ኦሪት ዘሌዋውያን 1
1
የሚቃጠል መሥዋዕት
1ከመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር ሙሴን ጠራው፤ እንዲህ ብሎም አዘዘው፥ 2እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር መባ በሚያቀርቡበት ጊዜ ሊጠብቁት የሚገባ ሥርዓት ይህ ነው፦
እያንዳንዱ ሰው ከቀንድ ከብትም ሆነ፥ ከበግ ወይም ከፍየል ወገን ማንኛውንም ዐይነት መባ በሚያቀርብበት ጊዜ፥ 3ይኸውም ከቀንድ ከብቱ መካከል አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ቢፈልግ ምንም ነውር የሌለበትን ኰርማ መርጦ ያምጣ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት የሰመረ መሥዋዕት ይሆንለት ዘንድ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ በር በኩል ያቅርበው። 4ሰውየው ለሚቃጠል መሥዋዕት ባቀረበው እንስሳ ራስ ላይ እጆቹን ይጫን፤ እርሱም ለኃጢአቱ ማስተስረያ የሰመረ መሥዋዕት ይሆንለታል። 5ያ ሰው ወይፈኑን በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ትውልዳቸው ከአሮን ወገን የሆነ ካህናት ደሙን ወደ እግዚአብሔር ያቅርቡት፤ በድንኳኑ በር መግቢያ በኩል በሚገኘው መሠዊያ ጐኖች ሁሉ ላይ ይርጩት። #1፥5 በእግዚአብሔር ፊት፦ በመገናኛው ድንኳን ማለት ነው። 6ከዚያ በኋላ ያ ሰው የዚያን እንስሳ ቆዳ ይግፈፍ፤ ብልቱንም በየዐይነቱ ይቈራርጠው፤ 7የካህኑ የአሮን ዘሮች የሆኑትም ካህናት በመሠዊያው ላይ እንጨት ረብርበው እሳት ያቀጣጥሉ፤ 8የእንስሳውንም ሥጋ ብልቶች በየዐይነታቸው ለያይተው ራሱንና ስቡንም ጭምር በመሠዊያው ላይ በተረበረበው እንጨት ላይ ያኑሩት። 9ያም ሰው የእንስሳውን ሆድ ዕቃና የኋላ እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም መሥዋዕቱን በሙሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ ይህም የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። የዚህ ዐይነቱ መሥዋዕት መዓዛ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል።
10ሰውየው ከበግ ወይም ከፍየል መንጋዎቹ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ቢፈልግ ምንም ነውር የሌለበት ተባዕት ይሁን። 11እርሱንም ከመሠዊያው በስተ ሰሜን በኩል በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ የአሮን ዘር የሆኑ ካህናትም ደሙን ወስደው በመሠዊያው ጐኖች ሁሉ ላይ ይርጩት። 12ያም ሰው እንስሳውን በየብልቱ ከቈራረጠው በኋላ ካህኑ ብልቶቹን ሁሉ፥ ራሱንና ስቡን ጭምር በመሠዊያ ላይ ተረብርቦ በሚቃጠለው እንጨት ላይ ያኑር፤ 13ሰውየውም የእንስሳውን የሆድ ዕቃና የኋላ እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም ያን ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ በመሠዊያው ላይ በሙሉ ያቃጥለው፤ ይህም ዐይነት በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል።
14ሰውየው፥ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ የፈለገው መባ ከወፎች ወገን ከሆነም የርግብ ጫጩት ወይም ዋኖስ መሆን ይችላል፤ 15ካህኑም ይህን ወፍ ተቀብሎ ወደ መሠዊያው በማቅረብ አንገቱን ይቈልምመው፤ በመሠዊያውም ላይ በሚገኘው እሳት ያቃጥለው፤ ደሙም በመሠዊያው ጐን ይንጠፍጠፍ። 16ላባውንና የሆድ ዕቃውን ለያይቶ ከመሠዊያው በስተ ምሥራቅ ዐመድ በሚፈስበት ስፍራ ይጣለው። 17ክንፎቹንም ይዞ ሳይከፋፍል አካሉን በመከፋፈል በመሠዊያው ላይ በሚገኘው እሳት ያቃጥለው፤ የዚህ ዐይነቱ መሥዋዕት መዓዛ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997