ኦሪት ዘሌዋውያን 23
23
የበዓላት አከባበር
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2“ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የተቀደሱ ብላችሁ የምታውጁአቸው የእኔ የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው፤ 3ሥራ የምትሠሩባቸው ስድስት ቀኖች አሉላችሁ፤ ሰባተኛው ዕለተ ሰንበት ግን የዕረፍት ቀን ነው፤ በዚያን ቀን ለአምልኮ ተሰብሰቡ እንጂ ምንም ሥራ አትሥሩበት፤ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ሰንበት ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ዕለት ነው፤ #ዘፀ. 20፥8-10፤ 23፥12፤ 31፥15፤ 34፥21፤ 35፥2፤ ዘዳ. 5፥12-14። 4ለእያንዳንዳቸው በተወሰነላቸው ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት እየተሰበሰባችሁ የምታከብሩአቸው ዋና ዋናዎቹ በዓላት እነዚህ ናቸው።
የፋሲካና የቂጣ በዓል
(ዘኍ. 28፥16-25)
5“እግዚአብሔር የሚከበርበት የፋሲካ በዓል የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ጀንበር ጠልቃ መሸትሸት ሲል ይጀመራል፤ #ዘፀ. 12፥1-13፤ ዘዳ. 16፥1-2። 6በዐሥራ አምስተኛው ቀን የቂጣ በዓል ይጀመራል፤ ከዚያን በኋላ እስከ ሰባት ቀን ድረስ እርሾ ያልነካው ቂጣ ትመገባላችሁ። 7ከእነዚህ ዕለቶች በመጀመሪያው ቀን ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ፤ ከዕለት ተግባራችሁ ማንኛውንም በዚህ ቀን አትሠሩም። 8እስከ ሰባት ቀን ድረስ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የዕለት ተግባራችሁን ማከናወን ትታችሁ በሰባተኛው ቀን ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ።” #ዘፀ. 12፥14-20፤ 23፥15፤ 34፥18፤ ዘዳ. 16፥3-8። 9እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 10“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ እግዚአብሔር ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከር በምታጭዱበት ጊዜ የመጀመሪያውን ነዶ ለካህኑ ስጡ፤ 11እግዚአብሔር ይቀበላችሁ ዘንድ ካህኑ ነዶውን በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርባል። ካህኑም እርሱን ማቅረብ ያለበት ከሰንበት ቀጥሎ በሚውለው ቀን ነው። 12የእህል መባችሁን በምታቀርቡበት በዚያኑ ቀን ነውር የሌለበትና አንድ ዓመት የሆነውን የበግ ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አብራችሁ አቅርቡ። 13ከእርሱም ጋር በወይራ ዘይት የተለወሰ ሁለት ኪሎ የላመ ዱቄት የምግብ መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል፤ ከዚህም ጋር አንድ ሊትር የሚሆን የወይን ጠጅ ስጦታ ታቀርባላችሁ። 14ይህንንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ከማቅረባችሁ በፊት ከአዲሱ እህል ጥሬውን ወይም የተቈላውን ወይም እንጀራ ጋግራችሁ አትብሉ። ይህም ድንጋጌ በሚመጡት ዘመናት ሁሉ በልጅ ልጆቻችሁ ተጠብቆ ይኑር።
የመከር በዓል
(ዘኍ. 28፥26-31)
15“ነዶአችሁን ለእግዚአብሔር በመወዝወዝ የሚቀርብ ልዩ መባ አድርጋችሁ ካመጣችሁበት ሰንበት ማግስት ጀምሮ ሰባት ሳምንት ቊጠሩ፤ 16ከሰባተኛው ሰንበት በኋላ በኀምሳኛው ቀን እንደገና የአዲስ እህል ቊርባን ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ 17እያንዳንዱ ቤተሰብ ሁለት እንጀራ በመወዝወዝ ልዩ መባ አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ እያንዳንዱ እንጀራ እርሾ ገብቶበት ከሁለት ኪሎ የላመ ዱቄት ጋር ተጋግሮ ስለሚሰበሰበው አዲስ መከር ለእግዚአብሔር የበኲራት መባ ሆኖ ይቅረብ። 18ከእንጀራውም ጋር ማኅበሩ ምንም ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰባት የበግ ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ያምጡ፤ እነርሱም ከእህሉ ቊርባንና ከወይን ጠጁ መባ ጋር የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት ሆነው ይቀርባሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርበው መሥዋዕት ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። #ዘፀ. 23፥16፤ 34፥22፤ ዘዳ. 16፥9-12። 19ከዚያም ቀጥሎ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አንድ ተባዕት ፍየል፤ ለአንድነት መሥዋዕት የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ 20ካህኑም ከበኲራቱ እንጀራ ከሁለቱ ጠቦቶች ጋር በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርባል፤ እርሱም የካህናቱ ድርሻ ሆኖ ይነሣል፤ እነዚህም ስጦታዎች የተቀደሱ ናቸው። 21በዚያም ቀን የአምልኮ ስብሰባ እንዲሆንላችሁ ታውጃላችሁ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ ይህ በምትኖሩበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው።
22“የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር አትጨዱ፤ የመከሩንም ቃርሚያ ለመሰብሰብ ወደ ኋላ አትመለሱ፤ እርሱን ለድኾችና ለመጻተኞች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” #ዘሌ. 19፥9-10፤ ዘዳ. 24፥19-22።
የመለከት በዓል
(ዘኍ. 29፥1-6)
23እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 24“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ በሰባተኛው ወር፥ ወሩ በገባ በመጀመሪያው ቀን እግዚአብሔርን ለማምለክ በመለከት የታወጀ መታሰቢያ የዕረፍት ቀን ይሁንላችሁ። 25በዚያን ዕለት ለእግዚአብሔር የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡበት እንጂ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አትሥሩበት።”
የኃጢአት ስርየት ቀን
(ዘኍ. 29፥7-11)
26እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 27“በዚህ በሰባተኛው ወር ዐሥረኛው ቀን የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረያ ሥርዓት የሚፈጸምበት ቀን ነው፤ በዚያን ዕለት እግዚአብሔርን ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ ለንስሓም ሰውነታችሁን አዋርዱ፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡ፤ 28በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት የሕዝቡን ኃጢአት የማስወገድ ሥርዓት የሚፈጸምበት ዕለት ስለ ሆነ፥ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አትሥሩበት። 29በዚያን ዕለት በንስሓ ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ 30በዚያን ዕለት ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ቢኖር ከሕዝብ ለይቼ አጠፋዋለሁ፤ 31ስለዚህ በዚያን ዕለት ምንም ሥራ እንዳትሠሩ፤ ይህም የሥርዓት መመሪያ በምትኖሩበት ቦታ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ተጠብቆ ይኖራል። 32ወሩ ከገባ ከዘጠነኛው ቀን የፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት ጀምሮ እስከ ዐሥረኛው ቀን የፀሐይ መጥለቂያ ጊዜ ድረስ ለንስሓ ራሳችሁን አዋርዱ፤ ይህን ዕለት ልዩ የዕረፍት ቀን አድርጋችሁ ጠብቁት።” #ዘሌ. 16፥29-34።
የዳስ በዓል
(ዘኍ. 29፥12-40)
33እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 34“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ በዚህ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይከበራል። 35ከእነዚህም ቀኖች በመጀመሪያው ዕለት እግዚአብሔርን የምታመልኩበት በዓል ይሁን እንጂ ምንም ሥራ አትሥሩበት፤ 36ከሰባቱም ቀኖች በእያንዳንዱ ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ታደርጋላችሁ፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡ፤ ይህም ጉባኤውን የምትፈጽሙበት ቀን ስለ ሆነ ምንም ሥራ አትሥሩበት። #ዘዳ. 16፥13-15።
37“የምግብ መባ፥ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህሉን ቊርባን፥ መሥዋዕቱንና የመጠጡንም ቊርባን፥ በየተወሰነው ቀን ወደ እግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ ስብሰባዎች እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 38እነዚህም በዓላት ከእግዚአብሔር ሰንበቶች ጋር ተጨማሪ ሆነው የሚከበሩ ናቸው፤ ለእግዚአብሔር ከምትሰጡት ስጦታ ስእለት ሲፈጸምላችሁ ከምትሰጡት ስጦታና በፈቃዳችሁ ከምታቀርቡት ሁሉ ጋር ተደምረው የሚቀርቡ ናቸው።
39“የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ ሰባተኛው ወር ከገባ ከዐሥራ አምስተኛው ቀን በመጀመር ይህን የደስታ በዓል በእግዚአብሔር ፊት እስከ ሰባት ቀን ድረስ ታከብራላችሁ፤ መጀመሪያውና ስምንተኛው ቀን ልዩ የዕረፍት ቀን ይሆናል። 40በዚያም በመጀመሪያው ቀን ከምድራችሁ ዛፎች ምርጥ ፍሬ፥ የዘንባባ ዝንጣፊና የለምለም ዛፍ ቅርንጫፍ የወንዝ አኻያ ዛፍ ይዛችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት እየተደሰታችሁ እስከ ሰባት ቀን ድረስ በዓል አድርጉ። 41ይህንንም በዓል በየዓመቱ በሰባተኛው ወር ለሰባት ቀን ለእግዚአብሔር በደስታ አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጆቻችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው፤ 42ለሰባት ቀኖች በዳሶች ትቀመጣላችሁ፤ መላው የእስራኤል ሕዝብ በዳስ ይቀመጣሉ። 43ስለዚህም እኔ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ምድር ባወጣሁ ጊዜ ዳሶችን እየጣሉ እንዲኖሩ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”
44በዚህም ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔርን ለማክበር ስለሚጠብቁአቸው የሃይማኖት በዓላት ይህን መመሪያ ለእስራኤል ሕዝብ ሰጠ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 23: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997