የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘሌዋውያን 4:1-26

ዘሌዋውያን 4:1-26 NASV

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፤ “ ‘የተቀባውም ካህን በሕዝቡ ላይ በደል የሚያስከትል ኀጢአት ቢሠራ፣ ስለ ሠራው ኀጢአት እንከን የሌለበት አንድ ወይፈን ለእግዚአብሔር የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫን፤ በእግዚአብሔርም ፊት ይረደው። የተቀባው ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ ከመቅደሱ መጋረጃ ትይዩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። ካህኑ ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለውንና ሽታው ጣፋጭ የሆነ ዕጣን የሚታጠንበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ። የተረፈውን የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። ለኀጢአት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ይኸውም፦ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብና ከሆድ ዕቃው ጋራ የተያያዘውን ሥብ፣ ሁለቱንም ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጕበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋራ ዐብሮ አውጥቶ ያቅርብ፤ ለኅብረት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን እንዳወጣ ሁሉ ሥቡን ያውጣ፤ ካህኑም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለው። ነገር ግን የወይፈኑን ቈዳና ሥጋውን ሁሉ፣ ጭንቅላቱንና እግሮቹን፣ ሆድ ዕቃውንና ፈርሱን፣ የወይፈኑን ብልት ሁሉ ከሰፈር ውጭ ዐመድ ወደሚፈስስበት በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነው ስፍራ ይውሰደው፤ በተቈለለው ዐመድ ላይ ዕንጨት አንድዶ ያቃጥለው። “ ‘መላው የእስራኤል ሕዝብ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አታድርጉ ብሎ እግዚአብሔር ካዘዘውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ ይህ ሕዝብ ጥፋቱ ባይታወቀውም በደለኛ ነው። የሕዝቡ ጉባኤ ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን በመገናኛው ድንኳን ፊት ያቅርብ። የሕዝቡም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ፊት እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫኑ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር ፊት ይታረድ። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ። ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ በመጋረጃው ትይዩ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለውን የመሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። ከወይፈኑም ሥቡን ሁሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ለኀጢአት መሥዋዕት ባቀረበው ወይፈን ላይ እንዳደረገው ሁሉ፣ በዚህኛውም ወይፈን ያድርግ፤ በዚህም መሠረት ካህኑ ስለ ሕዝቡ ያስተሰርያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። ወይፈኑንም ከሰፈር ውጭ ያውጣው፤ የመጀመሪያውን ወይፈን እንዳቃጠለው ሁሉ ይህኛውንም ያቃጥል፤ ይህም ስለ ሕዝቡ የሚቀርብ የኀጢአት መሥዋዕት ነው። “ ‘አንድ የሕዝብ መሪ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አምላኩም እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ እርሱ በደለኛ ነው። ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ እንከን የሌለበትን ተባዕት ፍየል የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበትም ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። ካህኑም ከመሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍስሰው። የኅብረት መሥዋዕቱን እንዳቃጠለ ሁሉ ሥቡንም በሙሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።