ኦሪት ዘሌዋውያን 3
3
የአንድነት መሥዋዕት
1ማንኛውም ሰው ከቀንድ ከብቱ ለእግዚአብሔር የአንድነት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ነውር የሌለበትን አንድ ኰርማ ወይም ላም መርጦ ያምጣ። 2መሥዋዕት አቅራቢው ሰው መባ አድርጎ በሚያቀርበው እንስሳ ራስ ላይ እጁን ጭኖ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ ይረደው፤ የአሮን ዘር የሆኑ ካህናትም ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ዙሪያ ይርጩት። 3ለአንድነት መሥዋዕት ከሚቀርበው መባ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡት ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነው ስብ በሙሉ፥ 4ኲላሊቶቹና በእነርሱ ላይ የሚገኘው ስብ፥ እንዲሁም እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን ከሚሸፍነው ስብ ምርጥ የሆነው ናቸው። 5ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በመሆኑ የአሮን ልጆች በሚቃጠለው መሥዋዕት መሠዊያ ላይ ያቃጥሉት፤ ይህ ዐይነቱ መሥዋዕት መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነው።
6ስለ አንድነት የሚቀርበው መሥዋዕት በግ ቢሆን፥ ተባዕትም ሆነ እንስት ምንም ነውር የማይገኝበት ይሁን። 7አንድ ሰው የሚያቀርበው መባ የበግ ጠቦት ቢሆን፥ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርበው፤ 8እጁን በጠቦቱ ራስ ላይ ጭኖ በድንኳኑ ደጃፍ ፊት ለፊት ይረደው፤ ካህናቱም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ይርጩት። 9ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበው ከአንድነቱ መሥዋዕት ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡት ስቡና ከጀርባ አጥንቱ ሥር የተቈረጠው ላቱ በሙሉ፥ የሆድ ዕቃው የሚሸፈንበት ስብ ሁሉ፥ 10ኲላሊቶቹና እነርሱ የተሸፈኑበት ስብ፥ እንዲሁም እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን የሚሸፍነው ምርጥ ስብ ናቸው። 11ካህኑም ይህን ሁሉ ለእግዚአብሔር የምግብ መባ አድርጎ በማቅረብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።
12አንድ ሰው ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው መባ ፍየል ከሆነ፥ በእግዚአብሔር ድንኳን ፊት ያቅርበው፤ 13እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ጭኖ በድንኳኑ ፊት ለፊት ይረደው፤ ካህናቱ ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ዙሪያ ይርጩት፤ 14ከዚህም እንስሳ ሥጋ የሚከተሉትን ክፍሎች የምግብ መባ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ያቅርቡ፤ ይኸውም የሆድ ዕቃው የተሸፈነበትን ስብ ሁሉ፥ 15ኲላሊቶቹንና እነርሱ የተሸፈኑበትን ስብ፥ እንዲሁም እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱ ከተሸፈነበት ስብ ምርጥ የሆነውን ወስደው፥ 16ካህኑ ይህን ሁሉ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ ስብ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሁን። 17ከእስራኤላውያን ወገን ስብ የሆነውን ሥጋ ወይም የእንስሶችን ደም የሚመገብ አይኑር፤ ይህም እስራኤላውያን በሚኖሩበት ዘመንና ቦታ ሁሉ ለዘለዓለሙ ተጠብቆ የሚኖር ቋሚ ሥርዓት ይሁን።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 3: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997