ኦሪት ዘሌዋውያን 2
2
የእህል መባ
1ማነኛውም ሰው ለእግዚአብሔር የእህል መባ በሚያቀርብበት ጊዜ ምርጥ ዱቄት መሆን አለበት፤ በእርሱም ላይ የወይራ ዘይትና ዕጣን ይጨምርበት፤ 2የአሮን ዘር ወደ ሆኑት ካህናት ያምጣው፤ ተረኛው ካህን ከዚያ ዱቄት በእፍኙ ሙሉ በመዝገን ዘይቱንና ዕጣኑን በሙሉ ወስዶ ለእግዚአብሔር የቀረበ መሆኑን ለማሳወቅ በመሠዊያው ላይ በእሳት ያቃጥለው፤ ይህም ዐይነቱ የምግብ መባ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 3ከእህል መባውም የተረፈው ዱቄት የአሮን ዘር ለሆኑት ካህናት ይሰጥ፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ከቀረበው መባ የሚቃጠል ቊርባን በመሆኑ እጅግ የተቀደሰ ነው።
4መባው በምድጃ የተጋገረ ከሆነም እርሾ ያልነካው ይሁን፤ እርሱም የወይራ ዘይት ተደባልቆበት ከላመ ዱቄት የተጋገረ ዳቦ ወይም በዘይት የታሸ ቂጣ መሆን አለበት።
5መባው በምጣድ የተጋገረ ኅብስት ከሆነ እርሾ ሳይነካው የወይራ ዘይት ተጨምሮበት ከላመ ዱቄት የተዘጋጀ ይሁን፤ 6ኅብስቱንም ቈራርሰህ በእርሱ ላይ የወይራ ዘይት ታፈስበትና የእህል መባ አድርገህ ታቀርበዋለህ።
7መባው በመጥበሻ የተጋገረ ቂጣ ከሆነ የወይራ ዘይት ተጨምሮበት ከተለወሰ የላመ ዱቄት የተዘጋጀ ይሁን። 8የእህሉንም መባ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ መሥዋዕት አድርገህ ለካህኑ ታስረክበዋለህ፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል። 9ካህኑም ከዚያ መባ ከፊሉን ወስዶ በሙሉ ለእግዚአብሔር የቀረበ መሆኑን ለማስታወስ በመሠዊያው ላይ በሚገኘው እሳት ያቃጥለዋል፤ ይህም ዐይነት በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 10ቀሪው መባ ግን ለካህናቱ ይሰጥ፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ከቀረበው መባ ተከፍሎ የተወሰደ በመሆኑ እጅግ የተቀደሰ ነው።
11የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው መባ ጋር የሚገኘውን እርሾም ሆነ ማር. በእሳት ማቃጠል ስለሌለብህ፥ ለእግዚአብሔር የምታቀርበው የእህል መባ ሁሉ ምንም ዐይነት እርሾ ያልነካው ይሁን፤ 12በየዓመቱ የመከር መጀመሪያ ከእህላችሁ በኲራት አድርጋችሁ የምታቀርቡትንም መባ ለእግዚአብሔር ታመጣላችሁ፤ እርሱ ግን በመሠዊያው ላይ አይቃጠል። 13ይህ የእህል ቊርባን ስለ ሆነ በእህል ቊርባንህ ሁሉ ላይ ጨው ጨምርበት፤ የአምላክህን የጨው ቃል ኪዳን አትተው፤ በቊርባኖች ሁሉ ጨው መግባት አለበት። 14የመከር ወራት መጀመሪያ የሆነውን በኲራት በምታቀርብበትም ጊዜ ተጠብሶ የታሸ እሸት ይሁን። 15ይህ የእህል መባ ስለ ሆነ በእርሱ ላይ የወይራ ዘይትና ዕጣን ጨምርበት፤ 16ካህኑም ከዚያ መባ ከፊሉን ወስዶ ለእግዚአብሔር የቀረበ መሆኑን ለማስታወስ ዘይቱንም፥ ዕጣኑንም በሙሉ ከእህሉ ጋር አብሮ ያቃጥለዋል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 2: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997