የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 19

19
የፍትሕና የቅድስና ኅጎች
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2“ለእስራኤል ሕዝብ ይህን ንገር፦ ‘እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፤ #ዘሌ. 11፥44-45፤ 1ጴጥ. 1፥16። 3ከእናንተ እያንዳንዱ እናትና አባቱን ያክብር፤ እኔ ባዘዝኩት መሠረት ሰንበትን ይጠብቅ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ #ዘፀ. 20፥8፤12፤ ዘዳ. 5፥12፤16።
4“ወደ ጣዖት አምልኮ አትመለሱ፤ ወይም ብረት አቅልጣችሁ አማልክትን አትሥሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። #ዘሌ. 20፥15-16፤ ዘዳ. 5፥19-20።
5“ለአንድነት መሥዋዕት አንድ ዐይነት እንስሳ በምተሠዉበት ጊዜ፥ የሰጠኋችሁን ሥርዓት ጠብቁ፤ መሥዋዕቱም በእኔ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል። 6ሥጋውም እንስሳው በታረደበት ዕለት ወይም በማግስቱ መበላት አለበት፤ እስከ ሦስተኛው ቀን ተርፎ የቈየ ማናቸውም ሥጋ በእሳት ይቃጠል። 7በሦስተኛው ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ መሥዋዕቱም ተቀባይነት አይኖረውም፤ 8ከእርሱ የሚበላ ማንም ሰው ለእኔ የተቀደሰውን እንደ ተራ ነገር በመቊጠሩ በደል ይሆንበታል፤ ከሕዝቤም ይለያል።
9“የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ በእርሻችሁ ድንበር ያለውን እህል አትጨዱ፤ ስታጭዱ የቀረውንም ቃርሚያ ለመሰብሰብ ወደ ኋላ አትመለሱ፤ 10የወይን መከርህንም ስትሰበስብ በሐረጉ ላይ ተሰውሮ የቀረውን ወይም በመሬት ላይ የረገፈውን የወይን ዘለላ አጥርተህ ለመልቀም እንደገና ወደ ኋላ አትመለስ፤ ይህን ሁሉ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
11“አትስረቁ፤ አታታሉ፤ ውሸት አትናገሩ፤ 12በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ የአምላካችሁንም ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። #ዘፀ. 20፥7፤ ዘዳ. 5፥11፤ ማቴ. 5፥33።
13“በጐረቤትህ ላይ ግፍ አትሥራ፤ ወይም ንብረቱን አትቀማው፤ ቀጥረህ የምታሠራውን ሰው ደመወዝ ለአንድ ሌሊት እንኳ በአንተ ዘንድ አይደር። #ዘዳ. 24፥14-15። 14ደንቆሮውን አትስደብ፤ ዐይነ ዕውሩንም ለማሰናከል በፊቱ እንቅፋት አታኑር፤ አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ። #ዘዳ. 27፥18።
15“የፍርድ ውሳኔ በምትሰጡበት ጊዜ ታማኞችና ትክክለኞች ሁኑ፤ ለሁሉም በትክክል ፍረዱ እንጂ ለድኻው ስለ ድኽነቱ አድልዎ አታድርጉለት፤ ባለጸጋውንም ስለ ሀብቱ ብዛት አትፍሩት። #ዘፀ. 23፥6-8፤ ዘዳ. 16፥19። 16በሕዝብህ መካከል እየዞርክ የስም አጥፊነት ወሬ አታሰራጭ፤ ሰውን ወደ ሞት አደጋ የሚያደርስ ምንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ።
17“ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በእርሱ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው። #ማቴ. 18፥15። 18መበቀል አትፈልግ፤ በወገንህ በማንም ላይ ቂም አትያዝ፤ ነገር ግን ጐረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። #ማቴ. 5፥43፤ 19፥19፤ 22፥39፤ ማር. 12፥31፤ ሉቃ. 10፥2።
19“ትእዛዞቼን ጠብቁ፤ አንዱን እንስሳ ከሌላው ጋር አታዳቅል፥ በአንድ እርሻ ላይ ሁለት ዐይነት እህል አትዝራ፥ ከሁለት ዐይነት ነገር ተፈትሎ የተሠራ ልብስ አትልበስ። #ዘዳ. 22፥9-11፤ 13፥9፤ ገላ. 5፥14፤ ያዕ. 2፥8።
20“አንድ ሰው ልጃገረድ የሆነች አገልጋዩን ለሌላ ሰው ቊባት ትሆን ዘንድ ለመሸጥ ካስማማ በኋላ ገዢው ገንዘቡን ከፍሎ ከመጨረሱ በፊት ሻጩ ከልጃገረዲቱ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት ቢያደርግ ሁለቱም ይቀጣሉ፤ ሆኖም እርስዋ ገና ነጻ ያልወጣች አገልጋዩ ስለ ሆነች የሞት ቅጣት አይፈጸምባቸውም። 21ይህን በደል የፈጸመ ሰው ለበደል ስርየት መሥዋዕት አድርጎ አንድ የበግ አውራ ወደ መገናኛው ድንኳን ወደ እኔ ያምጣ። 22ካህኑም የዚያን ሰው ኃጢአት በአውራ በጉ የበደል መሥዋዕት ያስተሰርይለታል፤ እኔ እግዚአብሔርም በደሉን ይቅር እለዋለሁ።
23“ወደ ከነዓን ምድር ገብታችሁ ማንኛውንም ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ እስከ መጀመሪያው ሦስት ዓመት ድረስ የሚሰጠውን ፍሬ መብላት የተከለከለ መሆኑን አስታውሱ። በእነዚህም ዓመቶች ውስጥ ፍሬው አይበላም። 24በአራተኛው ዓመት እኔን እግዚአብሔርን ታመሰግኑበት ዘንድ ለእኔ የተለየ ስጦታ ይሁን። 25በአምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ ይህን ብታደርጉ ዛፎቻችሁ በየጊዜው የሚሰጡአችሁ ፍሬ ይበልጥ እየበዛ ይሄዳል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
26“ደም ያለበትን ሥጋ አትብሉ፤ የአስማትን ነገር አትከተሉ፤ #ዘፍ. 9፥4፤ ዘሌ. 7፥26-27፤ 17፥10-14፤ ዘዳ. 12፥16፤23፤ 15፥23፤ 18፥10። 27የራስ ጠጒራችሁን ዙሪያውን አትከርክሙት፤ ጢማችሁን አሳጥራችሁ አትቊረጡት፤ 28በሰውነታችሁ ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ ወይም ለሙታን በማዘን ሰውነታችሁን አትቈራርጡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። #ዘሌ. 21፥5፤ ዘዳ. 14፥1።
29“ምድሪቱ በዝሙትና በርኲሰት እንዳትሞላ ታመነዝር ዘንድ ለሴት ልጅህ አትፍቀድላት። #ዘዳ. 23፥17። 30ሰንበትን ጠብቁ፤ መቅደሴን አክብሩ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። #ዘሌ. 26፥2።
31“ከሙታን መናፍስት ጠሪዎች ወይም ከጠንቋዮች ምክር አትጠይቁ፥ ይህን ብታደርጉ የረከሳችሁ ትሆናላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። #ዘዳ. 18፥11፤ 1ሳሙ. 28፥3፤ 2ነገ. 23፥4፤ ኢሳ. 8፥19።
32“በዕድሜ የገፉ ሽማግሌዎች ሲመጡ ስታይ ከተቀመጥክበት በመነሣት አክብራቸው፤ እኔን አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
33“በምድራችሁ ከእናንተ ጋር ባዕዳን ቢኖሩ አትበድሉአቸው፤ 34ለእስራኤላዊ ወገናችሁ በምታደርጉት ዐይነት መልካም ነገር አድርጉላቸው፤ እንደ ራሳችሁም አድርጋችሁ ውደዱአቸው፤ እናንተም ከዚህ በፊት በግብጽ ምድር ባዕዳን እንደ ነበራችሁ አስታውሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። #ዘፀ. 22፥21፤ ዘዳ. 24፥17-18፤ 27፥19።
35“በርዝመት መለኪያ፥ በክብደት መለኪያና በመስፈሪያ አትበድሉ። 36ትክክለኞች የሆኑ ሚዛኖች ማለት የርዝመት፥ የክብደትና የፈሳሽ መለኪያዎች ይኑሩአችሁ፤ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። #ዘዳ. 25፥13-16፤ ምሳ. 20፥10። 37ለሰጠኋችሁ ሕግና ትእዛዝ ሁሉ ታማኞች ሁኑ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ