ኦሪት ዘሌዋውያን 24
24
ስለ መብራቶች የሚደረግ ጥንቃቄ
(ዘፀ. 27፥20-21)
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2“በድንኳኑ ውስጥ ያለው መብራት ዘወትር ሲበራ እንዲኖር ለማድረግ ተጨምቆ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ እስራኤላውያንን እዘዝ። 3አሮን በየምሽቱ መብራቱን ያቀጣጥላል፤ እርሱም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ባለው በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ካለው መጋረጃ ውጪ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ንጋት ድረስ ሲበራ ያድራል፤ ይህም ድንጋጌ በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ተጠብቆ ይኖራል። 4አሮን መብራቶቹን በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟቋረጥ የሚበሩ መሆናቸውንም ይቈጣጠራል።
ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የተቀደሰ ኅብስት
5“ዐሥራ ሁለት ኪሎ የላመ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ 6ኅብስቱን በእግዚአብሔር ፊት ባለው በንጹሕ ወርቅ በተለበጠው ገበታ ላይ ስድስቱን በአንድ በኩል፥ ስድስቱን በሌላ በኩል በሁለት ረድፍ ደርድረህ አኑር። #ዘፀ. 25፥30። 7በእሳት የሚቃጠል ለእግዚአብሔር የቀረበ የተቀደሰ ኅብስት ለመሆኑ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ንጹሕ የሆነ ዕጣን በሁለቱም ረድፍ ላይ አኑር። 8አሮን ስለ እስራኤል ሕዝብ ሆኖ ኅብስቱን በየሰንበቱ ለሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ያኖረዋል። 9ይህም የእስራኤል ሕዝብ ዘወትር ሊፈጽሙት የሚገባ የቃል ኪዳን ሥርዓት ነው። ኅብስቱ የአሮንና የልጅ ልጆቹ ድርሻ ይሆናል፤ እነርሱም በተቀደሰ ቦታ ይብሉት፤ እርሱ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል ቅዱስ መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበ በኋላ ለካህናቱ የተለየ ቋሚ ድርሻ ይሆናል።” #ማቴ. 12፥4፤ ማር. 2፥26፤ ሉቃ. 6፥4።
በደልና ቅጣት
10እናቱ እስራኤላዊት፥ አባቱ ግብጻዊ የሆነ አንድ ሰው በእስራኤላውያን መካከል ወጥቶ ከአንድ እስራኤላዊ ጋር ተጣላ፤ 11የእስራኤላዊቱ ልጅ የእግዚአብሔርን ስም ስለ ተሳደበ ወደ ሙሴ አቀረቡት፤ የእናቱም ስም ሰሎሚት የምትባልና ከዳን ነገድ የሆነው የዲብሪ ልጅ ነበረች። 12የእግዚአብሔር ፈቃድ እስኪገለጥላቸው ድረስ በቊጥጥር ሥር አዋሉት። 13እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 14“ያን ሰው ከሰፈር አውጣ፤ ሲሳደብ የሰማው ሰው ሁሉ ያ ሰው በደል የሠራ መሆኑን ለመመስከር እያንዳንዱ እጁን በዚያ ሰው ራስ ላይ ይጫን፤ ከዚያም በኋላ መላው የእስራኤል ሕዝብ በድንጋይ ወግሮ ይግደለው፤ 15እኔን እግዚአብሔርን የሚሰድብ ማንም ሰው ቅጣቱን ይቀበላል፤ 16የእግዚአብሔርን ስም የሚሰድብ ይገደል፤ ማኅበረሰቡ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት፤ እስራኤላዊም ሆነ መጻተኛ የእግዚአብሔርን ስም ሲሰድብ ይገደል።
17“ሰውን የሚገድል ማንም ሰው በሞት ይቀጣ፤ #ዘፀ. 21፥12። 18የሌላን ሰው እንስሳ የገደለ ምትኩን ይክፈል፤ ይህም ዐይነቱ ሥርዓት በሕይወት ምትክ ሕይወት መሆኑ ነው።
19“ማንም ሰው በሌላ ሰው ላይ ጒዳት ቢያደርስ የዚያኑ ዐይነት ጒዳት ይድረስበት፤ 20የሌላውን ሰው አጥንት ቢሰብር አጥንቱ ይሰበር፤ የሌላውን ሰው ዐይን ቢያወጣ ዐይኑ ይውጣ፤ ጥርስም ቢሰብር ጥርሱ ይሰበር። በሌላ ሰው ላይ ምንም ዐይነት ጒዳት ቢያደርስ የዚያው ዐይነት ጒዳት በእርሱ ላይ ይመለስበት። #ዘፀ. 21፥23-25፤ ዘዳ. 19፥21፤ ማቴ. 5፥38። 21እንስሳ የሚገድል ምትኩን ይክፈል፤ ሰውን የሚገድል ግን በሞት ይቀጣ። 22ይህም ሕግ ለሁላችሁም ማለትም ለእናንተ ለእስራኤላውያንም ሆነ፥ በእናንተ መካከል ለሚኖሩት መጻተኞች ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” #ዘኍ. 15፥16።
23ሙሴም ይህን ሁሉ ለሕዝቡ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ ያን ሰው ከሰፈር አወጡና በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ በዚህም ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 24: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997