ኦሪት ዘሌዋውያን 22
22
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2“ለአሮንና ለልጆቹ እንዲህ በላቸው፦ የተቀደሰ ስሜን እንዳታረክሱ የእስራኤል ልጆች ለይተው ለእኔ የሚያቀርቡትን መባ ሁሉ በአክብሮት ተቀብላችሁ በቅድስና ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3ከልጅ ልጆቻችሁ መካከል የረከሰ ሆኖ ሳለ የእስራኤል ልጆች ለእኔ ለይተው ወዳቀረቡት ቅዱስ ስጦታ ደፍሮ ቢቀርብ ከፊቴ ተወግዶ ይጠፋል፤ ይህም ሥርዓት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ተጠብቆ ይኖራል፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
4“ከአሮን ተወላጆች ማንም ሰው የሥጋ ደዌ በሽታ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት ከሆነ እስከሚነጻበት ድረስ ከተቀደሰው ነገር አይብላ። በድን በመንካቱ የረከሰውን ነገር የሚነካ ወይም የዘር ፈሳሽ ያለበት 5እንዲሁም በልቡ የሚሳብ፥ የሚያረክስ ነገርን የሚነካ፥ ወይም ርኲሰቱ ምንም ዐይነት ቢሆን የረከሰውን ሰው የሚነካ፤ 6ማንኛውም ሰው እነዚህን ነገሮች ቢነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውን በውሃ ካልታጠበ በቀር የተቀደሱትን ነገሮች አይብላ። 7ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ግን ንጹሕ ስለሚሆን የእርሱ ድርሻ የሆነውን የተቀደሰ የእህል መባ መብላት ይችላል፤ 8ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የገደለውን የእንስሳ ሥጋ አይብላ፤ እርሱን ቢበላ ያረክሰዋል፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
9“ካህናት ሁሉ እኔ የሰጠኋቸውን የሥርዓት መመሪያዎች ይጠብቁ፤ ይህን ባያደርጉ ግን ለተቀደሱት የትእዛዝ መመሪያዎች ባለመታዘዛቸው በደል ሆኖባቸው ይሞታሉ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
10“ከተቀደሰው ስጦታ መብላት የሚችለው የካህን ቤተሰብ የሆነ ሰው ብቻ ነው፤ ሌላ ሰው ግን ከእርሱ አይብላ፤ ከካህኑ ጋር በእንግድነት ወይም ተቀጥሮ የሚኖር አይብላ። 11ካህኑ በገንዘቡ የገዛው ወይም በቤቱ የተወለደ አገልጋዩ ግን የካህኑ ድርሻ ከሆነው ምግብ ይብላ። 12ካህን ያልሆነ የውጪ ሰው ያገባች የካህኑ ልጅ ከተቀደሰው ስጦታ አትብላ። 13ነገር ግን ልጅ ሳትወልድ ባልዋ የሞተባት ወይም ከባልዋ በመፋታት ወደ አባቷ ቤት ተመልሳ መጥታ በጥገኝነት የምትኖር የካህኑ ልጅ በልጅነትዋ ታደርገው እንደ ነበረው ሁሉ የአባቷ ድርሻ ከሆነው ቅዱስ ነገር ትብላ፤ ሆኖም ከካህኑ ቤተሰብ ሌላ ሰው የተቀደሰውን ነገር መብላት የለበትም።
14“የካህን ቤተሰብ ያልሆነ ማንም ሰው ባለማወቅ ከተቀደሰው ስጦታ በልቶ ቢገኝ የምግቡን ሙሉ ዋጋና አንድ አምስተኛ እጅ ጨምሮ ለካህኑ ይክፈለው። 15የእስራኤል ሕዝብ ለእግዚአብሔር የሚያመጡአቸውን የተቀደሱ ስጦታዎች፥ ካህናት ማርከስ የለባቸውም፤ 16ይኸውም መብላት ለማይፈቀድለት ሰው ቢሰጡት በደል ሆኖ በዚያ ሰው ላይ ቅጣት ያስከትልበታል፤ ስጦታዎችን ሁሉ የምቀድስ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
17እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 18“ለአሮንና ለልጆቹ ለመላውም የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ እስራኤላዊ የሆነ ወይም በእስራኤላውያን መካከል የሚኖር መጻተኛ ስእለት ተፈጽሞለት ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጎ የሚቃጠል መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ 19መሥዋዕቱም ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ምንም ነውር የሌለበት የከብት፥ የበግ ወይም የፍየል ተባዕት ይሁን። 20ነውር ያለበትን ማናቸውንም እንስሳ ብታቀርቡ ግን እግዚአብሔር አይቀበለውም። #ዘዳ. 17፥1። 21ማንም ሰው ስእለት ተፈጽሞለት ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጎ የአንድነት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ቢያቀርብ፥ ተቀባይነት ማግኘት እንዲችል፥ እንስሳው ምንም ነውር የሌለበት ይሁን። 22ዕውር፥ ሰባራ ወይም ጉንድሽ የሆነ ወይም የሚመግል ቊስል፥ እከክ ወይም ሽፍታ ያለበት ማናቸውንም እንስሳ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ፤ እንደነዚህ ያሉትን እንስሶች በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ። 23አካሉ የጐደለ ወይም ቅርጹ የተበላሸ እንስሳ የበጎ ፈቃድ መሥዋዕት ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፤ ነገር ግን ስእለት የተፈጸመለት ሰው መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው አይችልም። 24ብልቱ የተበላሸ እንስሳ ለእግዚአብሔር በምድርህ መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ።
25“ከባዕድ ሰው የተገኘውን እንስሳ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገህ አታቅርብ፤ እነዚህን የመሳሰሉ እንስሶች ነውር እንዳለባቸው ስለሚቈጠሩ ተቀባይነት የላቸውም።”
26እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 27“እንቦሳ፥ ወይም በግ፥ ወይም ፍየል ሲወለድ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ ይችላል።
28“ላምን ከጥጃዋ ጋር፥ በግንም ከግልገልዋ ጋር በአንድ ቀን አትረድ፤ 29ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት በምታቀርብበት ጊዜ ተቀባይነት ታገኝ ዘንድ የመመሪያ ሥርዓቶችን ጠብቅ፤ 30ለተከታዩ ቀን ሳታስተርፍ ሁሉንም በቀረበበት ዕለት ብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
31እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ትእዛዞቼን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ 32የተቀደሰውን ስሜን አታዋርዱ፤ መላው የእስራኤል ሕዝብ እኔ ቅዱስ መሆኔን ተገንዝበው ያክብሩኝ፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ 33አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 22: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997