የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘሌዋውያን 25:1-23

ዘሌዋውያን 25:1-23 NASV

እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ምድሪቱ ራሷ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ሰንበት ታክብር። ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ ስድስት ዓመት ወይንህን ግረዝ፤ ፍሬውንም ሰብስብ። በሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ታድርግ፤ ይህም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነው። በዕርሻህ ላይ አትዝራ፤ ወይንህንም አትግረዝ። ሳይዘራ የበቀለውን አትጨደው፤ ካልተገረዘው የወይን ተክልህ ፍሬ አትሰብስብ። ምድሪቱ የአንድ ዓመት ዕረፍት ታድርግ። ምድሪቱም በሰንበት ጊዜዋ የምታስገኘው ማንኛውም ፍሬ ለአንተ፣ ለወንድ ባሪያህ፣ ለሴት ባሪያህ፣ ለቅጥር ሠራተኛህና ከአንተ ጋር ለሚኖር መጻተኛ ምግብ ይሁን፤ እንዲሁም ለቤት እንስሶችህና በምድርህ ለሚኖሩ የዱር አራዊት ምድሪቱ የምታበቅለው ሁሉ መኖ ይሁን። “ ‘ሰባት የሰንበት ዓመታት ማለትም ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመታትን ቍጠር፤ ሰባቱ የሰንበት ዓመታትም አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ። ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን፣ መለከት ይነፋ፤ በማስተስረያ ቀንም በምድራችሁ ሁሉ መለከት ንፉ። አምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱ ሁሉ ላሉ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻነት ዐውጁ፤ ይህም ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደ ቤተ ሰቡ ርስት፣ ወደ ወገኑም ይመለስ። የአምሳኛው ዓመት ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ አትዝሩ፤ ሳትዘሩት የበቀለውን አትጨዱ፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬ አትሰብስቡ። ኢዮቤልዩ ስለሆነ ለእናንተ የተቀደሰ ይሁን፤ ሳትዘሩት በሜዳ የበቀለውን ብሉ። “ ‘በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለስ። “ ‘ከወገንህ ከአንዱ መሬት ብትገዛ ወይም ብትሸጥለት፣ አንዱ ሌላውን አያታልል። ከኢዮቤልዩ በኋላ ያሉትን ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ከወገንህ ትገዛለህ፤ እርሱም የቀሩትን የመከር ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ይሸጥልሃል። የዓመቱ ቍጥር ከበዛ ዋጋውን ጨምር፤ የዓመቱ ቍጥር ካነሰም፣ ዋጋውን ቀንስ፤ ምክንያቱም የሚሸጥልህ የዓመቱን የምርት መጠን ነውና። አንዱ ሌላውን አያታልል፤ አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ። “ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤ ሕጌን በጥንቃቄ አድርጉ፤ በምድሪቱም በሰላም ትኖራላችሁ። ምድሪቱ ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በዚያም በሰላም ትኖራላችሁ። እናንተም፣ “ካልዘራን ወይም ሰብላችንን ካልሰበሰብን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?” በማለት ትጠይቁ ይሆናል። በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እሰድድላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ፍሬ ትሰጣለች። በስምንተኛው ዓመት በምትዘሩበት ጊዜ፣ የምትበሉት ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ሰብል ይሆናል፤ የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስክትሰበስቡ ድረስ ከዚሁ እህል ትበላላችሁ። “ ‘መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ።