የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 4

4
ባለ ማወቅ ስለ ተፈጸመ በደል የሚቀርብ መሥዋዕት
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ይህ ነው፦ ማንም ሰው ተሳስቶ ኃጢአት ቢሠራ ወይም ባለማወቅ ከእግዚአብሔር ትእዛዞች አንዱን ቢተላለፍ ከዚህ የሚከተለውን ሥርዓት ይጠብቅ፦
3“ተቀብቶ የተሾመው ካህን ኃጢአት ሠርቶ ሕዝቡን እንደ በደለኛ የሚያስቈጥር ሆኖ ቢገኝ፥ ምንም ነውር የሌለበትን አንድ ወይፈን ያምጣ፤ ስለ ኃጢአቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ያቅርበው። 4ኰርማውንም ወደ ድንኳኑ ደጃፍ አምጥቶ እጁን በእንስሳው ራስ ላይ በመጫን በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይረደው። 5ከዚያም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ከኰርማው ደም ጥቂት ወስዶ ወደ ድንኳኑ በማስገባት፥ 6በቤተ መቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሆኖ ደሙን በጣቱ እያጠቀሰ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። 7ከዚያም ደግሞ ጥቂት ደም ወስዶ በድንኳኑ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው አራት ማእዘን ጒጦች ላይ ያኑር፤ የተረፈውን ደም ግን በድንኳኑ መግቢያ በኩል የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ሥር ያፍስሰው። 8ከዚህም ኰርማ ስቡን ሁሉ፥ 9ኲላሊቶቹን፥ እነርሱም የተሸፈኑበትን ስብና እንዲሁም እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን ከሸፈነው ስብ ምርጥ የሆነውን ይውሰድ። 10ሊቀ ካህናቱም ይህን ስብ ሁሉ ተቀብሎ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለው፤ አፈጻጸሙም ለአንድነት መሥዋዕት ከሚቀርበው የእንስሳ ስብ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚያቀርበው ዐይነት ይሁን። 11ነገር ግን ቆዳውን፥ ሥጋውን ሁሉ፥ ራሱንና እግሮቹን፥ አንጀቱንና የሆድ ዕቃውን በሙሉ፥ 12ከሰፈር ውጪ ያውጣ፤ ዐመድ ወደሚፈስበት ርኩስ ወዳልሆነ ስፍራ በመውሰድ እንጨት ሰብስቦ ያንድድና በእሳት ያቃጥለው።
13“ባለማወቅ ኃጢአት የሠራው መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ቢሆንና፥ ጉዳዩም ከማኅበረሰቡ ቢሰወር፥ ይህም ኃጢአት እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸው ትእዛዞች አንዱን በማፍረስ በደለኞች ቢያደርጋቸው፥ 14የተሠራው ኃጢአት እንደ ታወቀ ወዲያውኑ ማኅበሩ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ያምጣ፤ እርሱንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ያቅርቡት፤ 15የማኀበሩም አለቆች እጆቻቸውን በኰርማው ራስ ላይ ይጫኑበትና በዚያው በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይታረድ። 16የተቀባው ካህንም ከኰርማው ደም ጥቂት ይዞ ወደ ድንኳኑ ይግባ፤ 17በቤተ መቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሆኖ ደሙን በጣቱ እያጠቀሰ ሰባት ጊዜ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይርጨው። 18ደግሞም ጥቂት ደም ወስዶ በድንኳኑ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ባለው በመሠዊያው ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚያም የተረፈውን ደም በድንኳኑ መግቢያ በኩል የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ሥር ያፍስሰው። 19ከዚህም ቀጥሎ የዚህን ወይፈን ስብ ሁሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው። 20አፈጻጸሙም ለኃጢአት መሥዋዕት በሚቀርበው ኰርማ ላይ በሚደረገው ዐይነት ይሁን፤ በዚህም ዐይነት ስለ ሕዝቡ ኃጢአት መሥዋዕትን ያቀርባል፤ ሕዝቡም የኃጢአታቸውን ይቅርታ ያገኛሉ። 21ከዚህም በኋላ ኰርማውን ከሰፈር ወደ ውጪ አውጥቶ ስለ ራሱ በደል በቀረበው ወይፈን ላይ እንደተፈጸመው ዐይነት ያቃጥለው፤ ይህም የማኅበረሰቡን ኃጢአት የሚያስወግድ መሥዋዕት ይሆናል።
22“ኃጢአት የሠራውና ባለማወቅ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዘው ትእዛዝ በመተላለፍ በደለኛ የሆነው የሕዝብ መሪ ከሆነ፥ 23ኃጢአት መሥራቱን እንዳወቀ ወዲያውኑ ምንም ነውር የሌለበትን ተባዕት ፍየል የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ። 24እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ጭኖ፥ ከመሠዊያው በስተ ሰሜን በኩል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ይረደው፤ ይህም ኃጢአትን የሚያስወግድ መሥዋዕት ይሆናል። 25ካህኑ የእንስሳውን ደም በጣቱ እያጠቀሰ በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያው አራት ማእዘን ላይ በሚገኙ ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚህ የተረፈውንም በሚቃጠል መሥዋዕት በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው። 26ስቡንም ሁሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ የዚህም አፈጻጸም ለአንድነት መሥዋዕት የቀረቡትን እንስሶች ስብ ባቃጠለው ዐይነት ይሁን፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ ስለ ሕዝቡ መሪ ኃጢአት መሥዋዕት በማቅረብ ያስተሰርያል፤ መሪውም የኃጢአቱን ይቅርታ ያገኛል።
27“ኃጢአት የሠራውና ባለማወቅም እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸው ትእዛዞች አንዱን የተላለፈውና በደለኛ የሆነው ሰው ከተራው ሕዝብ ወገን ከሆነ፥ 28ኃጢአት መሥራቱን እንዳወቀ ወዲያውኑ ምንም ነውር የሌለባት እንስት ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ያቅርብ። 29እጁንም በእንስሳይቱ ራስ ላይ ይጫን፤ ከመሠዊያው በስተ ሰሜን ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ ይረዳት። 30ካህኑም የእንስሳይቱን ደም በጣቱ እያጠቀሰ በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያው አራት ማእዘን በሚገኙ ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚህም የተረፈውን ደም በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው። 31ለአንድነት መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶችን ስብ በመግፈፍ በሚፈጽመው ዐይነት የዚህችንም እንስሳ ስብ ሁሉ ገፎ ያስወግድ፤ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህ ዐይነት ካህኑ ስለዚያ ሰው የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ያቀርባል፤ ያም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል። #ዘኍ. 15፥27-28።
32“ሰውየው ስለ ኃጢአቱ ስርየት የበግ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ ምንም ነውር የሌለባት እንስት ትሁን። 33እርሱም በእንስሳይቱ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ ከመሠዊያው በስተሰሜን በኩል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ ይረዳት፤ 34ካህኑም የእንስሳይቱን ደም በጣቱ እያጠቀሰ በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያው አራት ማእዘን በሚገኙ ጒጦች ላይ ያኑር፤ ከዚህም የተረፈውን ደም በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው፤ 35ከዚህም በኋላ ለአንድነት መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶችን ስብ በመግፈፍ በሚፈጽመው ዐይነት የዚህችንም እንስሳ ስብ ሁሉ ገፎ ያስወግድ፤ እርሱንም ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የምግብ መባ ጋር በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ ስለዚያ ሰው የኃጢአት መሥዋዕትን በማቅረብ ያስተስርይለት፤ ያም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ