ኦሪት ዘሌዋውያን 20
20
አለመታዘዝ የሚያስከትለው ቅጣት
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገር፦ ከእናንተም ሆነ ወይም በመካከላችሁ ከሚኖሩት የውጪ አገር ተወላጆች ውስጥ፥ ማንም ሰው ሞሌክ ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ ከልጆቹ አንዱን አሳልፎ ሰጥቶ ቢገኝ መላው የእስራኤል ሕዝብ በድንጋይ ወግሮ ይግደለው። 3ማንም ሰው ከልጆቹ አንዱን ለሞሌክ አሳልፎ በመስጠት የተቀደሰውን ድንኳኔን ቢያረክስና ቅዱስ ስሜንም ቢያሰድብ፥ ያ ሰው በእኔ ፊት የተጠላ ይሆናል፤ ከሕዝቡም ለይቼ አጠፋዋለሁ። 4ነገር ግን ሕዝቡ ያ ሰው ያደረገውን ሁሉ በቸልተኛነት ቢያልፈውና በሞት ባይቀጣው፥ 5እኔ ራሴ በዚያ ሰውና በመላ ቤተሰቡ እንዲሁም ለእኔ ታማኝ ባለመሆን ለሞሌክ በመስገድ ከእርሱ ጋር በሚተባበሩት ሁሉ ላይ መዓቴን አመጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ ከሕዝቡ መካከል ለይቼ አጠፋቸዋለሁ።
6“ማንም ሰው ምክር ለመጠየቅ ወደ ሙታን መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች ቢሄድ በዚያ ሰው ላይ ቊጣዬን አወርዳለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ፤ 7እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሁለንተናችሁን የተቀደሰ አድርጉ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ 8ኅጎቼን ጠብቁ፤ ፈጽሙአቸውም፤ እኔ እናንተን የምቀድሳችሁ አምላካችሁ ነኝ።”
9ማንኛውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን ቢሰድብ ይገደል፤ አባቱንና ወይም እናቱን ስለ ሰደበ ሞት የተፈረደበት በራሱ በደል ነው። #ዘዳ. 21፥17፤ ማቴ. 15፥4፤ ማር. 7፥10።
10አንድ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ቢያመነዝር፤ አመንዝራውና አመንዝራይቱ ሁለቱም በሞት ይቀጡ፤ #ዘፀ. 20፥14፤ ዘሌ. 18፥20፤ ዘዳ. 5፥18። 11አንድ ሰው የአባቱ ሚስት ከሆነችው ሴት ጋር ቢተኛ፥ የአባቱን ኀፍረተ ሥጋ ስለ ገለጠ እርሱና ሴትዮዋ ሁለቱም በሞት ይቀጡ፤ የተፈረደባቸውም በራሳቸው በደል ነው። 12አንድ ሰው ከምራቱ ጋር ቢያመነዝር ሁለቱም በሞት ይቀጡ፤ የሥጋን ዝምድና በዝሙት በማርከሳቸው ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። 13አንድ ወንድ ከሌላው ወንድ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርግ የረከሰ ሥራ ስለ ሠሩ ሁለቱም ይገደሉ፤ ለመሞታቸውም ኀላፊነቱ የራሳቸው ነው። 14አንድ ሰው እናትና ሴት ልጅዋን ቢያገባ፥ ስለ ፈጸሙት ክፉ ድርጊት ሦስቱም በእሳት ተቃጥለው ይገደሉ፤ እንዲህ ያለው ነገር በመካከላችሁ መፈጸም የለበትም። #ዘሌ. 18፥17፤ ዘዳ. 27፥23። 15አንድ ሰው ከእንስሳ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርግ፥ እርሱም እንስሳውም ይገደሉ፤ 16አንዲት ሴት ከእንስሳ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ብታደርግ እርስዋም እንስሳውም ይገደሉ፤ ስለ መሞታቸውም ኀላፊነቱ የራሳቸው ይሆናል። #ዘፀ. 22፥19፤ ዘሌ. 18፥23፤ ዘዳ. 27፥21።
17አንድ ሰው እኅቱን ወይም በአንድ በኩል ብቻ ከአባቱ ወይም ከእናቱ የተወለደችውን እኅቱን አግብቶ ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርጉ ይህ አስነዋሪ ነገር በመሆኑ ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ፤ ከእኅቱ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ስላደረገ ፍዳውን ይቀበላል። #ዘሌ. 18፥9፤ ዘዳ. 27፥22። 18አንድ ሰው የወር አበባ ካለባት ሴት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርግ የወር አበባዋን ኀፍረት ገልጠዋል ሁለቱም ከሕዝቡ ተለይተው ይባረሩ። #ዘሌ. 18፥19።
19ከአክስትህ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ፤ በዚህ የሥጋ ዝምድናን ማፍረሳቸው ስለ ሆነ ሁለቱም ፍዳቸውን ይቀበላሉ። 20አንድ ሰው ከአጐቱ ሚስት ጋር ቢተኛ አጐቱን ያዋረደ ስለ ሆነ እርሱም ሆነ ሴትዮዋ ፍዳቸውን ይቀበላሉ፤ ያለ ልጅም ይቀራሉ። #ዘሌ. 18፥12-14። 21አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ቢያገባ ተግባሩ ርኲሰት ነው፤ የወንድሙንም ክብር ያዋርዳል፤ በዚህም ምክንያት ሁለቱም ልጅ አልባ ሆነው ይቀራሉ። #ዘሌ. 18፥16።
22“እኔ እንድትገቡባት የማደርጋት የከነዓን ምድር አንቅራ እንዳትተፋችሁ ሕጌንና ሥርዓቴን ሁሉ ጠብቁ፤ 23በፊታችሁ የማባርራቸውን ሕዝቦች ልማድ አትከተሉ፤ ይህን ሁሉ ነገር ስላደረጉ ተጸየፍኳቸው። 24ነገር ግን ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ በማርና በወተት የበለጸገችውን ምድር እንድትወርሱ እሰጣችኋለሁ፤ ከሌሎች ሕዝቦች እንድትለዩ ያደረግኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 25ስለዚህም ንጹሓን በሆኑትና ንጹሓን ባልሆኑት እንስሶችና ወፎች መካከል ልዩነት አድርጉ፤ እኔ ርኩሳን ናቸው ብዬ ለይቼ ባስታወቅኋችሁና በምድር ላይ በሚገኙ እንስሶች፥ ወፎችና ሌሎችም ነገሮች ሁሉ ራሳችሁን አታርክሱ፤ 26እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለ ሆንኩና የእኔ ትሆኑ ዘንድ እናንተን ከአሕዛብ ስለ ለየኋችሁ፥ እናንተ ለእኔ የተቀደሳችሁ ሁኑ።
27“ወንድ ወይም ሴት የሙታን መናፍስት ጠሪዎች ወይም ጠንቋዮች ቢሆኑ ይገደሉ፤ በድንጋይ ተወግረው ይገደሉ፤ በሞት የሚቀጡትም በራሳቸው በደል ነው።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 20: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997