ዘሌዋውያን 25:1-23
ዘሌዋውያን 25:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ እኔ የምሰጣችሁ ምድር ታርፋለች፤ ለእግዚአብሔርም ሰንበት ታደርጋለች። ስድስት ዓመት እርሻህን ትዘራለህ፤ ስድስት ዓመትም ወይንህን ትቈርጣለህ፤ ፍሬዋንም ትሰበስባለህ። በሰባተኛው ዓመት ግን ሰንበት ነው፤ የምድር ዕረፍት ነው፤ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው፤ እርሻህን አትዝራ፤ ወይንህንም አትቍረጥ። የምድራችሁን ገቦ አትጨደው፤ የተቀደሰውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ዓመት ይሆናል። የምድርም ሰንበት ለአንተ፥ ለወንድ ባሪያህም፥ ለሴት ባሪያህም፥ ለምንደኛም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን። ለእንስሶችህም፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ ምግብ ይሁን። “የዓመታትን ሰባት ሰንበቶች ሰባት ጊዜ ሰባት ለራስህ ትቈጥራለህ፤ እነዚህም ሰባት የዓመታት ሱባዔያት አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ። ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር ከወሩ በዐሥረኛው ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ። አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፤ በምድሪቱም ለሚኖሩት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ። ያ አምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፤ የገቦውንም አትጨዱ፤ የተቀደሰውንም በእርሱ አትልቀሙ። ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ በሜዳ ላይ የበቀለውን ብሉ። “በዚች ኢዮቤልዩ ዓመት ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለሳል። ለባልንጀራህም አንዳች ብትሸጥለት፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ ሰው ባልንጀራውን አያስጨንቀው። ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይከፍልሃል። እንደ ዓመታቱ ብዛት ዋጋውን ያበዛል፤ እንደ ዓመታቱም ማነስ ዋጋውን ያሳንሳል፤ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃል። እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያስጨንቅ፤ ነገር ግን አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ። “ሥርዐቴንም አድርጉ፤ ፍርዴንም ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። እናንተም፦ ‘ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ፥ እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፤ ከከረመውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከከረመው እህል ትበላላችሁ። “ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም በእኔ ፊት እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘለዓለም አትሽጡ።
ዘሌዋውያን 25:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ምድሪቱ ራሷ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ሰንበት ታክብር። ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ ስድስት ዓመት ወይንህን ግረዝ፤ ፍሬውንም ሰብስብ። በሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ታድርግ፤ ይህም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነው። በዕርሻህ ላይ አትዝራ፤ ወይንህንም አትግረዝ። ሳይዘራ የበቀለውን አትጨደው፤ ካልተገረዘው የወይን ተክልህ ፍሬ አትሰብስብ። ምድሪቱ የአንድ ዓመት ዕረፍት ታድርግ። ምድሪቱም በሰንበት ጊዜዋ የምታስገኘው ማንኛውም ፍሬ ለአንተ፣ ለወንድ ባሪያህ፣ ለሴት ባሪያህ፣ ለቅጥር ሠራተኛህና ከአንተ ጋር ለሚኖር መጻተኛ ምግብ ይሁን፤ እንዲሁም ለቤት እንስሶችህና በምድርህ ለሚኖሩ የዱር አራዊት ምድሪቱ የምታበቅለው ሁሉ መኖ ይሁን። “ ‘ሰባት የሰንበት ዓመታት ማለትም ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመታትን ቍጠር፤ ሰባቱ የሰንበት ዓመታትም አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ። ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን፣ መለከት ይነፋ፤ በማስተስረያ ቀንም በምድራችሁ ሁሉ መለከት ንፉ። አምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱ ሁሉ ላሉ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻነት ዐውጁ፤ ይህም ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደ ቤተ ሰቡ ርስት፣ ወደ ወገኑም ይመለስ። የአምሳኛው ዓመት ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ አትዝሩ፤ ሳትዘሩት የበቀለውን አትጨዱ፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬ አትሰብስቡ። ኢዮቤልዩ ስለሆነ ለእናንተ የተቀደሰ ይሁን፤ ሳትዘሩት በሜዳ የበቀለውን ብሉ። “ ‘በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለስ። “ ‘ከወገንህ ከአንዱ መሬት ብትገዛ ወይም ብትሸጥለት፣ አንዱ ሌላውን አያታልል። ከኢዮቤልዩ በኋላ ያሉትን ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ከወገንህ ትገዛለህ፤ እርሱም የቀሩትን የመከር ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ይሸጥልሃል። የዓመቱ ቍጥር ከበዛ ዋጋውን ጨምር፤ የዓመቱ ቍጥር ካነሰም፣ ዋጋውን ቀንስ፤ ምክንያቱም የሚሸጥልህ የዓመቱን የምርት መጠን ነውና። አንዱ ሌላውን አያታልል፤ አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ። “ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤ ሕጌን በጥንቃቄ አድርጉ፤ በምድሪቱም በሰላም ትኖራላችሁ። ምድሪቱ ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በዚያም በሰላም ትኖራላችሁ። እናንተም፣ “ካልዘራን ወይም ሰብላችንን ካልሰበሰብን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?” በማለት ትጠይቁ ይሆናል። በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እሰድድላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ፍሬ ትሰጣለች። በስምንተኛው ዓመት በምትዘሩበት ጊዜ፣ የምትበሉት ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ሰብል ይሆናል፤ የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስክትሰበስቡ ድረስ ከዚሁ እህል ትበላላችሁ። “ ‘መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ።
ዘሌዋውያን 25:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ሰንበት ታድርግ። ስድስት ዓመት እርሻህን ዝራ፥ ስድስት ዓመትም ወይንህን ቍረጥ ፍሬዋንም አግባ። በሰባተኛው ዓመት ግን ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት፥ ለእግዚአብሔር ሰንበት፥ ትሁን፤ እርሻህን አትዝራ፥ ወይንህንም አትቍረጥ። የምድራችሁን የገቦ አትጨደው፥ ያልተቈረጠውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን። የምድርም ሰንበት ለአንተ፥ ለወንድ ባሪያህም፥ ለሴት ባሪያህም፥ ለምንደኛም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን። ለእንስሶችህም፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ መኖ ይሁን። ሰባት ጊዜ ሰባት አድርገህ የዓመታትን ሰንበት ሰባት ቍጠር፤ የሰባት ዓመታትም ሰንበት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ትቈጥራለህ። ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ። አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእንናተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ። ያ አምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ የገቦውንም አትጨዱ፥ የወይኑንም ፍሬ አታከማቹ። ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ በሜዳ ላይ የበቀለውን ብሉ። በዚች በኢዮቤልዩ ዓመት ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለሳል። ለባልንጀራህም አንዳች ብትሸጥለት፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ ሰው ባልንጀራውን አያታልል። ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል። እንደ ዓመታቱ ማነስ ዋጋውን ታሳንሳለህ፤ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃል። እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። ሥርዓቴንም አድርጉ፥ ፍርዶቼንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ። ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ። እናንተም፦ ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን? ብትሉ፥ እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ከአሮጌውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከአሮጌው እህል ትበላላችሁ። ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ጋር እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘላለም አትሽጡ።
ዘሌዋውያን 25:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ በሰባተኛው ዓመት ምንም ሳታርሱ ምድሪቱን በማሳረፍ እግዚአብሔርን ታከብራላችሁ። በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘርህን ትዘራለህ፤ የወይን ተክልህን ትገርዛለህ፤ እህልህን ትሰበስባለህ። ሰባተኛው ዓመት ግን ለእኔ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሆኖ ምድሪቱ ፍጹም ዕረፍት የምታደርግበት ጊዜ ነው። በዚህ ዓመት ዘርህን አትዘራም፤ የወይን ተክልህንም አትገርዝም። ሳይዘራ ገቦ ሆኖ የበቀለውንም እህል አትሰበስብም፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬውን አትሰበስብም፤ ያ ዓመት ምድሪቱ ፍጹም ዕረፍት የምታደርግበት ጊዜ ነው። በምድር ሰንበት ዓመት የሚበቅለው ሰብል ሁሉ ለአንተ፥ ለወንድ አገልጋይህ፥ ለሴት አገልጋይህ፥ ለቅጥረኛህ፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ጊዜያዊ መጻተኛ ምግብ ይሆናል። ለእንስሶችህና በምድርህ ለሚገኙ አራዊት የሚበቃ ምግብ ታገኛለህ፤ ምድሪቱ የምታስገኘው ነገር ሁሉ ሊበላ ይችላል። “ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመት ቊጠር፥ ጠቅላላ ድምሩም አርባ ዘጠኝ ዓመት ይሆናል፤ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን በሚውለው የኃጢአት ስርየት ቀን በመላይቱ ምድር የእምቢልታ ድምፅ የሚያሰማ ሰው ትልካለህ፤ በዚህም ሁኔታ ኀምሳኛውን ዓመት ለይታችሁ በምድሪቱ ለሚኖሩት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ ከዚያ በፊት የተሸጠ ማናቸውም መሬት ለባለቤቱ ወይም ለዘሩ ይመለሳል፤ ባርያም ሆኖ ለማገልገል የተሸጠ ሰው ወደ ቤተሰቡ ይመለሳል። በዚህም ዓመት ዘራችሁን አትዘሩም፤ ሳይዘራ ገቦ ሆኖ የበቀለውን እህላችሁን ወይም ካልተገረዘ የወይን ሐረግ ፍሬውን አትሰበስቡም። ዓመቱ በሙሉ ለእናንተ የተቀደሰ ይሆናል፤ እርሻዎቻችሁ ማንም ሳይንከባከባቸው ራሳቸው የሚያስገኙትን ምግብ ብቻ ትበላላችሁ። “ከዚያ በፊት የተሸጠ መሬት ሁሉ በዚሁ ዓመት ለባለቤቱ ይመለስለታል፤ ስለዚህ ወገንህ ለሆነው እስራኤላዊ መሬት ብትሸጥ ወይም ከእርሱ መሬት ብትገዛ የግፍ ሥራ አትሥራ፤ ዋጋውም የሚተመነው ተከታዩ የንብረት መመለሻ ዓመት ከመግባቱ በፊት፥ ምድሪቱ ልታስገኝ በምትችለው ሰብል መጠን ይሆናል። ዓመታቱ ብዙ ቢሆኑ፥ ዋጋው ከፍ ይላል፤ ዓመታቱ ጥቂቶች ከሆኑ ዋጋው ዝቅ ይላል፤ የሚሸጥበት ዋጋ የሚተመነው ምድሪቱ በምታስገኘው ሰብል መጠን ነው፤ አንዱ እስራኤላዊ በሌላው እስራኤላዊ ላይ ግፍ አይሥራ፤ አምላካችሁን ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “በምድሪቱ ላይ በሰላም ትኖሩ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት ሁሉ አክብሩ፤ ምድሪቱም ራስዋ በቂ ሰብል ስለምታስገኝ የምትበሉትን ሁሉ አግኝታችሁ በምቾትና በሰላም ትኖራላችሁ። “ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ዘር ካልዘራንና ሰብል ካልሰበሰብን ምን እንበላለን ብላችሁ ብትጠይቁ፤ በስድስተኛው ዓመት እኔ ምድሪቱን እባርካታለሁ፤ ስለዚህም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ሰብል ታስገኛለች፤ በስምንተኛው ዓመት እንኳ ዘራችሁን ስትዘሩ የምትመገቡት ቀድሞ የሰበሰባችሁትን መከር ነው፤ ይህንኑ መከር የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስከምትሰበስቡ ድረስ ትበላላችሁ። “ምድሪቱ ለዘለቄታ መሸጥ አይገባትም፤ እርስዋ የእኔ እንጂ የእናንተ አይደለችም፤ እናንተ እንደ መጻተኛ ሆናችሁ እንድትጠቀሙባት ብቻ ፈቅጃለሁ።
ዘሌዋውያን 25:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለጌታ ሰንበት ታድርግ። ስድስት ዓመት እርሻህን ትዘራለህ፥ ስድስት ዓመትም የወይን ተክልህን ግረዝ ፍሬዋንም ሰብስብ። በሰባተኛው ዓመት ግን ለጌታ ሰንበት፥ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ይሁን፤ በእርሻህ ላይ አትዝራ፥ የወይን ተክልህንም አትግረዝ። በመከርህ ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለውን አትሰብስብ፥ ያልተገረዘውን የወይንህን ተክል ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን። የምድሪቱ ሰንበት ለእናንተ፥ ለአንተም፥ ለወንድ ባርያህም፥ ለሴት ባርያህም፥ ተቀጥሮ ለሚያገለግልህም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ትሰጣችኋለች። እንዲሁም ለእንስሶችህ፥ በምድርህም ላሉት አራዊት እርሷ የምትሰጠው ሁሉ ለመኖ ይሆናል። “ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመት አድርገህ በዓመታት ውስጥ ያሉትን ሰንበታት ቁጠር፤ የዓመታቱም የሰንበታት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ይሆኑልሃል። ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የቀንደ መለከትን ድምፅ ከፍ አድርገህ ታሰማለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ የቀንደ መለከትን ድምፅ ታሰማላችሁ። ኀምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእንናተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ ከእናንተም እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለሳል። ያ ኀምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ዓመት ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ እንዲሁም ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለውን አትሰብስቡ፥ ያልተገረዘውን የወይን ተክል ፍሬ አታከማቹ። ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ ምድሪቱ ራስዋ የምትሰጠውን ፍሬ ትበላላችሁ። “በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለሳል። ለባልንጀራህም መሬት ብትሸጥ፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ አንዱ ሌላውን አያታልል። ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል። እርሱ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃልና ዓመታቱ ብዙ በሆኑ ቍጥር ዋጋውን ከፍ ታደርጋለህ፥ ዓመታቱ ግን ባነሱ ቍጥር ዋጋውን ታሳንሳለህ። እኔም ጌታ አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። “ሥርዓቶቼን አድርጉ፥ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርሷም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። ዳሩ ግን እናንተ፦ ‘ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ፥ እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በእናንተ ላይ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ፤ የእርሷ ፍሬ እስከሚገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ። ምድሪቱም የእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድሪቱን ለዘለዓለም አትሽጧት።