እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ በሰባተኛው ዓመት ምንም ሳታርሱ ምድሪቱን በማሳረፍ እግዚአብሔርን ታከብራላችሁ። በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘርህን ትዘራለህ፤ የወይን ተክልህን ትገርዛለህ፤ እህልህን ትሰበስባለህ። ሰባተኛው ዓመት ግን ለእኔ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሆኖ ምድሪቱ ፍጹም ዕረፍት የምታደርግበት ጊዜ ነው። በዚህ ዓመት ዘርህን አትዘራም፤ የወይን ተክልህንም አትገርዝም። ሳይዘራ ገቦ ሆኖ የበቀለውንም እህል አትሰበስብም፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬውን አትሰበስብም፤ ያ ዓመት ምድሪቱ ፍጹም ዕረፍት የምታደርግበት ጊዜ ነው። በምድር ሰንበት ዓመት የሚበቅለው ሰብል ሁሉ ለአንተ፥ ለወንድ አገልጋይህ፥ ለሴት አገልጋይህ፥ ለቅጥረኛህ፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ጊዜያዊ መጻተኛ ምግብ ይሆናል። ለእንስሶችህና በምድርህ ለሚገኙ አራዊት የሚበቃ ምግብ ታገኛለህ፤ ምድሪቱ የምታስገኘው ነገር ሁሉ ሊበላ ይችላል። “ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመት ቊጠር፥ ጠቅላላ ድምሩም አርባ ዘጠኝ ዓመት ይሆናል፤ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን በሚውለው የኃጢአት ስርየት ቀን በመላይቱ ምድር የእምቢልታ ድምፅ የሚያሰማ ሰው ትልካለህ፤ በዚህም ሁኔታ ኀምሳኛውን ዓመት ለይታችሁ በምድሪቱ ለሚኖሩት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ ከዚያ በፊት የተሸጠ ማናቸውም መሬት ለባለቤቱ ወይም ለዘሩ ይመለሳል፤ ባርያም ሆኖ ለማገልገል የተሸጠ ሰው ወደ ቤተሰቡ ይመለሳል። በዚህም ዓመት ዘራችሁን አትዘሩም፤ ሳይዘራ ገቦ ሆኖ የበቀለውን እህላችሁን ወይም ካልተገረዘ የወይን ሐረግ ፍሬውን አትሰበስቡም። ዓመቱ በሙሉ ለእናንተ የተቀደሰ ይሆናል፤ እርሻዎቻችሁ ማንም ሳይንከባከባቸው ራሳቸው የሚያስገኙትን ምግብ ብቻ ትበላላችሁ። “ከዚያ በፊት የተሸጠ መሬት ሁሉ በዚሁ ዓመት ለባለቤቱ ይመለስለታል፤ ስለዚህ ወገንህ ለሆነው እስራኤላዊ መሬት ብትሸጥ ወይም ከእርሱ መሬት ብትገዛ የግፍ ሥራ አትሥራ፤ ዋጋውም የሚተመነው ተከታዩ የንብረት መመለሻ ዓመት ከመግባቱ በፊት፥ ምድሪቱ ልታስገኝ በምትችለው ሰብል መጠን ይሆናል። ዓመታቱ ብዙ ቢሆኑ፥ ዋጋው ከፍ ይላል፤ ዓመታቱ ጥቂቶች ከሆኑ ዋጋው ዝቅ ይላል፤ የሚሸጥበት ዋጋ የሚተመነው ምድሪቱ በምታስገኘው ሰብል መጠን ነው፤ አንዱ እስራኤላዊ በሌላው እስራኤላዊ ላይ ግፍ አይሥራ፤ አምላካችሁን ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “በምድሪቱ ላይ በሰላም ትኖሩ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት ሁሉ አክብሩ፤ ምድሪቱም ራስዋ በቂ ሰብል ስለምታስገኝ የምትበሉትን ሁሉ አግኝታችሁ በምቾትና በሰላም ትኖራላችሁ። “ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ዘር ካልዘራንና ሰብል ካልሰበሰብን ምን እንበላለን ብላችሁ ብትጠይቁ፤ በስድስተኛው ዓመት እኔ ምድሪቱን እባርካታለሁ፤ ስለዚህም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ሰብል ታስገኛለች፤ በስምንተኛው ዓመት እንኳ ዘራችሁን ስትዘሩ የምትመገቡት ቀድሞ የሰበሰባችሁትን መከር ነው፤ ይህንኑ መከር የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስከምትሰበስቡ ድረስ ትበላላችሁ። “ምድሪቱ ለዘለቄታ መሸጥ አይገባትም፤ እርስዋ የእኔ እንጂ የእናንተ አይደለችም፤ እናንተ እንደ መጻተኛ ሆናችሁ እንድትጠቀሙባት ብቻ ፈቅጃለሁ።
ኦሪት ዘሌዋውያን 25 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 25:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos