ኦሪት ዘሌዋውያን 16

16
የኃጢአት ስርየት ቀን
1ሁለቱ የአሮን ልጆች ያልተፈቀደ እሳት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ፊት በመቅረባቸው ከሞቱ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2“እኔ በታቦቱ ስርየት መክደኛ በደመና የምገለጥበት ስለ ሆነ፥ መጋረጃውን አልፎ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት ያለበት ሁልጊዜ ሳይሆን፥ በአንድ በተወሰነ ቀን ብቻ መሆኑን፥ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው፤ ይህን ትእዛዝ የማይፈጽም ከሆነ ይሞታል፤ #ዕብ. 6፥19። 3ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችለውም ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አንድ አውራ በግ ካቀረበ በኋላ መሆን አለበት።” #ዕብ. 9፥7።
4“አሮን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከመግባቱ በፊት ሰውነቱን ታጥቦ የክህነት ልብሱን ይልበስ፤ ይኸውም ከበፍታ የተሠራውን ቀሚስና ሱሪ ይልበስ፤ እንዲሁም ከበፍታ የተሠራውን ቀበቶ ይታጠቅ፤ ከበፍታ የተሠራውንም መጠምጠሚያ ራሱ ላይ ያድርግ።
5“የእስራኤልም ማኅበር ስለ ኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት ሁለት ተባዕት ፍየሎች፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ለአሮን ያምጡለት። 6የራሱንና የቤተሰቡንም ኃጢአት ለማስተስረይ አንድ ኰርማ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። 7ከዚህም በኋላ ሁለቱን ፍየሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ይውሰድ፤ 8በዚያም አንዱ ‘ለእግዚአብሔር’ ሁለተኛው ‘ለዐዛዜል’ የሚል ምልክት ያለባቸው ሁለት ድንጋዮች ወስዶ ዕጣ ያውጣ፤ #16፥8 ዐዛዜል፦ የዚህ የዕብራይስጥ ቃል ፍቺ በትክክል አይታወቅም፤ ምናልባት የበረሓ ጋኔን ስም ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል። 9አሮንም በዕጣ ለእግዚአብሔር የተመረጠውን ፍየል ስለ ኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል። 10ለዐዛዜል የተመረጠውም ፍየል የሕዝቡን ኃጢአት ተሸክሞ ወደ በረሓ እንዲላክ ከነሕይወቱ ወደ እግዚአብሔር ፊት ይቀርባል።”
11አሮንም ኰርማውን ስለ ራሱና ስለ ቤተሰቡ የኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት በማድረግ ይረደው፤ 12ከመሠዊያው የሚቃጠል የእሳት ፍም በጥናው ሞልቶም ሁለት እፍኝ ጣፋጭ ሽታ ያለውን የተወቀጠ ደቃቅ ዕጣን በመውሰድ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያግባ፤ 13እዚያም በእግዚአብሔር ፊት በእሳቱ ላይ ዕጣን ይጨምርበት፤ እርሱም አይቶ እንዳይሞት የዕጣኑ ጢስ የስርየት መክደኛውን ይሸፍነው። 14ከኰርማውም ደም ጥቂት ወስዶ በጣቱ እየነከረ በስርየት መክደኛው ላይ ከፊት ለፊት በኩል ይርጭ፤ እንዲሁም ከእርሱ ጥቂቱን በኪዳኑ ታቦት ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው።
15ከዚህም በኋላ ለሕዝቡ የኃጢአት ማስተስረያ የሆነውን ፍየል ይረድ፤ ደሙንም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አስገብቶ በኰርማው ደም ባደረገው ዐይነት፥ በስርየት መክደኛው ላይ፥ እንዲሁም በኪዳኑ ታቦት ፊት ይርጨው። #ዕብ. 9፥12። 16በዚህም ዐይነት ቅድስተ ቅዱሳኑን ከእስራኤል ሕዝብ ርኲሰትና ከኃጢአታቸውም ሁሉ ለማጥራት የማንጻትን ሥርዓት ይፈጽማል፤ ንጹሕ ባልሆነ ሰፈር መካከል ስለሚገኝ ድንኳኑንም ለማንጻት እንዲሁ ያደርጋል። 17አሮን ለማስተሰረይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተሰቡ፥ ለእስራኤል ጉባኤ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ ድንኳን ውስጥ ማንም አይኑር፤ 18ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ወዳለው መሠዊያ ወጥቶ መሠዊያውን ያንጻው፤ ከኰርማውና ከፍየሉ ጥቂት ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ጒጦች ይቀባ፤ 19ከደሙም ጥቂቱን ወስዶ በጣቱ እየነከረ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ይርጭ፤ በዚህም ዐይነት ከእስራኤል ሕዝብ ርኲሰትን በማንጻት መሠዊያውን የተቀደሰ ያደርገዋል።
የሕዝብን በደል ተሸክሞ ወደ በረሓ የሚለቀቅ ፍየል
20አሮን ቅድስተ ቅዱሳኑን፥ የመገናኛውን ድንኳን የቀረውን ክፍልና መሠዊያውንም የማንጻት ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ ለዐዛዜል የተመረጠውን ፍየል ወስዶ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። 21ሁለት እጆቹን በፍየሉ ራስ ላይ ይጭናል፤ የሕዝቡን ክፋት፥ ኃጢአትና ዐመፅ ሁሉ በመናዘዝ አዛውሮ በፍየሉ ራስ ላይ ያሸክመዋል፤ ከዚህ በኋላ ለዚህ ሥራ የተመደበ ሰው ፍየሉን ነድቶ ወደ በረሓ ይወስደዋል። 22ፍየሉንም ኃጢአታቸውን ሁሉ ተሸክሞ ምንም ሰው ወደማይኖርበት ምድረ በዳ ወስዶ ይለቀዋል።
23“አሮንም ወደ ድንኳኑ ይግባ፤ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከመግባቱ በፊት ለብሶት የነበረውን የክህነት ልብስ አውልቆ፥ በዚያ ይተወው፤ #ሕዝ. 44፥19። 24በተቀደሰውም ቦታ ሰውነቱን ታጥቦ የዘወትር ልብሱን ይልበስ፤ ከዚያም ወጥቶ የራሱንና የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቅርብ። 25ኃጢአትን ለማስተስረይ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውንም የእንስሳ ስብ፥ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ 26የተመረጠውን ፍየል እየነዳ ወደ በረሓ ይዞት ሄዶ የነበረውም ሰው ወደ ሰፈር ከመግባቱ በፊት ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ። 27ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሆነው የቀረቡትና ኃጢአትን ለማስተስረይ ደማቸው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ የነበረው ኰርማና ፍየልም ከሰፈር ወደ ውጪ ተወስደው በእሳት ይቃጠሉ፤ እንዲሁም ቆዳቸው፥ ሥጋቸውና የሆድ ዕቃቸው በሙሉ ይቃጠል። #ዕብ. 13፥11። 28እነርሱንም የሚያቃጥለው ሰው ወደ ሰፈር ከመመለሱ በፊት ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ።
የኃጢአት ማስተስረያን ቀን ስለ መጠበቅ
29“ከዚህ የሚከተሉትን መመሪያዎች በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ቋሚ ሥርዓት አድርጋችሁ ትጠብቁአቸዋላችሁ፦ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እስራኤላውያንና በእነርሱ መካከል የሚኖሩ መጻተኞች ራሳቸውን ማዋረድ አለባቸው፤ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አይሥሩበት። #ዘሌ. 23፥26-32፤ ዘኍ. 29፥7-11። 30በዚያን ዕለት ንጹሖች እንድትሆኑ የኃጢአት ማስተስረይ ይደረግላችኋል፤ ከዚያም ከኃጢአታችሁ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የነጻችሁ ትሆናላችሁ፤ 31ያም ዕለት እንደ ሰንበት የዕረፍት ቀን ይሁንላችሁ፤ በዚያን ቀን ራሳችሁን አዋርዱ ይህም የዘለዓለም ሥርዓት ነው። 32በአባቱ ምትክ ሊቀ ካህናት እንዲሆን ተለይቶ የሚሾመው ካህን የተቀደሰ የክህነት በፍታ ልብሱን ለብሶ ያስተሰርያል። 33እርሱም ለቅድስተ ቅዱሳኑ፥ ለመገናኛው ድንኳን፥ ለመሠዊያው፥ ለካህናቱና ለጉባኤው ያስተሰርያል። 34በዓመት አንድ ጊዜ የእስራኤላውያንን ኃጢአት ሁሉ ማስተስረይ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል።”
በዚህም ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ