የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 14

14
ከሥጋ ደዌ በሽታ የመንጻት ሥርዓት
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2“አንድ ሰው ከሥጋ ደዌ በሽታ ከዳነ በኋላ የሚፈጸምለት የመንጻት ሥርዓት ይህ ነው፦ ንጹሕ መሆኑ በሚነገርለት ቀን ወደ ካህኑ እንዲቀርብ ይደረግ፤ #ማቴ. 8፥4፤ ማር. 1፥44፤ ሉቃ. 5፥14፤ 17፥14። 3ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጪ አውጥቶ ይመርምረው፤ በሽታው የተፈወሰ ከሆነ፥ 4ካህኑ ንጹሕ የሆኑ ሁለት ወፎችና የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቊራጭ፥ ቀይ የግምጃ ክርና የሂሶጵ ቅጠል ጨምሮ እንዲያመጣ ይዘዘው። 5ከዚህም በኋላ ካህኑ ከወፎቹ አንዱን ንጹሕ የምንጭ ውሃ ባለበት ጐድጓዳ የሸክላ ዕቃ ላይ እንዲታረድ ይዘዝ፤ 6ሌላውንም ወፍ ወስዶ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቊራጭ፥ ከቀዩ ከፈይ ክርና ከሂሶጱ ቅጠል ጋር በአንድነት ቀድሞ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይንከረው፤ 7ደሙንም ከሥጋ ደዌ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይርጭ፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅለታል፤ በሕይወት ያለውንም ወፍ ወደ ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል። 8ከበሽታው የነጻው ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ጠጒሩን ሁሉ ይላጫል፤ ሰውነቱንም ይታጠባል፤ ከዚያም በኋላ የነጻ ሆኖ ወደ ሰፈር ይገባል፤ ነገር ግን እስከ ሰባት ቀን ከራሱ ድንኳን ውጪ መቈየት አለበት። 9በሰባተኛውም ቀን እንደገና ራሱን፥ ጢሙን፥ ቅንድቡንና በሌላውም ሰውነት ላይ ያለውን ጠጒር ሁሉ ተላጭቶ ልብሱን በውሃ ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ፤ ከዚያም በኋላ የነጻ ይሆናል።
10“በስምንተኛውም ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና አንድ ዓመት የሆናት አንዲት ቄብ ያምጣ፤ ከዚህም ጋር በወይራ ዘይት የተለወሰ ሦስት ኪሎ ግራም ዱቄትና የሊትር አንድ ሦስተኛ የሆነ የወይራ ዘይት ያምጣ። 11ካህኑም ሰውየውን ካመጣቸው ከእነዚህ ሁሉ መባዎች ጋር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል፤ 12ከዚህም በኋላ ካህኑ ተባዕት ከሆኑት ከሁለቱ የበግ ጠቦቶች አንዱን የሊትር አንድ ሦስተኛ ከሆነው የወይራ ዘይት ጋር ወስዶ የበደል ስርየት መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል። ካህኑ ይህን በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርበዋል። 13ጠቦቱንም ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕትና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች በሚታረዱበት ቅዱስ ስፍራ ያርደዋል፤ ይህንንም የሚያደርግበት ምክንያት የበደል ዕዳ መሥዋዕት ልክ ለኃጢአት ስርየት እንደሚቀርበው መሥዋዕት የካህኑ ድርሻ ሆኖ ስለሚሰጥ ነው፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ ነው። 14ካህኑም ከጠቦቱ ደም ጥቂት ወስዶ የነጻ መሆኑን በሚያስታውቅለት ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንና የቀኝ እግሩን አውራ ጣቶች ይቀባ። 15ካህኑ ከወይራው ዘይት ጥቂት ወስዶ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፍስስ፤ 16በቀኝ እጁ ጫፍ እያጠቀሰ ከእርሱ ጥቂቱን በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። 17በእጁ መዳፍ ላይ ካለውም ዘይት ጥቂት ወስዶ የነጻ መሆኑን ለማስታወቅ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የቀኝ እጁንና የቀኝ እግሩን አውራ ጣቶች ይቀባ፤ 18በእጁ መዳፍ ላይ የተረፈውንም ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፍስሰው፤ በዚህም ዐይነት ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል።
19“ከዚህም በኋላ ካህኑ ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት በማቅረብ የመንጻትን ሥርዓት ይፈጽማል፤ ቀጥሎም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርበውን እንስሳ ያርዳል፤ 20እርሱንም ከእህል መባ ጋር በመሠዊያው ላይ አኑሮ ያቃጥለዋል፤ በዚህ ዐይነት ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ ያም ሰው ንጹሕ ይሆናል።
21“ሰውየው ይህን ሁሉ ለማምጣት የማይችል ድኻ ከሆነ፥ በመወዝወዝ ለኃጢአት ማስተስረያ ይሆንለት ዘንድ ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ ጠቦት ያምጣ፤ ከዚሁም ጋር በወይራ ዘይት የተለወሰ አንድ ኪሎ የላመ ዱቄት ለእህል መባ ያምጣ፤ እንዲሁም የሊትር ሲሶ የሆነ የወይራ ዘይት ያቅርብ፤ 22እንዲሁም ችሎታው በሚፈቅድለት መጠን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት ዋኖሶች፥ አንዱን ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያመጣል፤ 23የመንጻትን ሥርዓት በሚፈጽምበት በስምንተኛው ቀን እነዚህን ሁሉ አምጥቶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ለካህኑ ይሰጣል። 24ካህኑም የበጉን ጠቦትና የወይራውን ዘይት ተቀብሎ በእግዚአብሔር ፊት የመወዝወዝ መሥዋዕት አድርጎ ያቀርበዋል። 25ካህኑ ይህን ለበደል ስርየት መሥዋዕት የቀረበውን የበግ ጠቦት ይረድ፤ ከደሙም ትንሽ ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የቀኝ እጁንና የቀኝ እግሩን አውራ ጣቶች ይቀባ፤ 26ካህኑ ከዘይቱ ትንሽ በግራ እጁ መዳፍ ላይ ያፈሳል፤ 27በቀኝ እጁ ጣት እያጠቀሰ ከዚያ ጥቂቱን በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ 28በእጁ ካለው ጥቂት ዘይት ወስዶ በበደል ስርየት መሥዋዕቱ ደም እንዳደረገው በሚነጻው ሰው በቀኝ ጆሮ የቀኝ እጁ አውራ ጣት መዳፍ ላይና በቀኝ እግሩ አውራ ጣት ላይ ያስነካዋል። 29በእግዚአብሔር ፊት ለማስተሰረይ ካህኑ በእጁ ላይ የተረፈውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፈስሳል። 30የሚነጻውም ሰው ከዋኖስ ወይም ከርግብ እርሱ የሚችለውን አንዱን ያቅርብ፤ 31አንዱን ለኃጢአት መስዋዕት ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፥ ከዚህም ጋር የእህል መባ ያቅርብ፤ ካህኑም ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተስርይለት። 32ከሥጋ ደዌ በሽታ ለመንጻት የተመደበውን መሥዋዕት በድኽነቱ ምክንያት ማቅረብ ለማይችል ሰው የሚፈጸመው ሥርዓት ይህ ነው።”
በቤት ላይ ስለሚታይ ሻጋታ መንጻት
33እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 34“እኔ ወደምሰጣችሁ ወደ ከነዓን ምድር በምትገቡበት ጊዜ በዚያ አገር በሚገኝ በአንድ ቤት ውስጥ ሻጋታ ሳሠራጭ፥ 35የሻጋታው ምልክት በራሱ ቤት ውስጥ መኖሩን የተገነዘበ ማንም ሰው ሄዶ ለካህኑ ‘በቤቴ ሻጋታ መሰል ነገር አለ’ ብሎ ይንገር፤ 36ካህኑም ሄዶ የሻጋታውን ዐይነት ከመመርመሩ በፊት በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዲወጣ ትእዛዝ ይስጥ፤ አለበለዚያ በቤቱ ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ካህኑ ወደ ቤት ገብቶ ይመርምር፤ 37የሻጋታውን ዐይነት በሚመረምርበት ጊዜ ግድግዳውን እየቦረቦሩ የሚበሉት አረንጓዴ ወይም ቀይ ዐይነት ዝንጒርጒር ምልክቶች ቢታዩበት፥ 38ከዚያ ቤት ወጥቶ ለሰባት ቀን እንዲዘጋ ያድርገው። 39በሰባተኛው ቀን ተመልሶ መጥቶ እንደገና ይመርምረው፤ የሻጋታው ምልክት ተስፋፍቶ ቢገኝ፥ 40የሻጋታው ምልክት ያለባቸው ድንጋዮች ተፈልፍለው ወጥተው ከከተማው ውጪ በሚገኘው በረከሰ ጒድፍ ማከማቻ እንዲጣሉ ይዘዝ። 41ከዚያም በኋላ የውስጡ ግድግዳ ሁሉ እንዲፋቅና ምርጊቱ ሁሉ ተቀርፎ ከከተማ ውጪ በሚገኘው በረከሰ ጒድፍ መጣያ እንዲጣል ያድርግ። 42ከዚህም በኋላ በእነዚያ በቀድሞዎቹ ድንጋዮች ምትክ ሌሎች አዳዲስ ድንጋዮች ተገንብተው ቤቱ በአዲስ ጭቃ ይመረግ።
43“ድንጋዮቹ ተወግደው፥ ግድግዳው ተፍቆ፥ ምርጊቱም ተነሥቶ ቤቱ በዐዲስ ጭቃ ተመርጎ ከታደሰ በኋላ የሻጋታው ምልክት እንደገና ቢታይ፥ 44ካህኑ ሄዶ ይመልከተው፤ የሻጋታው ዐይነት የሚስፋፋና የማይለቅ ሻጋታ ስለ ሆነ ቤቱ ርኩስ ነው። 45ስለዚህ መፍረስ አለበት፤ ድንጋዮቹ እንጨቱና ምርጊቱ ሁሉ ከከተማ ውጪ ተወስዶ በረከሰ ጒድፍ ማከማቻ ስፍራ ይጣል፤ 46ከተዘጋ በኋላ ወደዚያ ቤት የገባ ሰው ሁሉ እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ 47በዚያ ቤት ውስጥ የተኛ ወይም ምግብ የተመገበ ቢኖር ልብሱን ይጠብ።
48“ቤቱ እንደገና ታድሶ ከተለሰነ በኋላ ካህኑ መጥቶ በሚመለከትበት ጊዜ ሻጋታው የመስፋፋት ምልክት የማያሳይ ሆኖ ከተገኘ ግን የሻጋታው ምልክት ጨርሶ ስለ ጠፋ ያ ቤት ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። 49ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ ጥቂት የሊባኖስ ዛፍ እንጨት፥ የቀይ ከፈይ ክርና የሂሶጵ ቅጠል ይውሰድ። 50ከወፎቹ አንዱን ንጹሕ የምንጭ ውሃ ባለበት የሸክላ ዕቃ ላይ ይረደው፤ 51ከዚያም በኋላ የሊባኖሱን ዛፍ እንጨት፥ የሂሶጱን ቅጠል፥ የቀዩን ከፈይ ክርና በሕይወት ያለውን ወፍ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውሃ ውስጥ ይንከረው፤ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይርጨው። 52በዚህም ዐይነት ካህኑ ያንን ቤት በወፉ ደም፥ በንጹሑ ውሃ፥ ሕይወት ባለው ወፍ፥ በሊባኖሱ ዛፍ እንጨት በሂሶጱ ቅጠልና በቀዩ የከፈይ ክር እንዲነጻ ያደርገዋል። 53ከዚያም በኋላ በሕይወት ያለውን ወፍ ከከተማ ውጪ ወደ ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል፤ በዚህም ዐይነት ለቤቱ የማንጻት ሥርዓት ይፈጽማል፤ ቤቱም ንጹሕ ይሆናል።
54“እነዚህም ለማንኛውም ተላላፊ ለሆነ የሥጋ ደዌ በሽታ፥ ለእከክ የሥርዓት መመሪያዎች ናቸው። 55በልብስና በቤት ላይ የሚወጣ ሻጋታን፥ 56እባጭን፥ ሽፍታንና ቋቊቻን ለማንጻት የወጡ ሕጎች ናቸው። 57እነዚህ ሥርዓቶች አንድን ነገር ንጹሕ መሆኑን ወይም አለመሆኑን የሚወስኑ ናቸው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ