ኦሪት ዘሌዋውያን 25
25
ሰባተኛው ዓመት
(ዘዳ. 15፥1-11)
1እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፦ 2“ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ በሰባተኛው ዓመት ምንም ሳታርሱ ምድሪቱን በማሳረፍ እግዚአብሔርን ታከብራላችሁ። 3በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘርህን ትዘራለህ፤ የወይን ተክልህን ትገርዛለህ፤ እህልህን ትሰበስባለህ። 4ሰባተኛው ዓመት ግን ለእኔ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሆኖ ምድሪቱ ፍጹም ዕረፍት የምታደርግበት ጊዜ ነው። በዚህ ዓመት ዘርህን አትዘራም፤ የወይን ተክልህንም አትገርዝም። 5ሳይዘራ ገቦ ሆኖ የበቀለውንም እህል አትሰበስብም፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬውን አትሰበስብም፤ ያ ዓመት ምድሪቱ ፍጹም ዕረፍት የምታደርግበት ጊዜ ነው። 6በምድር ሰንበት ዓመት የሚበቅለው ሰብል ሁሉ ለአንተ፥ ለወንድ አገልጋይህ፥ ለሴት አገልጋይህ፥ ለቅጥረኛህ፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ጊዜያዊ መጻተኛ ምግብ ይሆናል። 7ለእንስሶችህና በምድርህ ለሚገኙ አራዊት የሚበቃ ምግብ ታገኛለህ፤ ምድሪቱ የምታስገኘው ነገር ሁሉ ሊበላ ይችላል። #ዘፀ. 23፥10-11።
የምሕረት ዓመት (ኢዮቤልዩ)
8“ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመት ቊጠር፥ ጠቅላላ ድምሩም አርባ ዘጠኝ ዓመት ይሆናል፤ 9ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን በሚውለው የኃጢአት ስርየት ቀን በመላይቱ ምድር የእምቢልታ ድምፅ የሚያሰማ ሰው ትልካለህ፤ 10በዚህም ሁኔታ ኀምሳኛውን ዓመት ለይታችሁ በምድሪቱ ለሚኖሩት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ ከዚያ በፊት የተሸጠ ማናቸውም መሬት ለባለቤቱ ወይም ለዘሩ ይመለሳል፤ ባርያም ሆኖ ለማገልገል የተሸጠ ሰው ወደ ቤተሰቡ ይመለሳል። 11በዚህም ዓመት ዘራችሁን አትዘሩም፤ ሳይዘራ ገቦ ሆኖ የበቀለውን እህላችሁን ወይም ካልተገረዘ የወይን ሐረግ ፍሬውን አትሰበስቡም። 12ዓመቱ በሙሉ ለእናንተ የተቀደሰ ይሆናል፤ እርሻዎቻችሁ ማንም ሳይንከባከባቸው ራሳቸው የሚያስገኙትን ምግብ ብቻ ትበላላችሁ።
13“ከዚያ በፊት የተሸጠ መሬት ሁሉ በዚሁ ዓመት ለባለቤቱ ይመለስለታል፤ 14ስለዚህ ወገንህ ለሆነው እስራኤላዊ መሬት ብትሸጥ ወይም ከእርሱ መሬት ብትገዛ የግፍ ሥራ አትሥራ፤ 15ዋጋውም የሚተመነው ተከታዩ የንብረት መመለሻ ዓመት ከመግባቱ በፊት፥ ምድሪቱ ልታስገኝ በምትችለው ሰብል መጠን ይሆናል። 16ዓመታቱ ብዙ ቢሆኑ፥ ዋጋው ከፍ ይላል፤ ዓመታቱ ጥቂቶች ከሆኑ ዋጋው ዝቅ ይላል፤ የሚሸጥበት ዋጋ የሚተመነው ምድሪቱ በምታስገኘው ሰብል መጠን ነው፤ 17አንዱ እስራኤላዊ በሌላው እስራኤላዊ ላይ ግፍ አይሥራ፤ አምላካችሁን ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
በሰባተኛው ዓመት ስለሚያጋጥም ችግር
18“በምድሪቱ ላይ በሰላም ትኖሩ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት ሁሉ አክብሩ፤ 19ምድሪቱም ራስዋ በቂ ሰብል ስለምታስገኝ የምትበሉትን ሁሉ አግኝታችሁ በምቾትና በሰላም ትኖራላችሁ።
20“ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ዘር ካልዘራንና ሰብል ካልሰበሰብን ምን እንበላለን ብላችሁ ብትጠይቁ፤ 21በስድስተኛው ዓመት እኔ ምድሪቱን እባርካታለሁ፤ ስለዚህም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ሰብል ታስገኛለች፤ 22በስምንተኛው ዓመት እንኳ ዘራችሁን ስትዘሩ የምትመገቡት ቀድሞ የሰበሰባችሁትን መከር ነው፤ ይህንኑ መከር የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስከምትሰበስቡ ድረስ ትበላላችሁ።
የንብረት መመለስ
23“ምድሪቱ ለዘለቄታ መሸጥ አይገባትም፤ እርስዋ የእኔ እንጂ የእናንተ አይደለችም፤ እናንተ እንደ መጻተኛ ሆናችሁ እንድትጠቀሙባት ብቻ ፈቅጃለሁ።
24“መሬት በሚሸጥበት ጊዜ የቀድሞ ባለቤቱ መልሶ ለመዋጀት መብት ያለው መሆኑ መታወቅ አለበት። 25አንድ እስራኤላዊ ድኻ ሆኖ መሬቱን ለመሸጥ ቢገደድ የቅርብ ዘመዱ የሆነ ሰው ሊዋጅለት ይገባዋል። 26ሊዋጅለት የሚችል የቅርብ ዘመድ ባይኖረው ግን ዘግየት ብሎ ሀብት በሚያገኝበት ጊዜ እርሱ ራሱ መዋጀት ይችላል። 27ይህንንም ማድረግ በሚችልበት ጊዜ እስከ ተከታዩ የንብረት መመለስ ዓመት ያለውን ዘመን ቈጥሮ ቀሪውን ገንዘብ ለገዛው ሰው ከመለሰለት በኋላ ወደ ርስቱ ይመለስ። 28ነገር ግን ለመዋጀት የሚያስችል በቂ ገንዘብ ባይኖረው ርስቱ እስከ ተከታዩ የኢዩቤልዩ ዓመት ድረስ በዚያው በገዛው ሰው እጅ ሊቆይለት ይችላል። በዚያም ዓመት ርስቱ ለባለቤቱ ይመለሳል።
29“አንድ ሰው ቅጽር በተሠራላት ከተማ ውስጥ ቤት ቢሸጥ ከተሸጠበት ዕለት ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ መልሶ የመዋጀት መብት አለው። 30ነገር ግን በዓመቱ ውስጥ መልሶ መዋጀት ባይችል፥ መልሶ የመዋጀት መብቱን ያጣል፤ ቤቱም ለገዛው ሰው ወይም ለዘሮቹ ቀዋሚ ንብረት ሆኖ ይቀራል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት እንኳ ለሻጩ አይመለስለትም። 31ቅጽር ባልተሠራላቸው መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን መሸጥ የሚችሉት ግን የእርሻ መሬቶች በሚሸጡበት ዐይነት ይሆናል፤ ባለ ንብረቱ እንደገና የመዋጀት መብት አለው፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ንብረቱን መመለስ አለበት። 32ይሁን እንጂ ሌዋውያን ለእነርሱ በተመደቡላቸው ከተሞች የሚገኘውን ንብረት በማንኛውም ጊዜ መልሶ የመዋጀት መብት ይኖራቸዋል። 33ሌዋውያን በገዛ ከተሞቻቸው የሚሠሩአቸው ቤቶች በእስራኤላውያን መካከል የእነርሱ ቀዋሚ ንብረቶች ናቸው። በእነዚህ ከተሞች ውስጥ አንድ ሌዋዊ ቤት ቢሸጥና መልሶ ለመዋጀት ባይችል በኢዮቤልዩ ዓመት ይመለስለታል፤ 34ነገር ግን በሌዋውያን ከተሞች ዙሪያ የሚገኝ የግጦሽ ሣር መሬት ፈጽሞ አይሸጥም፤ እርሱ ለዘለዓለም ቀዋሚ ንብረታቸው ነው።
ለድኻ ብድር ስለ መስጠት
35“በአቅራቢያህ የሚኖር እስራኤላዊ ወገንህ ደኽይቶ ራሱን መርዳት የማይችል ቢሆን በአጠገብህ መኖር ይችል ዘንድ ላስጠጋኸው መጻተኛ በምታደርገው ዐይነት የሚያስፈልገውን ሁሉ በፈቃድህ አድርግለት። #ዘዳ. 15፥7-8። 36ወለድ እንዲከፍል አታድርገው፤ እግዚአብሔርን በመፍራት እስራኤላዊ ወገንህ በአጠገብህ እንዲኖር ፍቀድለት። 37በምታበድረውም ገንዘብ ወለድ አትጠይቀው፤ በምትሸጥለትም ምግብ ትርፍ አትጠይቀው። #ዘፀ. 22፥25፤ ዘዳ. 23፥19-20። 38የከነዓንን ምድር እንድሰጣችሁና አምላካችሁ እንድሆን ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ።
የባሪያዎች ነጻ መለቀቅ
39“በአጠገብህ የሚኖር እስራኤላዊ ወገንህ ድኻ ከመሆኑ የተነሣ እንደ ባሪያ ሆኖ ሊያገለግልህ ራሱን ቢሸጥ፥ ባሪያ የሚሠራውን ሁሉ እንዲሠራ አታድርገው። 40እስከ ተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ተቀጣሪ አገልጋይ እያገለገለህ እንደ መጻተኛ ይኑር፤ 41በዚያን ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ተለይቶ ወደ ወገኖቹና ወደ አባቶቹ ንብረት ይመለሳል። 42እስራኤላውያን የእኔ አገልጋዮች ናቸው፤ እኔ ከግብጽ ምድር ነጻ አውጥቼአቸዋለሁ፤ ስለዚህም ባርያ ሆነው መሸጥ የለባቸውም። 43እነርሱን በማስጨነቅ አትግዛቸው፤ ነገር ግን እኔን አምላክህን ፍራ። 44በአካባቢህ ከሚገኙት አሕዛብ መካከል እንዲኖሩህ የምትፈልጋቸውን ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችህ የሚሆኑትን ልትገዛ ትችላለህ። 45እንዲሁም በመካከላችሁ የሚኖሩትን የመጻተኞችን ልጆች መግዛት ትችላላችሁ፤ በምድራችሁ የተወለዱትም እንደነዚህ ያሉት ልጆች የራሳችሁ ንብረት መሆን ይችላሉ። 46እነርሱንም በውርስ ለልጆቻችሁ ማስተላለፍ ትችላላችሁ፤ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ አገልጋዮቻችሁ ይሆናሉ፤ ከእስራኤላውያን ወገኖቻችሁ መካከል ግን ማንንም በማስጨነቅ አትግዙ። #ዘፀ. 21፥2-6፤ ዘዳ. 15፥12-18።
47“ምናልባት በመካከልህ የሚኖር አንድ መጻተኛ ባለጸጋ ሲሆን፥ እስራኤላዊ ወገንህ ደኽይቶ ለዚያ መጻተኛ ወይም ከእርሱ ቤተሰብ ለአንዱ ራሱን በባርነት ያስገዛ ይሆናል። 48ከተሸጠም በኋላ እንደገና ተዋጅቶ የመመለስ መብት አለው፤ ስለዚህም ከወንድሞቹ አንዱ ሊዋጀው ይችላል፤ 49አጐቱ፥ የአጐቱ ልጅ ወይም ከቅርብ ዘመዶቹ አንዱ መልሶ ሊዋጀው ይችላል፤ በቂ ገንዘብ ካጠራቀመም የራሱን ነጻነት ራሱ መዋጀት ይችላል። 50ይህም በሚሆንበት ጊዜ ከገዛው ሰው ጋር ይመካከር፤ ዘመኑንም እርሱ ራሱን ከሸጠበት ዓመት ጀምሮ እስከ ተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቊጠሩት፤ ስለ እርሱም ነጻ መለቀቅ ተገቢውን ዋጋ በእነዚያ ዓመቶች ውስጥ ተቀጥሮ በሚሠራ ሰው ልክ ይተምኑት። 51ብዙ ዓመቶች ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቊጥር ከሽያጩ ዋጋ ይመልስ፥ 52እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመቶች ቢቀሩ ከእርሱ ጋር ይቈጥራል፤ እንደ ዓመቶቹም መጠን የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 53ይህም መሆን ያለበት በዓመት ክፍያ እንደ ተቀጠረ ሰው ታስቦ ነው፤ ጌታው እርሱን በማስጨነቅ መግዛት የለበትም። 54በዚህ ዐይነት ነጻ ለመውጣት ባይችል፥ በተከታዩ የኢዮቤልዩ ዓመት እርሱና ልጆቹ ነጻ ይለቀቁ። 55እስራኤላውያን የእኔ አገልጋዮች ስለ ሆኑ እስራኤላዊ የሆነ ማንም ሰው ለዘለቄታው ባርያ ሆኖ መገዛት የለበትም፤ እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ናቸው፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 25: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997