ኦሪት ዘሌዋውያን 17
17
መሥዋዕት የት ማቅረብ እንደሚገባ
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ 2“ ‘እግዚአብሔር ያዘዘው ትእዛዝ ይህ ነው’ ብለህ ለአሮንና ለልጆቹ እንዲሁም ለእስራኤላውያን ሁሉ ንገር፤ 3ከእስራኤል ሕዝብ ማናቸውም ሰው በሬ፥ ወይም በግ፥ ወይም ፍየል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ በሰፈር ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጪ ቢያርድ፥ 4በተቀደሰው ስፍራ ለእግዚአብሔር ቊርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደም በከንቱ እንዳፈሰሰ ተቈጥሮ ይፈረድበታል፤ ከሕዝቡም ይለያል።
5“ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያመጡታል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር የአንድነት መሥዋዕት አድርጎ ያቀርበዋል። 6ካህኑ ደሙን በድንኳኑ መግቢያ በመሠዊያው ላይ ይርጭ፤ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ጣፋጭ ሽታ ይሆን ዘንድ ስቡንም ያቃጥለው፤ 7የእስራኤል ሕዝብ ከእምነታቸው ለሚያርቁአቸው አጋንንት መሥዋዕት አድርገው እንስሶቻቸውን በየሜዳው በማረድ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ አይገባቸውም፤ እስራኤላውያን ይህን ሥርዓት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ይጠብቁት።
8“ለእነርሱም እንዲህ በላቸው፦ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በማኅበሩ መካከል የሚኖር መጻተኛ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ 9ለእግዚአብሔር ይሠዋው ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው ያ ሰው ከሕዝቡ ይለይ።’
የደም መብላት መከልከል
10“ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በሕዝቡ መካከል የሚኖር መጻተኛ ደም ቢበላ በፊቴ የተጠላ ይሆናል፤ ያንንም ሰው ከሕዝቡ እለየዋለሁ። #ዘፍ. 9፥4፤ ዘሌ. 7፥26-29፤ 19፥26፤ ዘዳ. 12፥16፤23፤ 15፥23። 11የማንኛውም ሕያው ፍጥረት ሕይወት የሚገኘው በደሙ ውስጥ ነው፤ ደሙ በመሠዊያው ላይ ለእናንተ ኃጢአት ማስተስረያ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ፤ ደምም ሕይወት ስለ ሆነ የኃጢአት ማስተስረያ ነው። #ዕብ. 9፥22። 12ስለዚህ ለእስራኤላውያን የምለው ይህ ነው፤ ከእናንተ ማንም፥ ወይም በመካከላችሁ ከሚኖሩ ማንኛውም መጻተኛ ደም መብላት የለበትም።
13“ማናቸውም እስራኤላዊ ወይም በሕዝቡ መካከል የሚኖር መጻተኛ የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ አድኖ ቢይዝ ደሙን በመሬት ላይ አፍስሶ በዐፈር ይሸፍነው። 14የእያንዳንዱ ሕያው ፍጥረት ሕይወት የሚገኘው በደሙ ውስጥ ነው፤ የያንዳንዱ ፍጥረት ሕይወት የሚገኘው በደሙ ስለ ሆነ ደም አትብሉ የእስራኤልን ሕዝብ ብዬ አዝዣለሁ፤ ደምንም የሚበላ ሁሉ ከሕዝቡ ይለያል።
15“ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም የውጪ አገር ተወላጅ የሆነ ሰው፥ ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የገደለውን የእንስሳ ሥጋ ቢበላ ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል፤ 16ገላውን ባይታጠብና ልብሱን ባያጥብ ግን በኃጢአቱ ቅጣቱን ያገኛል።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 17: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997