የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 26

26
በመታዘዝ የሚገኝ በረከት
(ዘዳ. 7፥12-2428፥1-14)
1እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ትሰግዱላቸው ዘንድ ማናቸውንም ዐይነት ጣዖቶች አትሥሩ፤ እንዲሁም ምስል ወይም ሐውልት ወይም የተቀረጸ የድንጋይ ዐምድ አታቁሙ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ #ዘፀ. 20፥4፤ ዘሌ. 19፥4፤ ዘዳ. 5፥8፤ 16፥21-22፤ 27፥1። 2ሰንበቶቼን ጠብቁ፤ መቅደሴን አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
3“በሕጌ ብትመሩና ትእዛዞቼንም ብትጠብቁ፥ 4ምድራችሁ በሰብል፥ ዛፎቻችሁም በፍሬ የተሞሉ ይሆኑ ዘንድ ዝናብን በወቅቱ እልክላችኋለሁ። 5ሰብላችሁም እጅግ የበዛ ከመሆኑ የተነሣ ገና መከር መሰብሰብ ሳትጨርሱ፥ የወይን ዘለላ የምትቈርጡበት ጊዜ ይደርሳል፤ የወይን ዘለላም ቈርጣችሁ ሳትጨርሱ እህል የምትዘሩበት ወቅት ይደርሳል፤ ለምግብ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ታገኛላችሁ፤ በምድራችሁም በሰላም ትኖራላችሁ። #ዘዳ. 11፥13-15፤ 28፥1-14።
6“በምድራችሁ ሰላምን እሰጣችኋለሁ፤ ማንንም ሳትፈሩ ያለ ስጋት ትተኛላችሁ፤ አደገኞች የሆኑ አራዊትን ከምድራችሁ አስወግዳለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ጦርነት በዚያ አይኖርም። 7ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ በፊታችሁም በጦርነት ያልቃሉ፤ 8ከእናንተ አምስቱ መቶውን ጠላት ያሸንፋሉ፤ አንድ መቶው ደግሞ ዐሥሩን ሺህ ድል ይነሣሉ፤ ጠላቶቻችሁም በጦርነት ያልቃሉ። 9ፊቴን በምሕረት ወደ እናንተ እመልሳለሁ፤ ዘራችሁን አበዛለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። 10ገና ያለፈውን ሰብል በመብላት ላይ እያላችሁ፥ ለአዲሱ ሰብል ቦታ ማስለቀቅ ይኖርባችኋል። 11እኔም መኖሪያዬን በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ አልጸየፋችሁም። 12እኔ ከእናንተ ጋር እሄዳለሁ፤ አምላካችሁ እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ። #2ቆሮ. 6፥16። 13በባርነት እንዳትገዙ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ተጭኖአችሁ የነበረውን የባርነት ቀንበር ሰብሬ፥ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአለሁ።”
አለመታዘዝ የሚያስከትለው ቅጣት
(ዘዳ. 28፥15-68)
14እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ነገር ግን እኔን ባትሰሙና እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ባትፈጽሙ፥ 15ትእዛዞቼን ባትጠብቁ፥ ሕግጋቴን ብትንቁ፥ ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱና ሥርዓቶቼን ብትጸየፉ፥ 16የሚከተለውን አመጣባችኋለሁ፦ ታላቅ ድንጋጤን፥ ክሳትን፥ ዐይንን የሚያፈዝና ሰውነትን የሚያመነምን የንዳድ በሽታ አመጣባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁ የሚበሉት ስለ ሆነ ዘራችሁን በከንቱ ትዘራላችሁ። 17ፊቴን በቊጣ እመልስባችኋለሁ፤ በጠላቶቻችሁም ትሸነፋላችሁ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ።
18“ይህም ሁሉ ከደረሰባችሁ በኋላ እንኳ የማትታዘዙኝ ከሆናችሁ፥ በእናንተ ላይ የማመጣውን ቅጣት ሰባት ጊዜ እጥፍ እንዲበዛ አደርገዋለሁ። 19እልኸኛ ትዕቢታችሁን አዋርዳለሁ፤ ሰማይን እንደ ብረት አጠንክሬ ዝናብ እንዳይዘንብ አደርጋለሁ፤ ምድርንም በድርቅ መትቼ እንደ ነሐስ የጠጠረች አደርጋለሁ። 20ምድራችሁ ሰብልን ዛፎቻችሁም ፍሬን ስለማይሰጡ በከንቱ ትደክማላችሁ።
21“እኔን በመቃወም ከቀጠላችሁና እኔን የማትሰሙኝ ከሆነ፥ እንደ ኃጢአታችሁ ብዛት ሰባት ጊዜ እጥፍ የሆነ መቅሠፍት አመጣባችኋለሁ። 22በመካከላችሁ አደገኞች አራዊትን እልካለሁ፤ እነርሱም ልጆቻችሁን ይገድላሉ፤ ከብቶቻችሁንም ያወድማሉ፤ ከእናንተ ጥቂት ሰዎች ብቻ ስለሚቀሩ ጐዳናዎቻችሁ ሁሉ ሰው አልባ ይሆናሉ።
23“ይህ ሁሉ ቅጣት ከተፈጸመባችሁ በኋላ ባትሰሙኝና እኔን በመቃወም ብትጸኑ፥ 24በእናንተ ላይ በቊጣ ተመልሼ ካለፈው ሰባት እጥፍ በበረታ ሁኔታ እቀጣችኋለሁ። 25ከእኔ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን በማፍረሳችሁ እናንተን ለመቅጣት ጦርነት አመጣባችኋለሁ፤ በከተሞቻችሁ ብትሰበሰቡም ሊፈወስ የማይችል በሽታ በመካከላችሁ እልካለሁ፤ ለጠላቶቻችሁም እጃችሁን ለመስጠት ትገደዳላችሁ። 26ምግብ እንድታጡ በማደርግበት ጊዜ እንጀራችሁን ዐሥር ሴቶች በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፤ ምግባችሁንም መጥነው ያቀርቡላችኋል፤ እናንተም በልታችሁ አትጠግቡም።
27“ይህም ሁሉ ተፈጽሞባችሁ እኔን መቃወም ብትቀጥሉና ለእኔም ባትታዘዙ፥ 28በእናንተ ላይ በቊጣ እነሣለሁ፤ በእናንተ ላይ የማመጣውንም ቅጣት ካለፈው ሰባት ጊዜ የበለጠ እንዲሆን አደርጋለሁ። 29ስለዚህም ከመራባችሁ ጽናት የተነሣ የገዛ ልጆቻችሁን ለመብላት ትገደዳላችሁ። 30በየኰረብታው ላይ ያሉአችሁን መስገጃዎች እደመስሳለሁ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁንም አፈራርሳለሁ፤ ሬሳዎቻችሁንም በወደቁት ጣዖቶቻችሁ ላይ እጥላለሁ፤ ፈጽሞ እጸየፋችኋለሁ፤ 31ከተሞቻችሁንም ውድማ አደርጋለሁ የማምለኪያ ስፍራዎቻችሁንም አፈራርሳለሁ መሥዋዕታችሁንም አልቀበልም። 32ምድራችሁን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ በወረራ የያዛትም ጠላት ጥፋትዋን አይቶ በፍርሃት ይንቀጠቀጣል። 33በእናንተም ላይ ጦርነት አምጥቼ በባዕዳን አገሮች ሁሉ እበትናችኋለሁ፤ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁ ሰው አልባ፥ ከተሞቻችሁም ውድማ ይሆናሉ፤ 34እናንተ በጠላቶቻችሁ አገር በምትኖሩባቸው ዓመቶች ሁሉ ምድራችሁ ባዶ ስለምትሆን ሰንበቶችን ታከብራለች፤ ከዚያ በኋላ ምድሪቱ ዕረፍት አድርጋ በሰንበቶች ትደሰታለች። 35እናንተ በነበራችሁባት ጊዜ በሰንበቶቻችሁ ያላገኘችውን ዕረፍት አሁን ሰው አልባ በሆነችበት ጊዜ ዐረፈች።
36“ከስደት የቀሩት ሁሉ ነፋስ የሚነካውን የቅጠል ኮሽታ በሰሙ ቊጥር በድንጋጤ በርግገው እንዲሸሹ አደርጋለሁ፤ በጦርነት ላይ ልክ ጠላት እንደሚያሳድዳቸው ያኽል ሆነው ይሸሻሉ፤ ምንም ዐይነት ጠላት በአጠገባቸው ሳይኖር ተደናቅፈው ይወድቃሉ፤ 37ማንም ሳያሳድዳቸው ከጠላት እንደሚሸሹ ሆነው አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ተሰነካክለው ይወድቃሉ፤ ማንኛውንም ጠላት ተቋቊማችሁ ለመዋጋት አትችሉም። 38በአሕዛብ መካከል ትጠፋላችሁ፤ በጠላቶቻችሁም ምድር ተውጣችሁ ትቀራላችሁ። 39በጠላቶቻችሁ ምድር ከሞት ተርፋችሁ የምትቀሩት ጥቂቶቻችሁ፥ በራሳችሁና በቀድሞ አባቶቻችሁ ኃጢአት ምክንያት መንምናችሁ ትቀራላችሁ።
40“ነገር ግን የእናንተ ዘሮች የራሳቸውን ኃጢአት፥ እንዲሁም በእኔ ላይ ያመፁትንና የተቃወሙኝን የቀድሞ አባቶቻቸውን ኃጢአት ይናዘዛሉ፤ 41እነርሱን ተቃውሜ ወደ ጠላቶቻቸው አገር እንዲሰደዱ አደረግሁ፤ ሆኖም እልኸኛ ልባቸው በትሕትና ተሰብሮ ከኃጢአታቸው ቢታረሙ፥ 42ከያዕቆብ፥ ከይስሐቅና ከአብርሃም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም ለሕዝቤ ለመስጠት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል አድሳለሁ። #ዘፍ. 17፥7-8፤ 26፥3-4፤ 28፥13-14። 43ከሕዝብዋ ባዶ የሆነችው ምድር ውድማ ሆና ሰንበቶችን ታከብራለች፤ እነርሱም ሥርዓቴን ስላልተቀበሉና ሕጌን ስላላከበሩ፥ በኃጢአታቸው ምክንያት ቅጣቱን በሙሉ ይቀበላሉ። 44ይሁን እንጂ በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ እንኳ እስከ መጨረሻ አልተዋቸውም ወይም አልደመስሳቸውም፤ ይህማ ቢሆን ኖሮ ከእነርሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን እስከ መጨረሻ ባልጠበቅሁም ነበር፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ። 45ነገር ግን አምላካቸው እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው ከአባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ስለ እነርሱ አስታውሳለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
46እግዚአብሔር በእርሱና በእስራኤል ሕዝብ መካከል በሙሴ አማካይነት በሲና ተራራ ላይ የሰጣቸው ደንቦች፥ ሥርዓቶችና ሕጎች እነዚህ ናቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ