የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 4:1-26

ኦሪት ዘሌዋውያን 4:1-26 መቅካእኤ

ጌታም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ማናቸውም ሰው ባለማወቅ ጌታ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ኃጢአት ቢሠራ፥ የተቀባውም ካህን ኃጢአት ሠርቶ በሕዝቡ ላይ በደል ቢያመጣ፥ ስለ ሠራው ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለጌታ ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርባል። ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በጌታ ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናል፥ ወይፈኑንም በጌታ ፊት ያርደዋል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በጌታ ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ትዩዩ ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጫል። ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በጌታ ፊት ባለው መዐዛው ያማረ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የተረፈውንም የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ በታች ያፈስሳል። ለኃጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኩላሊቶች ጋር፥ ለአንድነት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን እንደሚወሰደው ከወሰደ በኋላ፥ ካህኑ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለዋል። የወይፈኑን ቆዳ፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ ፈርሱንም፥ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ አመድ ወደሚፈስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስዳል፥ በእንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥለዋል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። “የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከጉባኤው ፊት ቢሸሸግ፥ ጌታም፦ አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዱን ሠርተው ቢበድሉ፥ የሠሩትም ኃጢአት ሲታወቅ ጉባኤው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ከመንጋው ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ መገናኛውም ድንኳን ፊት ያመጡታል። የጉባኤውም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በጌታ ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑም በጌታ ፊት ይታረዳል። የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣል፤ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በጌታ ፊት በመጋረጃው ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። በመገናኛውም ድንኳን ውስጥ በጌታ ፊት ባለው በመሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ በታች ያፈስሳል። ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። የኃጢአት መሥዋዕት በሆነው ወይፈን ላይ እንዳደረገው እንዲሁ በዚህ ወይፈን ላይ ደግሞ ያደርጋል፤ እርሱም እንዲህ ያደርግበታል፤ ካህኑም ስለ እነርሱ ያስተሰርያል፥ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። ወይፈኑንም ከሰፈሩ ውጭ ይወስዳል፥ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠለ ያቃጥለዋል፤ ይህ የማኅበሩ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። “አንድ ገዢም ኃጢአትን ቢሠራ፥ ጌታም አምላኩ አትሥራ ያለውን ትእዛዝ አንዱን ባለማወቅ ሠርቶ ቢበድል፥ ለእርሱም የሠራው ኃጢአት የታወቀ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቁርባኑ ያቀርባል፤ በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በጌታ ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፤ የተረፈውንም ደም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ በታች ያፈስሳል። ስቡንም ሁሉ እንደ አንድነት መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል። ካህኑም ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።