ኦሪት ዘሌዋውያን 25
25
ሰባተኛው ዓመት
1ጌታም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለጌታ ሰንበት ታድርግ። 3#ዘፀ. 23፥10-11።ስድስት ዓመት እርሻህን ትዘራለህ፥ ስድስት ዓመትም የወይን ተክልህን ግረዝ ፍሬዋንም ሰብስብ። 4#ዘሌ. 26፥34፤ 1መቃ. 6፥49።በሰባተኛው ዓመት ግን ለጌታ ሰንበት፥ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ይሁን፤ በእርሻህ ላይ አትዝራ፥ የወይን ተክልህንም አትግረዝ። 5በመከርህ ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለውን አትሰብስብ፥ ያልተገረዘውን የወይንህን ተክል ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን። 6የምድሪቱ ሰንበት ለእናንተ፥ ለአንተም፥ ለወንድ ባርያህም፥ ለሴት ባርያህም፥ ተቀጥሮ ለሚያገለግልህም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ትሰጣችኋለች። 7እንዲሁም ለእንስሶችህ፥ በምድርህም ላሉት አራዊት እርሷ የምትሰጠው ሁሉ ለመኖ ይሆናል።
የኢዮቤልዩ ዓመት
8“ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመት አድርገህ በዓመታት ውስጥ ያሉትን ሰንበታት ቁጠር፤ የዓመታቱም የሰንበታት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ይሆኑልሃል። 9#ዘሌ. 16፥29።ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የቀንደ መለከትን ድምፅ ከፍ አድርገህ ታሰማለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ የቀንደ መለከትን ድምፅ ታሰማላችሁ። 10#ዘኍ. 36፥4፤ ኢሳ. 61፥2፤ ኤር. 34፥8-22፤ ሕዝ. 46፥17፤ ሉቃ. 4፥19።ኀምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእንናተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ ከእናንተም እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለሳል። 11ያ ኀምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ዓመት ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ እንዲሁም ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለውን አትሰብስቡ፥ ያልተገረዘውን የወይን ተክል ፍሬ አታከማቹ። 12ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ ምድሪቱ ራስዋ የምትሰጠውን ፍሬ ትበላላችሁ።
13“በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለሳል። 14ለባልንጀራህም መሬት ብትሸጥ፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ አንዱ ሌላውን አያታልል። 15#ዘሌ. 27፥18፤ 23።ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል። 16እርሱ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃልና ዓመታቱ ብዙ በሆኑ ቍጥር ዋጋውን ከፍ ታደርጋለህ፥ ዓመታቱ ግን ባነሱ ቍጥር ዋጋውን ታሳንሳለህ። 17እኔም ጌታ አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
18“ሥርዓቶቼን አድርጉ፥ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። 19#ዘሌ. 26፥5-6።ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርሷም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። 20#ማቴ. 6፥25፤31-34፤ ሉቃ. 12፥22፤29።ዳሩ ግን እናንተ፦ ‘ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ፥ 21እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በእናንተ ላይ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። 22#ዘሌ. 26፥10።በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ፤ የእርሷ ፍሬ እስከሚገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ። 23ምድሪቱም የእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድሪቱን ለዘለዓለም አትሽጧት። 24በርስት በያዛችሁት ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ ታደርጋላችሁ።
25 #
ሩት 2፥20፤ 4፥4፤ ኤር. 32፥7-8። “ወንድምህም ቢደኸይ ከርስቱም ቢሸጥ፥ የቅርብ ዘመዱ የሆነ ሰው መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል። 26የሚቤዠውም ሰው ባይኖረው፥ እርሱም ቢበለጥግ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥ 27#ዘሌ. 27፥18፤ 23።እርሱም እስከ ሸጠበት ጊዜ ያሉትን ዓመታት ያሰላል፥ ከዚያም የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልሳል፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለሳል። 28#ዘሌ. 27፥24።ለማስመለስ ግን በቂ ገንዘብ ባያገኝ፥ ሽያጩ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ በገዛው ሰው እጅ ይሆናል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ነፃ ይወጣል፥ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለሳል።
29“ማናቸውም ሰው ቅጥር ባለው ከተማ ውስጥ ያለ መኖሪያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት የመቤዠት መብት አለውና። 30አንድ ዓመትም እስከሚፈጸም ባለው ጊዜ ሁሉ ባይቤዠው፥ ቅጥር ባለው ከተማ ውስጥ ያለው ቤት ለገዛው ሰው ለልጅ ልጁ ለዘለዓለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩም ከእርሱ ነፃ አይወጣም። 31ነገር ግን በዙሪያቸው ቅጥሮች በሌላቸው መንደሮች ያሉ ቤቶች እንደ እርሻ መሬቶች ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፥ በኢዮቤልዩም ነፃ ይወጣሉ። 32#ዘኍ. 35፥1-8።ነገር ግን ለሌዋውያን ርስታቸው በሆኑት በሌዋውያን ከተሞች ውስጥ ያሉትን ቤቶች ለዘለዓለም የመቤዠት መብት አላቸው። 33ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቤት ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል በሌዋውያን ከተሞች ያሉ ቤቶች ለሌዋውያን ርስቶቻቸው ናቸውና በርስታቸው ከተማ ውስጥ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ይመለሳል። 34#ዘኍ. 35፥3።በከተማቸውም ዙሪያ ያለው መሰማሪያ የዘለዓለም ርስታቸው ነውና አይሸጥም።
35 #
ዘዳ. 15፥7፤8። “ወንድምህ ቢደኸይ፥ እርሱም በአንተ ዘንድ ራሱን መቻል ቢያቅተው፥ አጽናው፤ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛም ከአንተ ጋር ይኑር። 36ወንድምህ ከአንተ ጋር እንዲኖር ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። 37#ዘፀ. 22፥24፤ ዘዳ. 23፥20።ብርህን በወለድ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት። 38የከነዓንን ምድር እንድሰጣችሁ፥ አምላክም እንድሆናችሁ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።
39 #
ዘፀ. 21፥2-11፤ ዘዳ. 15፥12-18፤ 1ነገ. 9፥22፤ ኤር. 34፥8-22። “በአንተም ዘንድ ያለው ወንድምህ ቢደኸይ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባርያ እንዲያገለግል አታድርገው። 40ይልቁንም እርሱ እንደ ተቀጣሪ አገልጋይ እና እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩም ዓመት ያገልግልህ። 41ከዚያም በኋላ እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ነፃ ይወጣል፥ ወደ ወገኖቹም ወደ አባቱም ርስት ይመለሳል። 42ስለዚህ ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ባርያዎቼ ናቸውና እንደ ባርያዎች አይሸጡ። 43በጽኑ እጅ አትግዛው፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። 44#ዘዳ. 21፥10-14።ወንድ ባርያና ሴት ባርያ እንዲኖራችሁ ብትፈልጉ ግን በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብ መካከል ወንድና ሴት ባርያዎች ትገዛላችሁ። 45እንዲሁም በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት መጻተኞች፥ በምድራችሁም ውስጥ ከወለዱአቸው ከእናንተ ጋር ካሉት ከቤተሰቦቻቸው ውስጥ ባርያዎችን ትገዛላችሁ፤ ርስትም ይሆኑላችኋል። 46#ኢሳ. 14፥1-2።ከእናንተም በኋላ ልጆቻችሁ ለዘለዓለም እንዲወርሱአቸው ተዉአቸው፤ እነርሱን ባርያዎች ታደርጋላችሁ፥ ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ወንድሞቻችሁ ናቸውና አንዱ ሌላውን በጽኑ እጅ አይግዛው።
47“በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው ወይም በአንተ ዘንድ ለተቀመጠው እንግዳ ወይም ለመጻተኛው የቤተሰብ አባላት ቢሸጥ፥ 48ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤ 49ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ የሥጋ ዘመዱ የሆነ ሰው ይቤዠው፤ ወይም እርሱ ቢበለጥግ ራሱን ይቤዥ። 50ከገዛውም ሰው ጋር ለገዢው ራሱን ከሸጠበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ያሰላል፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሆናል፤ ከባለቤቱም ጋር የነበረበት ጊዜ ተቀጣሪ አገልጋይ እንደ ነበረበት ጊዜ ተደርጎ ይተመናል። 51ብዙ ዓመታትም ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 52እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመታት ቢቀሩ ከእርሱ ጋር በመሆን ያሰላል፤ እርሱ ማገልገል እንደሚገባው የዓመታት መጠን የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 53በእርሱ ዘንድ በየዓመቱ እንደሚቀጠር አገልጋይ ይሁን እንጂ በአንተ ፊት በጽኑ እጅ አይግዛው። 54እርሱም በእነዚህ በማናቸውም መንገዶች ባይቤዥ፥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ነፃ ይወጣል። 55የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባርያዎች ናቸውና፤ ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው ባርያዎቼ ናቸው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 25: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ