የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 18

18
የተከለከለ ፍትወታዊ ግንኙነት
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ 3በኖራችሁባት በግብጽ ምድር፥ ወይም አሁን እኔ በማስገባችሁ በከነዓን ምድር የሚኖሩ አሕዛብ የሚያደርጉትን አታድርጉ፤ ሥርዓታቸውንም አትከተሉ። 4ኅጎቼን ፈጽሙ፤ ሥርዓቴን ጠብቁ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 5እኔ የምሰጣችሁን ኅጎቼንና ሥርዓቴን ጠብቁ፤ ይህን በማድረግ ማናቸውም ሰው ሕይወቱን ያድናል፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” #ነህ. 9፥29፤ ሕዝ. 18፥9፤ 20፥11-13፤ ሉቃ. 10፥28፤ ሮም 10፥5፤ ገላ. 3፥12።
6“ማንም ሰው ፍትወታዊ ግንኙነት ለማድረግ ወደ ሥጋ ዘመዱ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ 7ከእናትህ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት በማድረግ የአባትህን ክብር አታዋርድ፤ እናትህ ስለ ሆነች የእርስዋን ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ። 8ከሌሎቹ ሚስቶቹም ፍትወታዊ ግንኙነት በማድረግ አባትህን አታዋርድ። #ዘሌ. 20፥11፤ ዘዳ. 22፥30፤ 27፥20። 9ከእኅትህ ጋር የፍትወተ ሥጋ ግንኙነት አታድርግ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የናትህ ልጅ፥ በቤት ወይም በውጪ የተወለደች ብትሆን ኀፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። #ዘሌ. 20፥17፤ ዘዳ. 27፥22። 10ኀፍረተ እንዳይሆንብህ ከልጅ ልጅህ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ። 11እኅትህ ስለ ሆነች ከአባትህና ከእንጀራ እናትህ ልጅ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ። 12አክስትህ ስለ ሆነች ከአባትህ እኅት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ። 13አክስትህ ስለ ሆነች ከእናትህ እኅት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ። 14እንደ አክስትህ ስለ ሆነች ከአጐትህ ሚስት ጋር ፍትወታዊ #ዘሌ. 20፥19-20። ግንኙነት አታድርግ። 15የልጅህ ሚስት ስለ ሆነች ከምራትህ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ። #ዘሌ. 20፥1። 16ዋርሳ ስለ ሆነች ከወንድምህ ሚስት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ። #ዘሌ. 20፥21። 17ከእናትና ከሴት ልጅዋ፥ እንዲሁም ከልጅ ልጆችዋ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ፤ እነርሱም የቅርብ ዘመዶችህ ስለ ሆኑ ኃጢአት ይሆንብሃል። #ዘሌ. 20፥14፤ ዘዳ. 27፥23። 18ሚስትህ በሕይወት እያለች እኅትዋ ጣውንትዋ እንዳትሆን እኅትዋን አታግባ፤ ከእርስዋም ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።
19“በወር አበባዋ ምክንያት ካልነጻች ሴት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ። 20ከሌላ ሰው ሚስት ጋር በመተኛት ራስህን ከእርስዋ ጋር አታርክስ። #ዘሌ. 20፥10። 21የእግዚአብሔር አምላክህን ስም እንዳታሰድብ ከልጆችህ ማንኛውንም ሞሌክ ለተባለው ባዕድ አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆን ዘንድ አሳልፈህ አትስጥ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። #ዘሌ. 20፥1-5። 22በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነገር ስለ ሆነ፥ ግብረ ሰዶም አትፈጽም። #ዘሌ. 20፥13። 23ወንድ ወይም ሴት ማንም ሰው ከእንስሳ ጋር ተኝቶ ራሱን አያርክስ፤ እንዲህ ያለው ድርጊት የተፈጥሮን ሕግና ሥርዓት የሚያበላሽ ነው። #ዘፀ. 22፥19፤ ዘሌ. 20፥15-16፤ ዘዳ. 27፥21።
24“ወደ ምድራቸው ያስገባህ ዘንድ እግዚአብሔር ከፊትህ የሚያስወግዳቸው ሕዝቦች ራሳቸውን ያረከሱባቸው ስለ ሆኑ፥ ከእነዚህ ድርጊቶች በአንዱ እንኳ ራስህን አታርክስ። 25ምድሪቱ ረከሰች፤ በበደልዋ ምክንያት ቀጣኋት፤ እርስዋም የሚኖሩባትን ሰዎች አንቅራ ተፋቻቸው። 26ትእዛዞቼንና ኅጎቼን ጠብቁ፤ ከእነዚህ ርኲሰቶች እናንተም ሆናችሁ በመካከላችሁ የሚኖሩ ባዕዳን አንዳቸውንም አታድርጉ። 27ከእናንተ በፊት የነበሩት የምድሪቱ ኗሪዎች እነዚህን ርኲሰቶች ሁሉ ስለ ፈጸሙ ምድሪቱን አርክሰዋታል። 28ምድሪቱን ብታረክስዋት ከእናንተ በፊት የነበሩትን ሕዝቦች እንደ ተፋች እናንተንም አንቅራ ትተፋችኋለች። 29እነዚህን ርኲሰቶች የሚፈጽም ያ ሰው ከሕዝቡ ይለይ።
30“እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዝ ሁሉ ፈጽሙ፤ ከእናንተ በፊት በምድሪቱ ይፈጽሙት የነበረውን የረከሰ ልማድ አትከተሉ፤ ከእነዚህ አሳፋሪ ተግባሮች አንዱንም በመፈጸም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ