ኦሪት ዘሌዋውያን 13

13
ስለ ቆዳ በሽታ የተሰጠ መመሪያ
1እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2“ማንም ሰው በሰውነቱ ላይ እባጭ ወይም ሽፍታ ወይም ቋቊቻ ቢታይና በገላው ላይ የሥጋ ደዌ ቢመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ከልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። 3ካህኑም ቊስሉን ይመርምር፤ በዚያም ቊስል ላይ ያለው ጠጒር ወደ ነጭነት ቢለወጥ፥ ቊስሉም በዙሪያው ካለው ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ቢገኝ፥ እርሱ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው፤ ካህኑም ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። 4ነገር ግን ቊስሉ ነጭ ሆኖ በዙሪያው ካለው ቆዳ ይልቅ ጐድጐድ ብሎ ባይገኝና ጠጒሩም ወደ ነጭነት ባይለወጥ፥ ካህኑ ያን ሰው ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ፤ 5ካህኑ በሰባተኛው ቀን እንደገና ይመርምረው፤ በሚመረምረውም ጊዜ ቊስሉ ምንም ለውጥ ሳያሳይ እንደ ነበረ ሳይስፋፋ ቢያገኘው፥ አሁንም ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። 6ካህኑም እንደገና በሰባተኛው ቀን ይመርምረው፤ በሚመረምረውም ጊዜ ቊስሉ በመስፋፋት ፈንታ ከስሞ ከተገኘ፥ ቊስሉ እከክ ብቻ መሆኑን ገልጦ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ያም ሰው ስለ መንጻቱ ልብሱን ይጠብ፤ 7ነገር ግን ካህኑ መርምሮ ንጹሕ መሆኑን ካስታወቀለት በኋላ፥ ቊስሉ ተስፋፍቶ ቢገኝ ያ ሰው እንደገና በካህኑ ፊት ይቅረብ፤ 8ካህኑም እንደገና ይመርምረው፤ ቊስሉም ተስፋፍቶ ከተገኘ የሥጋ ደዌ በሽታ ስለ ሆነ የረከሰ የሥጋ ደዌ በሽተኛ መሆኑን ያስታውቅ።
9“ማንም ሰው የሥጋ ደዌ በሽታ ቢይዘው ወደ ካህኑ ያምጡት፤ 10ካህኑም ይመርምረው፤ በቈዳው ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጒሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ 11እርሱ በቈዳው ላይ የቈየ የሥጋ ደዌ ስለ ሆነ ካህኑ ሕመምተኛው የረከሰ መሆኑን ያስታውቅ፤ የረከሰ መሆኑ በግልጥ ስለ ታወቀ እንደዚህ ያለው ሰው በቤት ውስጥ ተዘግቶበት መቈየት አያስፈልገውም። 12እንደ ካህኑ አስተያየት የሥጋ ደዌው በሽታ ሰውየውን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጠጒሩ የሸፈነው ከሆነ፥ 13ካህኑ እንደገና ይመርምረው፤ መላ ሰውነቱን ሸፍኖት ቢያገኘው፥ ቆዳው በሙሉ ወደ ነጭነት ከተለወጠ የነጻ ስለሚሆን ካህኑ ያ ሰው የነጻ መሆኑን ያስታውቅ፤ 14ነገር ግን በሥጋው ላይ የሚያዥ ቊስል ቢታይበት የረከሰ ይሆናል። 15ካህኑም እንደገና መርምሮት የሚያዥ ቊስል ቢያገኝ፥ ያ ሰው የረከሰ መሆኑን ያስታውቅ፤ የሚያዥ፥ የሥጋ ደዌ በሽታ ስለ ሆነ ያ ሰው ርኩስ ነው። 16ቊስሉ ቢፈወስና እንደገና ወደ ነጭነት ቢለወጥ ግን እንደገና ወደ ካህኑ ይሄዳል፤ 17ካህኑም እንደገና መርምሮት ቊስሉ ወደነጭነት ተለውጦ ከተገኘ ያ ሰው የነጻ ይሆናል፤ ካህኑም ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያሳውቅለታል።
18“አንድ ሰው የዳነ እባጭ ቢኖርበትና፥ 19ዘግየት ብሎም ቊስሉ ባለበት ቦታ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ዐይነት ቊስል ቢወጣበት ወደ ካህኑ ይሂድ፤ 20ካህኑም መርምሮት ቊስሉ ያለበት ቦታ ከሌላው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ቢገኝና በቈዳው ላይ ያለውም ጠጒር ወደ ነጭነት ቢለወጥ እርሱም በእባጭ የተጀመረ የሥጋ ደዌ በሽታ ስለ ሆነ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። 21ነገር ግን ካህኑ መርምሮት በቈዳው ላይ ያለው ጠጒር ወደ ነጭነት ባይለወጥና ከሌላው የሰውነቱ ቆዳ ይበልጥ ጐድጒዶ ባይገኝ፥ የቀለሙ ልዩነት ስለ ተቀነሰ ካህኑ ያን ሰው ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ፤ 22ቊስሉ ያለበትም ቦታ እየሰፋ መሄዱ ከታወቀ፥ ያ የሥጋ ደዌ ስለ ሆነ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ። 23ነገር ግን ቋቁቻው ምንም ለውጥ ሳያደርግና ሳይስፋፋ ቢገኝ የእባጭ ጠባሳ መሆኑ ታውቆ መንጻቱን ካህኑ ያስታውቅለት።
24“የእሳት ቃጠሎ የደረሰበት ሰው ቢኖርና የተቃጠለ ሥጋው ቢነጣ ወይም ቀላ ያለ ነጭ ሆኖ ቢገኝ፥ 25ካህኑ ይመርምረው፤ ቊስሉ ባለበት ስፍራ የበቀለው ጠጒር ነጭ ቢሆንና ያም ስፍራ በዙሪያው ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ከተገኘ፥ ከእሳት ቃጠሎ የመጣ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው፤ ስለዚህም ካህኑ ያ ሰው የረከሰ መሆኑን ያስታውቅ። ይህም የሥጋ ደዌ ነው። 26ነገር ግን በእርሱ ላይ የበቀለው ጠጒር ወደ ነጭነት ካልተለወጠ በዙሪያውም ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ካልተገኘና የቀለም መለዋወጥ ብቻ ሆኖ ከተገኘ፥ ካህኑ ያ ሰው ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። 27በሰባተኛውም ቀን ካህኑ እንደገና ይመርምረው፤ ቊስሉ ተስፋፍቶ ከተገኘ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው፤ ስለዚህም ያ ሰው የረከሰ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። 28ነገር ግን ቊስሉ ያለበት ስፍራ ምንም ለውጥ ሳያሳይና ሳይስፋፋ የቀለም መለዋወጥ ብቻ ሆኖ ከተገኘ በእሳት ቃጠሎ ምክንያት የመጣ ጠባሳ ስለ ሆነ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅለት።
29“አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት በራስ ወይም በአገጭ ላይ ቊስል ቢወጣበት ወይም ቢወጣባት፥ 30ካህኑ ቊስሉን ይመርምር፤ በዙሪያው ካለው የሰውነት ቆዳ ይልቅ ወደ ውስጥ ጐድጒዶ በእርሱ ላይ የበቀለውም ጠጒር ወደ ቢጫነት በመለወጥ ስስ ሆኖ ከተገኘ የራስ ወይም የአገጭ ቈረቈር ወይም የሥጋ ደዌ ስለ ሆነ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። 31ነገር ግን ካህኑ ሲመረምረው የሚያሳክከው ቊስል በዙሪያው ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ የማይታይ ከሆነና በላዩ ላይ ያለው ጠጒር ጤናማ ካልሆነ፥ በሚያሳክከው ቊስል ምክንያት ያ ሰው በቤት ውስጥ ተዘግቶበት ለሰባት ቀን እንዲቈይ ያድርግ፤ 32በሰባተኛው ቀን እንደገና ካህኑ ይመርምረው፤ ቊስሉ እየተስፋፋ ካልሄደ፥ ወደ ቢጫነት የተለወጠ ጠጒርም ከሌለና በዙሪያው ካለው ከሌላው ሰውነቱ ቆዳ ይልቅ ጐድጒዶ ካልተገኘ፥ 33ያ ሰው ቊስሉን ሳይሆን በቊስሉ ዙሪያ ያለውን ጠጒር ይላጭ፤ ካህኑም እንደገና በሚያሳክከው በሽታ ምክንያት ለሰባት ቀን በቤት ውስጥ ተዘግቶበት እንዲቈይ ያድርግ። 34በሰባተኛውም ቀን እንደገና ካህኑ ቊስሉን ይመርምር፤ ቊስሉ በመስፋፋት ላይ ካልተገኘና በዙሪያውም ካለው የሰውነቱ ቆዳ ይልቅ የጐደጐደ ካልሆነ ያ ሰው የነጻ መሆኑን ያስታውቅለት፤ ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 35ሆኖም ንጹሕ መሆኑ ከተገለጠ በኋላ ቊስሉ እያመረቀዘ ተስፋፍቶ ቢገኝ፥ 36ካህኑ እንደገና ይመርምረው፤ ቊስሉ በእርግጥ ተስፋፍቶ ከሆነ ሰውየው የረከሰ በመሆኑ ወደ ቢጫነት የተለወጠ ጠጒር መኖርና አለመኖሩ አስፈላጊ አይደለም። 37ነገር ግን በካህኑ አመለካከት ቊስሉ ካልተስፋፋና ጤናማ ጠጒርም በቅሎበት ከተገኘ፥ ቊስሉ የተፈወሰ ስለ ሆነ፥ ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅለት።
38“አንድ ሰው ወይም አንዲት ሴት በቈዳ ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢወጣባቸው፥ 39ካህኑ ያን ሰው ይመርምር፤ ቋቁቻ ያለበትም ስፍራ ደብዘዝ ያለ ነጭ ቢሆን ብዙ ጒዳት የማያመጣ በቈዳ ላይ የሚታይ ሽፍታ ስለ ሆነ ያ ሰው ንጹሕ ነው። 40አንድ ሰው ጠጒሩ ከራሱ ላይ ቢመለጥ ራሰ በራ ነው እንጂ ንጹሕ ነው። 41አንድ ሰው ከግምባሩና ከዐናቱ ጠጒር ቢመለጥ ራሰ በራ ነው እንጂ ንጹሕ ነው። 42ነገር ግን በራ በሆነው ራስ ወይም ግንባር ላይ ወደ ቀይነት ያደላ ነጭ ቊስል ቢታይበት እርሱ የሥጋ ደዌ በሽታ ነው። 43ካህኑም መርምሮ በበራ ራሱ ወይም በበራ ግንባሩ ላይ በሰውነት ላይ የሚወጣ የሥጋ ደዌ በሽታ ዐይነት ቀላ ያለ የእባጭ ቊስል ቢያገኝ፥ 44እርሱ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሰው በመሆኑ የረከሰ ነውና የረከሰ መሆኑን ካህኑ ያውጅ፤ በሽታውም በራሱ ላይ ነው።
45“በዚህ ዐይነት የሥጋ ደዌ በሽታ ያለበት ሰው የተቀዳደደ ልብስ ይልበስ፤ ጠጒሩን አያበጥር፥ ከንፈሩን ይሸፍን፤ ከዚያም በኋላ ‘እኔ የረከስኩ ነኝ! የረከስኩ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። 46ይህም በሽታ እስካለበት ድረስ ያ ሰው የረከሰ ይሆናል። ስለዚህም ከኅብረተሰብ ተለይቶ መኖሪያው ከሰፈር ውጪ ይሆናል።
በልብስ ላይ የሚታይ ሻጋታ
47“ሻጋታ ነገር ከበግ ጠጒር ወይም ከበፍታ በተሠራ ልብስ ቢወጣ፥ 48በድሩም ሆነ በማጉ ላይ፥ እንዲሁም ከሱፍ ወይም ከቈዳ ወይም ከቈዳ በተሠራ ልብስ ላይ ቢታይና፥ 49መልኩም ወደ አረንጓዴነት ወይም ወደ ቀይነት ቢያደላ፥ የሚተላለፍ ሻጋታ ስለ ሆነ ለካህኑ ይታይ። 50ካህኑም ይመርምረውና እነዚህ ሁሉ የልብስ ዐይነቶች እስከ ሰባት ቀን ድረስ በአንድ ክፍል ተዘግቶባቸው ይቈዩ። 51በሰባተኛውም ቀን እንደገና በሚመረምረው ጊዜ ሻጋታው ነገር ተስፋፍቶ ከታየበት ያ የታየው አጥፊ ሻጋታ ስለ ሆነ፥ የዚያ ዐይነቱ ልብስ ሁሉ ርኩስ ነው፤ 52ይህም አጥፊ ሻጋታ እየሰፋ የሚሄድ ስለ ሆነ በእሳት ይቃጠል።
53“ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ሻጋታው ተስፋፍቶ ካልተገኘ፥ 54ልብሱ በውሃ ታጥቦ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ለብቻ እንዲቀመጥ ያድርግ። 55ከዚህም በኋላ እንደገና ይመርምረው፤ ምንም እንኳ በማፋግ ባይስፋፋ የሻጋታው ቀለም ካልተለወጠ በቀር፥ አሁንም ርኩስ ነው፤ ከፊትም ሆነ ከኋላ ሻጋታ ወይም የመበስበስ መልክ የሚታይበት ያ ልብስ ይቃጠል። 56ነገር ግን ካህኑ እንደገና በሚመረምርበት ጊዜ ሻጋታው ተቀንሶ ካገኘው፥ የመሻገት ምልክት ያለበትን ስፍራ ብቻ ከጨርቅ ወይም ከቈዳ ልብስ ቀዶ ያውጣው። 57ሻጋታው እንደገና ቢታይ እርሱ እየተስፋፋ የሚሄድ ስለ ሆነ፥ ባለ ንብረቱ ያቃጥለው። 58ልብሱ በሚታጠብበት ጊዜ የሻጋታው ምልክት ቢጠፋ እንደገና ይጠበው፤ ከዚያም በኋላ የነጻ ይሆናል።”
59ይህ እንግዲህ ከበፍታም ሆነ ከበግ ጠጒር፥ ወይም ከቈዳ በተሠራ ልብስ ላይ በድሩም ሆነ በማጉ በሻጋታ አማካይነት የሚተላለፍ ምልክት ተመርምሮ የሚታወቅበት የሥርዓት መመሪያ ነው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ