እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ማናቸውም ሰው ሳያውቅ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ የተቀባውም ሊቀ ካህናት በሕዝቡ ላይ በደል እንዲቈጠርባቸው ኀጢአት ቢሠራ፥ ስለ ሠራው ስለ ኀጢአቱ ከመንጋው ነውር የሌለበትን ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኀጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል። ወይፈኑንም ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፤ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል። ተቀብቶ የተሾመው ካህን ከወይፈኑ ደም በእጁ ወስዶ ወደ ምስክሩ ድንኳን ያመጣዋል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። ካህኑም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ጣፋጭ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የወይፈኑንም ደም ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። ለኀጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር፥ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ወይፈን እንደ ተወሰደው ይወስዳል፤ ካህኑም ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ያቀርበዋል። የወይፈኑን ቍርበት፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ ፈርሱንም፤ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አመድ ወደሚፈስስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስዱታል፤ በዕንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥሉታል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። “የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከማኅበሩ ዐይን ቢሸሸግ፥ እግዚአብሔርም አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፉ፤ ከዚህም በኋላ፥ የሠሩት ኀጢአት ቢታወቃቸውና ንስሓ ቢገቡ ማኅበሩ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ ምስክሩም ድንኳን ፊት ያመጡታል። የማኅበሩም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርዱታል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ ምስክሩ ድንኳን ያመጣል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ባለው በዕጣን መሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቀርበዋል። እንዲህም በወይፈኑ ያደርጋል፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት በታረደው ወይፈን እንደ አደረገ እንዲሁ በዚህ ያደርጋል፤ ካህኑም ኀጢአታቸውን ያስተሰርያል፤ ኀጢአቸውም ይሰረይላቸዋል። ወይፈኑንም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ይወስዱታል፤ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠሉ ያቃጥሉታል፤ የማኅበሩ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና። “መኰንንም ኀጢአትን ቢሠራ፥ ሳያውቅም እግዚአብሔር አምላኩ፦ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ እንዲህም ቢበድል፥ የሠራው ኀጢአት ቢታወቀውና ንስሓ ቢገባ፥ ከፍየሎች ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቍርባኑ ያቀርባል፤ በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኀጢአት መሥዋዕት ነውና። ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ ደሙንም ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። ስቡንም ሁሉ እንደ ደኅንነት መሥዋዕት ስብ፥ በመሠዊያው ላይ ይጨምረዋል። ካህኑም ኀጢአቱን ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል።
ኦሪት ዘሌዋውያን 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 4:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች