የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 5

5
የበደል መሥዋዕት የሚቀርብበት ምክንያት
1“አንድ ሰው በፍርድ አደባባይ በይፋ ለምስክርነት መጥቶ ያየውን ወይም ስለ ጉዳዩ የሚያውቀውን ነገር ባይመሰክር ኃጢአት ይሆንበታል።
2“አንድ ሰው ባለማወቅ ማናቸውንም ርኩስ ነገር ለምሳሌ የአውሬ፥ የቤት እንስሳ ወይም በደረቱ እየተሳበ የሚንቀሳቀስ ፍጥረት በድን ቢነካ፥ ያደረገውን ስሕተት ካወቀበት ጊዜ አንሥቶ በደል ይሆንበታል።
3“አንድ ሰው ባለማወቅ ምንም ዐይነት ይሁን ከሰውነት የሚፈስ አንዳች ርኩስ ነገር ቢነካ፥ ያደረገውን ስሕተት ካወቀበት ጊዜ አንሥቶ በደል ይሆንበታል።
4“አንድ ሰው ለክፉም ሆነ ለደግ ስለ ምንም ነገር ያለ ጥንቃቄ በግዴለሽነት ስእለት ቢሳል፥ ያደረገውን ስሕተት ካወቀበት ጊዜ አንሥቶ በደል ይሆንበታል።
5“አንድ ሰው ከእነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ቢሆን የሠራውን ኃጢአት ይናዘዝ። 6ስለ ሠራው ኃጢአት ለእግዚአብሔር የበደል መሥዋዕት ያምጣ፤ ይኸውም ከመንጋው የበግ ወይም የፍየል እንስት ይሆናል፤ ካህኑም ስለ ኃጢአቱ ያስተሰርይለታል።
7“አንድ ሰው በግ ወይም ፍየል ማቅረብ ካልቻለ ግን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት ዋኖሶች፥ አንደኛይቱን ስለ ኀጢአት ለሚቀርብ መሥዋዕት፥ ሁለተኛይቱንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ የበደሉን ዕዳ ይከፍል ዘንድ ለእግዚአብሔር ያምጣ። 8እርሱም እነዚያን አምጥቶ ለካህኑ ይስጥ፤ ካህኑም ከሁለቱ አንዲቱን ራስዋን ሳይቈርጥ አንገትዋን ቆልምሞ ለበደል መሥዋዕት ያቅርብ፤ 9ከደሙም ጥቂት ወስዶ በመሠዊያው ጐን ይርጨው፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ሥር ያፍስሰው፤ ይህም የኃጢአት ማስወገጃ መሥዋዕት ነው። 10ሌላይቱንም በሥርዓቱ መሠረት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ ስለ ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ያቀርባል፤ በደል የሠራውም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል።
11“አንድ ሰው ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት ዋኖሶች ማቅረብ ባይችል፥ አንድ ኪሎ የላመ ዱቄት ስለ ኃጢአቱ ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ፤ እርሱም ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት እንጂ የእህል መባ ስላልሆነ የወይራ ዘይት ወይም ዕጣን አይጨምርበት። 12እርሱንም አምጥቶ ለካህኑ ይስጠው፤ ካህኑም ከዚያ ዱቄት በእፍኙ ወስዶ ሁሉም ለእግዚአብሔር የቀረበ መሆኑን በማመልከት በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ እርሱም ኃጢአትን የሚያስወግድ መሥዋዕት ይሆናል። 13ካህኑም በዚህ ዐይነት ስለዚያ ሰው ኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕትን ያቀርባል፤ ያም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል፤ የቀረው ዱቄት የእህል መባ በሚቀርብበት ዐይነት ለካህኑ ይሁን።”
የበደል መሥዋዕት አቀራረብ
14እግዚአብሔር ሙሴን አለው፦ 15“አንድ ሰው ለእግዚአብሔር መክፈል የሚገባውን ባለመክፈል ሳያውቅ በደል ቢፈጽም፥ ለእግዚአብሔር የበደል መሥዋዕት የሚሆን ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ ያምጣ፤ ወይም በቤተ መቅደሱ ሚዛን መሠረት ዋጋው ተገምግሞ ይክፈል። ይህም የበደል መሥዋዕት ነው። 16ቀድሞ መስጠት ይገባው ከነበረው ጋር አንድ አምስተኛ ጨምሮ ያምጣ፤ እርሱንም አምጥቶ ለካህኑ ይስጥ፤ ካህኑም እንስሳውን ስለ ሰውየው ኃጢአት መሥዋዕት አድርጎ ያቅርበው፤ በደል የሠራውም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል።
17“አንድ ሰው ባለማወቅ ከእግዚአብሔር ትእዛዞች አንዲቱን ቢተላለፍ በደለኛ ይሆናል። 18ከመንጋው ምንም ነውር የሌለበት ተባዕት በግ ስለ በደሉ መሥዋዕት አድርጎ ወደ ካህን ያምጣ፤ ዋጋውም ተገምግሞ በይፋ በታወቀው ተመን ይወሰን፤ ካህኑም የእንስሳውን መሥዋዕት ስለዚያ ሰው ያቅርብ፤ በደል የሠራውም ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል። 19ይህም ያ ሰው በእግዚአብሔር ላይ ስለ ፈጸመው በደል የኃጢአቱ ማስተስረያ መሥዋዕት ነው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ