ኦሪት ዘሌዋውያን 21
21
ለካህናት የተሰጠ መመሪያ
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከሕዝቡ መካከል የሞተውን ሰው አስከሬን በመንካት ስለ ሞተ ሰው ማናቸውም ራሳቸውን እንዳያረክሱ የአሮን ተወላጆች ለሆኑ ካህናት ንገራቸው፤ 2በዝምድና ቅርብ ከሆኑት፥ ከአባቱ፥ ከእናቱ፥ ከወንድ ልጁ፥ ከሴት ልጁ፥ ከወንድሙ፥ 3ወይም ካላገባች እኅቱ በቀር፥ 4በጋብቻ የተዛመዱትን ሰዎች ሬሳ እንኳ በመንካት ራሱን አያርክስ።
5“ካህናት፥ ለሙታን በማዘን የራስ ጠጒራቸውን አይላጩ፤ ጢማቸውን አሳጥረው አይቊረጡ፤ ፊታቸውንም አይንጩ። #ዘሌ. 19፥27-28፤ ዘዳ. 14፥1። 6የሚቃጠል መሥዋዕትና የምግብ መባ ለእኔ ለአምላካቸው የሚያቀርቡ ካህናት ለእኔ የተለዩና ስሜንም የማያረክሱ መሆን አለባቸው፤ ስለዚህ የተቀደሱ ይሆናሉ። 7ካህናት ለአምላካቸው ተለይተው የተቀደሱ ስለ ሆኑ፥ አመንዝራ የነበረች ሴት፥ ወይም ክብረ ንጽሕናዋ የተደፈረ ልጃገረድ ወይም አግብታ የፈታች ሴት አያግቡ፤ 8ሕዝቡም ካህኑን ቅዱስ እንደ ሆነ ይቊጠረው፤ እርሱ ለእኔ ለአምላካችሁ የምግብ መባ ያቀርባል፤ እኔ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝ፤ 9የማንኛውም ካህን ሴት ልጅ አመንዝራ ብትሆን አባትዋን ታስነውራለች፤ እርስዋ በእሳት ተቃጥላ ትሙት።
10“ሊቀ ካህናቱ የቅባት ዘይት በራሱ ላይ የፈሰሰበትና የክህነትንም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ ስለ ሆነ፥ ሰው በሞተ ጊዜ ሐዘኑን ለመግለጥ ጠጒሩን አይላጭ፤ ልብሱንም አይቅደድ፤ 11የማናቸውም ሰው አስከሬን የአባቱም ሆነ ወይም የእናቱ ወደ አለበት ቤት ገብቶ ራሱን አያርክስ፤ 12የእኔ የአምላኩ የክህነት ቅድስና በእርሱ ላይ ስላለ ከመቅደስ ወጥቶ የአምላኩን መቅደስ አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13ድንግል የሆነችውን ልጅ ያግባ፤ 14ባልዋ የሞተባትን ወይም አግብታ የተፋታችውን ወይም ክብረ ንጽሕናዋ የተደፈረውን፥ ወይም አመንዝራ የነበረችውን ሴት አያግባ፤ ድንግል የሆነችውን ብቻ ወገኑ ከሆኑ ሕዝብ መካከል መርጦ ያግባ። 15ይህ ካልሆነ ግን በሕዝቡ መካከል ልጆቹ የረከሱ ይሆናሉ፤ የምቀድሰው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
16እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 17“ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘ከዘርህ የአካል ጒድለት ያለበት ማንም ሰው የእኔን የአምላኩን የምግብ መባ ማቅረብ የለበትም፤ ይህም ሥርዓት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ተጠብቆ ይኖራል፤ 18የአካል ጒድለት ያለበት ማንም ሰው፥ ይኸውም ዕውር ወይም አንካሳ የሆነ፥ መልኩ ወይም ቅርጹ የተበላሸ፥ 19እጀ ሰባራ ወይም እግረ ሰባራ የሆነ፥ 20በጀርባው ላይ ጉብር ያለበት ወይም ድንክ፥ የዐይን ሕመም ወይም ልዩ ልዩ ዐይነት የቆዳ በሽታ ያለበት፥ ወይም ጃንደረባ የምግብ ቊርባን ለእኔ ለእግዚአብሔር ሊያቀርብ አይገባውም። 21በአጠቃላይ ከካህኑ አሮን ዘሮች መካከል የአካል ጒድለት ያለበት ማንም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የምግብ ቊርባን ለአምላኩ ማቅረብ አይችልም። 22እንዲህ ያለው ሰው ሁለቱንም ዐይነት፥ ማለትም የተቀደሰውንና እጅግ ቅዱስ የሆነውን የምግብ መባ መብላት ይችላል፤ 23ነገር ግን የአካል ጒድለት ስላለበት ወደተቀደሰው መጋረጃ ወይም ወደ መሠዊያው አይቅረብ፤ እነዚህን ለእኔ የተቀደሱትን ነገሮች ማርከስ የለበትም፤ እነርሱንም የቀደስኳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”
24ሙሴም ይህን ሁሉ ለአሮንና ለአሮን ልጆች፥ ለመላውም የእስራኤል ሕዝብ ተናገረ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 21: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997