ኦሪት ዘሌዋውያን 25
25
ስለ ሰባተኛ ዓመት ዕረፍት
(ዘዳ. 15፥1-11)
1እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ እኔ የምሰጣችሁ ምድር ታርፋለች፤ ለእግዚአብሔርም ሰንበት ታደርጋለች። 3ስድስት ዓመት እርሻህን ትዘራለህ፤ ስድስት ዓመትም ወይንህን ትቈርጣለህ፤ ፍሬዋንም ትሰበስባለህ። 4በሰባተኛው ዓመት ግን ሰንበት ነው፤ የምድር ዕረፍት ነው፤ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው፤ እርሻህን አትዝራ፤ ወይንህንም አትቍረጥ። 5የምድራችሁን ገቦ አትጨደው፤ የተቀደሰውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ዓመት ይሆናል። 6የምድርም ሰንበት ለአንተ፥ ለወንድ ባሪያህም፥ ለሴት ባሪያህም፥ ለምንደኛም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን። 7ለእንስሶችህም፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ ምግብ ይሁን።
ዐመተ ኢዮቤልዩ
8“የዓመታትን ሰባት ሰንበቶች ሰባት ጊዜ ሰባት ለራስህ ትቈጥራለህ፤ እነዚህም ሰባት የዓመታት ሱባዔያት አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ። 9ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር ከወሩ በዐሥረኛው ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ። 10አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፤ በምድሪቱም ለሚኖሩት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ። 11ያ አምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፤ የገቦውንም አትጨዱ፤ የተቀደሰውንም በእርሱ አትልቀሙ። 12ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ በሜዳ ላይ የበቀለውን ብሉ።
13“በዚች ኢዮቤልዩ ዓመት ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለሳል። 14ለባልንጀራህም አንዳች ብትሸጥለት፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ ሰው ባልንጀራውን አያስጨንቀው። 15ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይከፍልሃል። 16እንደ ዓመታቱ ብዛት ዋጋውን ያበዛል፤ እንደ ዓመታቱም ማነስ ዋጋውን ያሳንሳል፤ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃል። 17እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያስጨንቅ፤ ነገር ግን አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ።
18“ሥርዐቴንም አድርጉ፤ ፍርዴንም ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። 19ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። 20እናንተም፦ ‘ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ፥ 21እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። 22በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፤ ከከረመውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከከረመው እህል ትበላላችሁ።
የዕዳ ምሕረት ዐመት
23“ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም በእኔ ፊት እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘለዓለም አትሽጡ። 24በርስታችሁም ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ አድርጉ። 25ወንድምህም ቢደኸይ፥ ከርስቱም ቢሸጥ፥ ለእርሱ የቀረበ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል። 26የሚቤዠውም ሰው ቢያጣ፥ እርሱም እጁ ቢረጥብ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥ 27የሽያጩን ዘመን ቈጥሮ የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ። 28ለራሱም ዕዳውን መክፈል ባይችል፥ ሽያጩ በገዛው ሰው እጅ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቀመጥ፤ በኢዮቤልዩም ዓመት ይውጣ፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ።
29“ሰውም ቅጥር ባለበት ከተማ መኖርያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት መቤዠት ይችላል። 30አንድ ዓመት እስኪጨረስ ባይቤዠው ቤቱ ለገዡ ይሆናል፤ ቅጥር ባለበት ከተማ ያለውን ያን ቤት ይመረምሩለታል፤ ለገዛው ሰው ለልጅ ልጁ ለዘለዓለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩ ዓመትም አይወስዱበትም። 31ቅጥር በሌለበት መንደር ያሉ ቤቶች ግን እንደ እርሻ ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፤ በኢዮቤልዩ ዓመትም ይመለሳሉ። 32የሌዋውያንን ከተሞች፥ በከተሞቻቸውም ያሉ ቤቶቻቸውን ሌዋውያን ለዘለዓለም መቤዠት ይችላሉ። 33ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የሌዋውያን ከተሞች ቤቶች ርስቶቻቸው ናቸውና በርስቱ ከተማ ያለ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ዓመት ይመለሳል። 34በከተማዎቻቸው ዙሪያ ያሉ እርሻዎቻቸውም የዘለዓለም ርስቶቻቸው ናቸውና አይሸጡም።
ለድኃ በወለድ አለማበደር
35“ከአንተ ጋር ያለው ወንድምህ ቢደኸይ፥ እጁም በአንተ ዘንድ ቢደክም እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛ ትረዳዋለህ፤ ከአንተም ጋር ይኑር። 36ወንድምህ ከአንተ ጋር ይኖር ዘንድ ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። 37ብርህን በወለድ አታበድረው፤ እህልህንም በትርፍ አትስጠው። 38የከነዓንን ምድር እሰጥህ ዘንድ፥ አምላክም እሆንህ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና።
ስለ ባሪያ ነጻነት
39“ወንድምህ ቢቸገር፥ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባሪያ አድርገህ አትግዛው። 40እንደ ምንደኛና እንደ ስደተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመትም ያገልግልህ። 41በኢዮቤልዩ ዓመትም እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ይወጣል፤ ወደ ወገኖቹም፥ ወደ አባቱም ርስት ይመለሳል። 42ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎች ናቸውና ባሪያ እንደሚሸጥ አይሸጡ። 43በሥራ አታስጨንቀው፤ ነገር ግን አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ። 44ምን ያህል ወንድ ባሪያና ሴት ባሪያ እንዲኖሩህ ብትፈልግ ግን በዙሪያችሁ ካሉት ከእነርሱ ከአሕዛብ ወንድና ሴት ባያሪያዎችን ግዙ። 45በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት ስደተኞች ልጆች ለራሳችሁ ትገዛላችሁ፤ ከዘመዶቻቸውም በምድራችሁ የሚኖሩት ሁሉ ለርስታችሁ ይሁኑአችሁ። 46ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ ታወርሱአቸዋላችሁ፤ እነርሱም ለእናንተ ለዘለዓለም ውርስ ይሆናሉ፤ ነገር ግን ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤል ልጆች ማናቸውም ሰው ወንድሙን በሥራ አያስጨንቀው።
47“በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው፥ ወይም ለእንግዳው ወይም ለወገኖቹ ዘር ቢሸጥ፥ 48ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤ 49ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ ለእርሱ የቀረበ ዘመድ ይቤዠው፤ ወይም እርሱ እጁ ቢረጥብ ራሱን ይቤዠው። 50ከገዛውም ሰው ጋር ከገዛበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቍጠር፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሁን፤ እንደ ምንደኛውም ዘመን ከእርሱ ጋር ይሁን። 51ብዙ ዓመታትም#ግእዙ “ስምንት ዓመት” ይላል። ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 52እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂት ዓመታት ቢቀሩ እንደ ዓመቱ ይቍጠሩለት፤ እንደ ኣመታቱም መጠን የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 53በየዓመቱ እንደ ምንደኛ ከእርሱ ጋር ይኑር፤ በፊትህ እንደ ቀደመው አያስጨንቀው። 54በዚህ ዘመን ሁሉ ግን ባይቤዥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ይውጣ። 55የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባሪያዎች ናቸውና፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎች ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።#“እኔ እግዚአብሔር አምላክ ነኝ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የምዕ. 26 መጀመሪያ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 25: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ