የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 6

6
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ማንም ሰው በዐደራ የተሰጠውን ንብረት ባለመመለስ እግዚአብሔርን ቢበድል፥ ወይም የሰውን ንብረት በመቀማት፥ ወይም አታሎ በመውሰድ፥ 3ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም በማለት በሐሰት ቢምል፥ ሰዎች ከሚፈጽሙአቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ ቢበድል፥ 4ማንም ሰው እነዚህን በደሎች ፈጽሞ ኃጢአተኛ ቢሆን፥ በቅሚያና በማታለል የወሰደውን፥ በዐደራ የተቀበለውንና ጠፍቶ ያገኘውን ንብረት ይመልስ፤ 5ወይም በሐሰት ምሎ የወሰደውን ሁሉ አንድ አምስተኛ ጨምሮ ለባለቤቱ ይክፈል። 6ለበደሉም ማስተስረያ ምንም ነውር የሌለበት አንድ ተባዕት በግ ወይም በታወቀው ተመን የተተመነውን ገንዘብ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ እርሱንም አምጥቶ ለካህኑ ይስጥ። 7ካህኑም ስለዚያ ሰው ኃጢአት ማስተስረያ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ በደለኛ ከሆነበት ጉዳይ ሁሉ ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል።” #ዘኍ. 5፥5-8።
በሙሉ ስለሚቃጠል መሥዋዕት
8እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 9“ለአሮንና ለልጆቹ የምትሰጣቸው የሥርዓት መመሪያ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት ሌሊቱን ሁሉ በመሠዊያው ላይ እንዲቈይ ተደርጎ እሳቱ ሲነድ ይደር፤ 10ካህኑም ከከፈይ የተሠራ ቀሚሱንና ሱሪውን ለብሶ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳት ከበላው በኋላ የቀረውን ዐመድ ሰብስቦ በመሠዊያው ጐን ያፍስሰው። 11ከዚያም በኋላ ልብሱን ለውጦ ያን ዐመድ ተሸክሞ ከሰፈር ውጪ ያውጣ፤ ንጹሕ በሆነውም ቦታ ይድፋው። 12በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ሳይጠፋ ሌሊትና ቀን ዘወትር ሲነድ ይኑር፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ የማገዶ እንጨት ይጨምርበት፤ በእርሱ ላይ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አመቻችቶ በማኖር የአንድነት መሥዋዕቱን ስብ ያቃጥለው። 13እሳቱም ሳይጠፋ በመሠዊያው ላይ ሁልጊዜ ይንደድ።
የእህል መባ
14“ስለ እህል መባ አቀራረብ የተደነገጉት መመሪያዎች እነዚህ ናቸው፦ ትውልዱ ከአሮን ዘር የሆነ ካህን የእህሉን መባ በመሠዊያው ፊት ለፊት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ 15ከዚህም በኋላ ካህኑ ዘይት ካለበት ከላመ ዱቄት በእፍኙ ወስዶና በእህሉ መባ ላይ ያለውን ዕጣን በሙሉ አንሥቶ ለእግዚአብሔር ያቀረበ መሆኑን ለማሳወቅ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ የዚህም መሥዋዕት መዓዛ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ይሆናል። 16ከእርሱ የተረፈውን ካህናቱ ይበሉታል፤ እርሾ ሳይጨመርበት ተጋግሮ በተቀደሰው ስፍራ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ይበሉታል። 17እርሾ ተጨምሮበት አይጋገርም፤ ከሚነድ ቊርባኔ ለእነርሱ ድርሻ እንዲሆን የሰጠኋቸውና እንደ ኃጢአት መሥዋዕትና እንደ በደል መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ነው። 18በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ትውልዱ ከአሮን ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ለእግዚአብሔር ከቀረበው መባ ለእርሱ የተመደበለትን ፈንታ መብላት ይችላል፤ መባውን የሚነካ ሁሉ በቅድስናው ኀይል ይቀሠፋል።”
19እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 20“ካህኑ በሚሾምበት ቀን መጠኑ በየዕለቱ ከሚቀርበው የእህል መባ ጋር እኩል የሆነ አንድ ኪሎ የላመ ዱቄት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ፤ እርሱም ከፊሉ ጠዋት፥ ከፊሉ ደግሞ ማታ መሥዋዕት ሆኖ ይቅረብ፤ 21በዘይት ተለውሶና በሚገባ ተቀላቅሎ እንደ እህል መሥዋዕት ከተጋገረ በኋላ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የእህል መባ ሆኖ ይቅረብ፤ 22ከአሮን ተወላጆች መካከል ተቀብቶ የክህነትን ሥልጣን የሚረከብ ያን ያዘጋጃል፤ ያም የእግዚአብሔር ቋሚ ድርሻ ስለ ሆነ በሙሉ መቃጠል አለበት። 23ካህኑ ከሚያቀርበው የእህል መባ ምንም ሳይበላ ሁሉም መቃጠል አለበት።”
ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት
24እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 25“ለአሮንና ለልጆቹ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘የኃጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚቀርበው እንስሳ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ይታረድ። ይህም እጅግ የተቀደሰ ነው። 26እንስሳውን የሚሠዋውም ካህን በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ባለው የተቀደሰ ስፍራ ይብላው፤ 27ሰውም ሆነ ማናቸውም ነገር ያን ሥጋ ቢነካ በቅድስናው ኀይል ይቀሠፋል፤ ማናቸውም የልብስ ዐይነት የእንስሳው ደም ቢፈስበት፥ በተቀደሰ ስፍራ ይታጠብ፤ 28ሥጋ የተቀቀለበት ማናቸውም የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ ሥጋው የተቀቀለው በነሐስ ዕቃ ከሆነም ተፈግፍጎ በውሃ ይለቃለቅ። 29ከካህናቱ ቤተሰብ ወንድ የሆነ ሁሉ ይህን መሥዋዕት ይመገብ፤ እርሱ እጅግ የተቀደሰ መሥዋዕት ነው። 30ኃጢአትን ለማስወገድ በሚደረገው ሥርዓት ደሙ ወደ ድንኳኑ ውስጥ የገባ ከሆነ ግን እንስሳው መበላት የለበትም፤ ሁሉም በእሳት ይቃጠል።’

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ