ኦሪት ዘሌዋውያን 26
26
በመታዘዝ የሚገኝ በረከት
(ዘዳ. 7፥12-24፤ 28፥1-14)
1“ለእናንተ በእጅ የተሠራ ጣዖት አታድርጉ፤ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና። 2ሰንበታቴንም ጠብቁ፤ የቀደስኋቸውንም ፍሩ፤#ዕብ. “መቅደሴንም” ይላል። እኔ እግዚአብሔር ነኝና።
3“በሥርዐቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ፥ ብታደርጉትም፥ 4ዝናሙን በወቅቱ አዘንማለሁ፤ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፤ የሜዳው ዛፎችም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ። 5የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቈረጥ ይደርሳል፤ የወይኑም መቈረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ላይ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። 6በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ የሚያስፈራችሁም የለም፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ።#ዕብ. “ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም” የሚል ይጨምራል። 7ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፤ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። 8ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፤ መቶውም ዐሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 9ወደ እናንተም እመለከታለሁ፤ አባዛችኋለሁ፤ ከፍ ከፍም አደርጋችኋለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። 10ብዙ ጊዜ የተቀመጠውን፥ የከረመውንም እህል ትበላላችሁ፤ አዲሱንም ታስገቡ ዘንድ የከረመውን ታወጣላችሁ። 11ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። 12በመካከላችሁም እመላለሳለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። 13ባሪያዎች ከነበራችሁበት ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ በግልጽም አወጣኋችሁ።
ባለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት
(ዘዳ. 28፥15-68)
14“ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ 15ሥርዐቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ሰውነታችሁ ፍርዴን ብትሰለች፥ 16እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሀትን፥ ክሳትንም፥ ዐይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያጠፋ ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። 17ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፤ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሏችሁም ያሸንፉአችኋል። ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። 18እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኀጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ መቅሠፍትን እጨምራለሁ። 19የትዕቢታችሁን ስድብ አጠፋለሁ፤#ዕብ. “የኀይላችሁን ትዕቢት እሰብራለሁ” ይላል። ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። 20ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፤ የዱር ዛፎችም ፍሬያቸውን አይሰጡም።
21“ከዚያም በኋላ በእንቢተኝነት ብትሄዱብኝ፥ ልትሰሙኝም ባትፈቅዱ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። 22በእናንተ ላይ ክፉዎች የምድርን አራዊት እሰድዳለሁ፤ ይበሉአችኋል፤#ዕብ. “ልጆቻችሁን ይነጥቃሉ” ይላል። እንስሶቻችሁንም ያጠፋሉ፤ እናንተንም ያሳንሳሉ፤ መንገዶቻችሁም በረሃ ይሆናሉ።
23“እስከዚህም ድረስ ባትቀጡ፥ አግድማችሁም ብትሄዱ፥ 24እኔ ደግሞ አግድሜ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እበቀላችኋለሁ። 25የቃል ኪዳኔንም በቀል ይበቀልባችሁ ዘንድ ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተማችሁም ትሸሻላችሁ፤ ቸነፈርንም እሰድድባችኋለሁ። በጠላቶቻችሁም እጅ ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ፤ 26በእህል ረሃብ ባስጨነክኋችሁ ጊዜ ዐሥር ሴቶች እንጀራ በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፤ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም። 27እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ አግድማችሁም ብትሄዱብኝ፥ 28እኔ ደግሞ አግድሜ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ እንደ ኀጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29የወንዶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴቶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ። 30የኮረብታ መስገጃዎቻችሁን አፈርሳለሁ፤ በእጅ የተሠሩ የዕንጨት ምስሎቻችሁንም አጠፋለሁ፤ ሬሳችሁንም በጣዖቶቻችሁ ሬሳዎች ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። 31ከተሞቻችሁንም ባድማ አደርጋለሁ፤ መቅደሶቻችሁንም አፈርሳለሁ፤ የመሥዋዕታችሁንም መዓዛ አላሸትትም። 32ምድሪቱንም የተፈታች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባት ጠላቶቻችሁም ከእርስዋ የተነሣ ይደነቃሉ። 33እናንተንም በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ በሄዳችሁበትም ሁሉ ሰይፍ ታጠፋችኋለች፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፤ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ።
34“በዚያም በተፈታችበት ዘመን ሁሉ እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር ሳላችሁ፥ ምድሪቱ ሰንበት በማድረግዋ ደስ ይላታል፤ በዚያም ጊዜ ምድሪቱ ታርፋለች፤ ስንበትንም በማድረግዋ ደስ ይላታል። 35እናንተ ተቀምጣችሁባት በነበረ ጊዜ በሰንበቶቻችሁ አላረፈችም ነበርና በተፈታችበት ዘመን ሁሉ ታርፋለች። 36በጠላቶቻቸውም ምድሮች ሳሉ ከእናንተ ተለይተው በቀሩት ላይ በልባቸው ድንጋጤን እሰድድባቸዋለሁ፤ በነፋስም የምትንቀሳቀስ የቅጠል ድምፅ ታሸብራቸዋለች፤ ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሸሻሉ ፤ 37ማንም ሳያሳድዳቸው ከሰይፍ እንዲሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ እናንተም በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም። 38በአሕዛብም መካከል ትጠፋላችሁ፤ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። 39ከእናንተም ተለይተው የቀሩት ስለ ኀጢአታቸው ይጠፋሉ፤ በአባቶቻቸውም ኀጢአት ደግሞ በጠላቶቻቸው ምድር ይቀልጣሉ።
40“እንደ ከዱኝ፥ ቸልም እንዳሉኝ፥ በፊቴም አግድመው እንደ ሄዱ፥ ኀጢአታቸውንና፥ የአባቶቻቸውን ኀጢአት ይናዘዛሉ። 41እኔም ደግሞ አግድሜ ከእነርሱ ጋር በቍጣ ሄድሁ፤ በጠላቶቻቸውም ምድር አጠፋቸዋለሁ። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ያፍራል፤ ስለ ኀጢአታቸውም ይናዘዛሉ፤ 42ያን ጊዜ እኔ ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ደግሞም ከይስሐቅ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን፥ ከአብርሃምም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባለሁ። 43ምድርም ከእነርሱ መጥፋት የተነሣ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱም ሳይኖሩ በተፈታችበት ዘመን ዕረፍት ታደርጋለች፤ ፍርዴንም ስለ ናቁ፥ ነፍሳቸውም ሥርዐቴን ስለ ተጸየፈች የኀጢአታቸውን ቅጣት ይሸከማሉ። 44ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝና እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም፤ አልጸየፋቸውምም። 45እኔ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ከግዞት ቤት እንዳወጣኋቸው የቀድሞ ቃል ኪዳናቸውን ስለ እነርሱ አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።”
46እግዚአብሔርም በእርሱና በእስራኤል ልጆች መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ እጅ የሰጣቸው ሥርዐቶችና ፍርዶች፥ ሕግጋትም እነዚህ ናቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 26: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ