ኦሪት ዘሌዋውያን 15
15
ርኲሰትን የሚያመጣ የሰውነት ፈሳሽ
1እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2“ማንም ሰው ከአባለ ዘሩ የሚወጣ ፈሳሽ ቢኖርበት፥ ያ ፈሳሽ ነገር ርኩስ ነው፤ 3ይህም ማለት ከአባለ ዘሩ ቢፈስ ወይም መፍሰሱን ቢያቆም ያው ርኩስ ነው፤ 4የሚተኛበትም ሆነ የሚቀመጥበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 5አልጋውን የሚነካም ሆነ፥ 6ወይም ሰውየው በተቀመጠበት በማንኛውም ነገር ላይ ሁሉ የሚቀመጥ ሰው ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሁን። 7ፈሳሽ ያለበትን ሰው የሚነካ ሁሉ ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ፥ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል። 8ፈሳሽ ያለበት ሰው ንጹሕ በሆነ ሰው ላይ ምራቁን ቢተፋበት፥ ያ ሰው ልብሱን አጥቦ ሰውነቱንም ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል። 9ፈሳሽ ያለበት ሰው የሚቀመጥበት ማንኛውም ኮርቻ የረከሰ ነው፤ 10ፈሳሽ ያለበት ሰው የተቀመጠበትን ዕቃ ሁሉ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ ሰውየው የተቀመጠበትን ማንኛውንም ዕቃ የያዘ ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ፥ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል። 11ፈሳሽ ያለበት ሰው እጁን ሳይታጠብ አንድን ሰው ቢነካ ያ ሰው ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱንም ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 12ፈሳሽ ያለበት ሰው የነካው ማንኛውም የሸክላ ዕቃ ቢኖር ይሰበር፤ ከእንጨት የተሠራ ዕቃ ሁሉ በውሃ ይታጠብ።
13“ፈሳሽ ያለበት ሰው ከፈሳሽ በሽታው በዳነ ጊዜ የነጻ እንዲሆን እስከ ሰባት ቀን ድረስ ይቈይ፤ ከዚያም በኋላ ልብሱን ይጠብ፤ በንጹሕ የምንጭ ውሃም ገላውን ይታጠብ፤ የነጻም ይሆናል። 14በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት ዋኖሶች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አምጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ለካህኑ ይስጥ፤ 15ካህኑም ከእነርሱ አንዱን ኃጢአት የሚሰረይበት መሥዋዕት፥ ሌላውንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፤ ስለ ፈሳሹ ነገር ያስተሰርይለታል።
16“ማንም ሰው ዘሩ ከአባለ ዘሩ ወጥቶ በሚፈስበት ጊዜ መላ ሰውነቱን ታጥቦ እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል። 17ዘሩ የፈሰሰበት ማንኛውም ልብስም ሆነ ቆዳ በውሃ ይታጠብ እርሱም እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ 18ሴትና ወንድ አብረው ተኝተው በሚነሡበት ጊዜ፥ ሁለቱም ሰውነታቸውን በውሃ ታጥበው እስከ ምሽት ድረስ የረከሱ ይሆናሉ።
19“ሴት የወር አበባ በምታይበት ጊዜ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ርኩስ ትሆናለች፤ እርስዋንም የሚነካ ማንም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 20በወር አበባዋ ጊዜ የምትቀመጥበትም ሆነ የምትተኛበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 21መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሁን፤ 22የምትቀመጥበትን ነገር የሚነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሁን፤ 23የምትተኛበትን ወይም የምትቀመጥበትን ነገር የነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 24በወር አበባዋ ወቅት ከእርስዋ ጋር የሚተኛ ወንድ ቢኖር እርሱም እንደ እርስዋ የረከሰ ይሆናል፤ ስለዚህም እስከ ሰባት ቀን ድረስ ርኩስ ሆኖ ይቈያል፤ እርሱ የሚተኛበትም አልጋ ርኩስ ይሆናል።
25“አንዲት ሴት ከወር አበባዋ ወቅት አልፎ ለብዙ ቀን የሚፈስ ወይም ከተመደበው የወር አበባዋ በኋላ ባለማቋረጥ የሚፈስ ደም ቢኖራት፥ ደሙ እስከሚቆምበት ጊዜ ድረስ ልክ በወር አበባዋ ጊዜ እንደ ነበረችበት ሁኔታ የረከሰች ትሆናለች። 26በዚህም ጊዜ የምትተኛበትም አልጋ ሆነ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 27እነርሱንም የሚነካ ሁሉ ስለሚረክስ ልብሱን አጥቦ፥ ሰውነቱን ታጥቦ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 28የደምዋም መፍሰስ ቢቆም እስከ ሰባት ቀን ትቈይ፤ ከዚያም በኋላ የነጻች ትሆናለች። 29በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት ዋኖሶች አምጥታ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለካህኑ ትስጥ፤ 30ካህኑም አንዱን ኃጢአት የሚሰረይበት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ ስለሚፈሰው ርኲሰት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል፥
31“በመካከላቸው ያለውን ማደሪያዬን በማርከስ እንዳይሞቱ እስራኤላውያንን ከርኲሰት ጠብቃቸው።”
32ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር ስለሚወጣበትና ስለሚያረክሰው ሰው የተሰጠ ደንብ ይህ ነው። 33እንዲሁም የወር አበባ በማየት ላይ ስላለች ሴት ወይም ወንድም ሆነ ሴት ፈሳሽ ነገር ከሰውነታቸው በሚወጣ ጊዜ ወይም ካልነጻች ሴት ጋር ስለሚተኛ ወንድ የተሰጠ መመሪያ ይህ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 15: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997