን ከሸፈነው ስብ ምርጥ የሆነውን ይውሰድ። ሊቀ ካህናቱም ይህን ስብ ሁሉ ተቀብሎ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለው፤ አፈጻጸሙም ለአንድነት መሥዋዕት ከሚቀርበው የእንስሳ ስብ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚያቀርበው ዐይነት ይሁን። ነገር ግን ቆዳውን፥ ሥጋውን ሁሉ፥ ራሱንና እግሮቹን፥ አንጀቱንና የሆድ ዕቃውን በሙሉ፥ ከሰፈር ውጪ ያውጣ፤ ዐመድ ወደሚፈስበት ርኩስ ወዳልሆነ ስፍራ በመውሰድ እንጨት ሰብስቦ ያንድድና በእሳት ያቃጥለው። “ባለማወቅ ኃጢአት የሠራው መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ቢሆንና፥ ጉዳዩም ከማኅበረሰቡ ቢሰወር፥ ይህም ኃጢአት እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸው ትእዛዞች አንዱን በማፍረስ በደለኞች ቢያደርጋቸው፥ የተሠራው ኃጢአት እንደ ታወቀ ወዲያውኑ ማኅበሩ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ያምጣ፤ እርሱንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ያቅርቡት፤ የማኀበሩም አለቆች እጆቻቸውን በኰርማው ራስ ላይ ይጫኑበትና በዚያው በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይታረድ። የተቀባው ካህንም ከኰርማው ደም ጥቂት ይዞ ወደ ድንኳኑ ይግባ፤ በቤተ መቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሆኖ ደሙን በጣቱ እያጠቀሰ ሰባት ጊዜ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይርጨው። ደግሞም ጥቂት ደም ወስዶ በድንኳኑ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ባለው በመሠዊያው ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚያም የተረፈውን ደም በድንኳኑ መግቢያ በኩል የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ሥር ያፍስሰው። ከዚህም ቀጥሎ የዚህን ወይፈን ስብ ሁሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው። አፈጻጸሙም ለኃጢአት መሥዋዕት በሚቀርበው ኰርማ ላይ በሚደረገው ዐይነት ይሁን፤ በዚህም ዐይነት ስለ ሕዝቡ ኃጢአት መሥዋዕትን ያቀርባል፤ ሕዝቡም የኃጢአታቸውን ይቅርታ ያገኛሉ። ከዚህም በኋላ ኰርማውን ከሰፈር ወደ ውጪ አውጥቶ ስለ ራሱ በደል በቀረበው ወይፈን ላይ እንደተፈጸመው ዐይነት ያቃጥለው፤ ይህም የማኅበረሰቡን ኃጢአት የሚያስወግድ መሥዋዕት ይሆናል። “ኃጢአት የሠራውና ባለማወቅ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዘው ትእዛዝ በመተላለፍ በደለኛ የሆነው የሕዝብ መሪ ከሆነ፥ ኃጢአት መሥራቱን እንዳወቀ ወዲያውኑ ምንም ነውር የሌለበትን ተባዕት ፍየል የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ። እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ጭኖ፥ ከመሠዊያው በስተ ሰሜን በኩል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይረደው፤ ይህም ኃጢአትን የሚያስወግድ መሥዋዕት ይሆናል። ካህኑ የእንስሳውን ደም በጣቱ እያጠቀሰ በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያው አራት ማእዘን ላይ በሚገኙ ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚህ የተረፈውንም በሚቃጠል መሥዋዕት በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው። ስቡንም ሁሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ የዚህም አፈጻጸም ለአንድነት መሥዋዕት የቀረቡትን እንስሶች ስብ ባቃጠለው ዐይነት ይሁን፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ ስለ ሕዝቡ መሪ ኃጢአት መሥዋዕት በማቅረብ ያስተሰርያል፤ መሪውም የኃጢአቱን ይቅርታ ያገኛል።
ዘሌዋውያን 4:1-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ማናቸውም ሰው ባለማወቅ ጌታ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ኃጢአት ቢሠራ፥ የተቀባውም ካህን ኃጢአት ሠርቶ በሕዝቡ ላይ በደል ቢያመጣ፥ ስለ ሠራው ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለጌታ ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርባል። ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በጌታ ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናል፥ ወይፈኑንም በጌታ ፊት ያርደዋል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በጌታ ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ትዩዩ ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጫል። ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በጌታ ፊት ባለው መዐዛው ያማረ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የተረፈውንም የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ በታች ያፈስሳል። ለኃጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶች ጋር፥ ለአንድነት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን እንደሚወሰደው ከወሰደ በኋላ፥ ካህኑ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለዋል። የወይፈኑን ቆዳ፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ ፈርሱንም፥ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ አመድ ወደሚፈስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስዳል፥ በእንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥለዋል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። “የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከጉባኤው ፊት ቢሸሸግ፥ ጌታም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዱን ሠርተው ቢበድሉ፥ የሠሩትም ኃጢአት ሲታወቅ ጉባኤው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ከመንጋው ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ መገናኛውም ድንኳን ፊት ያመጡታል። የጉባኤውም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በጌታ ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑም በጌታ ፊት ይታረዳል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በጌታ ፊት በመጋረጃው ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። በመገናኛውም ድንኳን ውስጥ በጌታ ፊት ባለው በመሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ በታች ያፈስሳል። ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። የኃጢአት መሥዋዕት በሆነው ወይፈን ላይ እንዳደረገው እንዲሁ በዚህ ወይፈን ላይ ደግሞ ያደርጋል፤ እርሱም እንዲህ ያደርግበታል፤ ካህኑም ስለ እነርሱ ያስተሰርያል፥ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። ወይፈኑንም ከሰፈሩ ውጭ ይወስዳል፥ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠለ ያቃጥለዋል፤ ይህ የማኅበሩ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። “አንድ ገዢም ኃጢአትን ቢሠራ፥ ጌታም አምላኩ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ አንዱን ባለማወቅ ሠርቶ ቢበድል፥ ለእርሱም የሠራው ኃጢአት የታወቀ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቁርባኑ ያቀርባል፤ በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በጌታ ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ የተረፈውንም ደም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ በታች ያፈስሳል። ስቡንም ሁሉ እንደ አንድነት መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል። ካህኑም ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።