ኦሪት ዘሌዋውያን 24
24
መብራቱ
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2#ዘፀ. 25፥31-40፤ 27፥20-21።“መብራቱ ሁልጊዜ እንዲበራ ለመብራቱ ተወቅጦ የተጠለለ ንጹሕ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዝ። 3አሮን ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ መጋረጃ ውጭ በጌታ ፊት ሁልጊዜ ያዘጋጀው፤ ለዘለዓለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ይሁን። 4በጌታ ፊት በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁልጊዜ ያዘጋጃል።
የመገናኛው ድንኳን ኅብስት
5 #
ዘፀ. 25፥23-30፤ 1ነገ. 7፥48፤ 2ዜ.መ. 13፥11፤ ዕብ. 9፥2። “መልካሙንም ዱቄት ውሰድ፤ በእርሱም ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በአንድ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ ይደረግበት። 6እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በጌታ ፊት በንጹሕ ወርቅ በተለበጠው ገበታ ላይ አኑራቸው። 7ለጌታም በእሳት የሚቀርብ ቁርባን ተደርጎ፥ ለእንጀራው የመታሰቢያ ቁርባን እንዲሆን በሁለቱ ተርታ ላይ ንጹሕ የሆነ ዕጣን አድርግ። 8#1ዜ.መ. 9፥32።ስለ እስራኤል ልጆች የዘለዓለም ቃል ኪዳን እንዲሆን በጌታ ፊት ሁልጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ በተርታ ያዘጋጀዋል። 9#1ሳሙ. 21፥5።እርሱም ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ለጌታም በእሳት ከሚቀርበው ቁርባን ውስጥ በዘለዓለም ሥርዓት፥ ለእርሱ እጅግ ቅዱስ የሆነ ድርሻ ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት።”
መሳደብ እና ቅጣቱ
10አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ልጅና አንድ እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ተጣሉ፤ 11የእስራኤላዊቱም ልጅ የጌታን ስም ሰደበ፥ አቃለለውም፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የደብራይ ልጅ ነበረች፥ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ። 12#ዘኍ. 15፥34።ጌታም ፍርዱን እስኪያሳውቃቸው ድረስ በእስር ቤት አኖሩት።
13ከዚያም ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 14#ዘሌ. 16፥21።“ተሳዳቢውን ከሰፈሩ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገረው። 15ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፦ ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኃጢአቱን ይሸከማል። 16#ዘፀ. 22፥27፤ 1ነገ. 21፥10፤ 13፤ ማቴ. 26፥65-66፤ ዮሐ. 10፥33።የጌታንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የአገሩ ተወላጅ ቢሆን፥ የጌታን ስም በሰደበ ጊዜ ይገደል። 17#ዘፍ. 9፥5-6፤ ዘፀ. 21፥12-14፤ ዘኍ. 35፥9-34፤ ዘዳ. 19፥11-13።ማናቸውንም ሰው መትቶ የሚገድል ፈጽሞ ይገደል። 18#ዘፀ. 21፥33-34፤ ዘሌ. 17፥4።እንስሳንም መትቶ የሚገድል ሕይወት በሕይወት ፋንታ ካሣውን ይከፍላል። 19ሰውም ባልንጀራው ላይ ጉዳት ቢያደርስ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት። 20#ዘፀ. 21፥23-25፤ ዘዳ. 19፥21፤ ማቴ. 5፥38።በስብራት ፋንታ ስብራት፥ በዐይን ፋንታ ዐይን፥ በጥርስ ፋንታ ጥርስ ይሁን፤ በሰው ላይ ጉዳት ያደረገ ሰው እንዲሁ ይደረግበት። 21እንስሳንም የሚገድል በካሣ ይተካ፤ ሰውን ግን የሚገድል ይገደል። 22#ዘሌ. 19፥34፤ ዘፀ. 12፥49፤ ዘኍ. 15፥16።እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለአገሩ ተወላጅ አንድ ዓይነት ሕግ ይኑራችሁ።” 23#የሐዋ. 7፥57-58።ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈሩ ውጭ አወጡት፥ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 24: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ