ዘሌዋውያን 16:11-19

ዘሌዋውያን 16:11-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“አሮ​ንም ስለ ራሱ ኀጢ​አት የሚ​ሠ​ዋ​ውን መሥ​ዋ​ዕት ወይ​ፈ​ኑን ያቀ​ር​ባል፤ ለራ​ሱም ለቤ​ተ​ሰ​ቡም ያስ​ተ​ሰ​ር​ያል፤ ስለ ኀጢ​አቱ የእ​ር​ሱን መሥ​ዋ​ዕት ወይ​ፈ​ኑን ያር​ዳል። በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ከአ​ለው መሠ​ዊያ ላይ የእ​ሳት ፍም አም​ጥቶ ጥና​ውን ይሞ​ላል፤ ከተ​ወ​ቀ​ጠ​ውም ልቅ​ምና ደቃቅ ዕጣን እጁን ሙሉ ይወ​ስ​ዳል፤ ወደ መጋ​ረ​ጃ​ውም ውስጥ ያመ​ጣ​ዋል። እን​ዳ​ይ​ሞ​ትም የጢሱ ደመና በም​ስ​ክሩ ታቦት ላይ ያለ​ውን መክ​ደኛ ይሸ​ፍን ዘንድ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ዕጣ​ኑን በእ​ሳቱ ላይ ያደ​ር​ጋል። ከወ​ይ​ፈ​ኑም ደም ወስዶ በስ​ር​የቱ መክ​ደኛ ላይ ወደ ምሥ​ራቅ በጣቱ ይረ​ጨ​ዋል፤ ከደ​ሙም በመ​ክ​ደ​ኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረ​ጫል። “ስለ ሕዝ​ቡም ኀጢ​አት የሚ​ሠ​ዋ​ውን መሥ​ዋ​ዕት ፍየል ያር​ዳል፤ ደሙ​ንም ወደ መጋ​ረ​ጃው ውስጥ ያመ​ጣ​ዋል፤ በወ​ይ​ፈ​ኑም ደም እን​ዳ​ደ​ረገ በፍ​የሉ ደም ያደ​ር​ጋል፤ በመ​ክ​ደ​ኛው ላይና በመ​ክ​ደ​ኛው ፊት ይረ​ጨ​ዋል። ከእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ርኩ​ስ​ነት፥ ከመ​ተ​ላ​ለ​ፋ​ቸ​ውም፥ ከኀ​ጢ​አ​ታ​ቸ​ውም የተ​ነሣ ለመ​ቅ​ደሱ ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ለ​ታል፤ እን​ዲ​ሁም በር​ኩ​ስ​ነ​ታ​ቸው መካ​ከል ከእ​ነ​ርሱ ጋር ለኖ​ረች ለም​ስ​ክሩ ድን​ኳን ያደ​ር​ጋል። እርሱ ለማ​ስ​ተ​ስ​ረይ ወደ መቅ​ደሱ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤ​ተ​ሰ​ቡም፥ ለእ​ስ​ራ​ኤል ጉባኤ ሁሉ አስ​ተ​ስ​ርዮ እስ​ኪ​ወጣ ድረስ በም​ስ​ክሩ ድን​ኳን ውስጥ ማንም አይ​ኖ​ርም። በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ወዳ​ለው ወደ መሠ​ዊ​ያው ወጥቶ ያስ​ተ​ሰ​ር​ይ​ለ​ታል፤ ከወ​ይ​ፈ​ኑም ደም፥ ከፍ​የ​ሉም ደም ወስዶ በመ​ሠ​ዊ​ያው ዙሪያ ያሉ​ትን ቀን​ዶች ያስ​ነ​ካል። ከደ​ሙም በእ​ርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረ​ጫል፤ ከእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ርኩ​ስ​ነት ያነ​ጻ​ዋል፤ ይቀ​ድ​ሰ​ው​ማል።

ዘሌዋውያን 16:11-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“አሮን ለራሱና ለቤተ ሰቡ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ወይፈኑን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ስለ ራሱ ያቅርብ፤ ወይፈኑንም ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረድ። በእግዚአብሔር ፊት ካለው መሠዊያ ፍም ተወስዶ የተሞላበትን ጥና ይያዝ፤ ሁለት እጅ ሙሉ መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን ይውሰድ፤ እነዚህንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ይዞ ይግባ። እንዳይሞትም የዕጣኑ ጢስ በምስክሩ ላይ ያለውን ስርየት መክደኛ ይሸፍነው ዘንድ፣ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ይጨምረው። ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ፊተኛው ወገን ላይ በጣቱ ይርጭ፤ ደግሞም በስርየቱ መክደኛ ትይዩ በጣቱ ሰባት ጊዜ ይርጭ። “ፍየሉንም ለሕዝቡ የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረደው፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ወስዶ በወይፈኑ ደም እንዳደረገው በዚህኛው ያድርግ፤ ደሙን በስርየቱ መክደኛ ላይ፣ እንዲሁም በመክደኛው ትይዩ ይርጭ። ከእስራኤላውያን ርኩሰትና ዐመፅ፣ ከየትኛውም ኀጢአታቸው ይነጻ ዘንድ በዚህ ሁኔታ ለቅድስተ ቅዱሳኑ ያስተሰርይለታል፤ በርኩሰታቸው መካከል በእነርሱ ዘንድ ላለችውም የመገናኛዋ ድንኳን እንደዚሁ ያደርጋል። አሮን ለማስተስረይ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለራሱ፣ ለቤተ ሰቡና ለእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ ማንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አይገኝ። “ከዚያም መጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ወዳለው መሠዊያ ይምጣ፤ ለመሠዊያውም ያስተስርይለት፤ ከወይፈኑና ከፍየሉ ደም ወስዶ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ያስነካ፤ ከእስራኤላውያንም ርኩሰት መሠዊያውን ለማንጻትና ለመቀደስ ከደሙ ወስዶ በጣቱ ሰባት ጊዜ ይርጭበት።

ዘሌዋውያን 16:11-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አሮንም ስለ ራሱ ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ወይፈኑን ያቀርባል፤ ለራሱም ለቤተ ሰቡም ያስተሰርያል፤ ስለ ኃጢአቱ የእርሱን መሥዋዕት ወይፈኑን ያርዳል። በእግዚአብሔርም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል፥ ከተወቀጠውም ከጣፋጭ ዕጣን እጁን ሙሉን ይወስዳል፤ ወደ መጋረጃውም ውስጥ ያመጣዋል። እንዳይሞትም የጢሱ ደመና በምስክሩ ላይ ያለውን መክደኛ ይሸፍን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል። ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ላይ ወደ ምሥራቅ በጣቱ ይረጨዋል፤ ከደሙም በመክደኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጫል። ስለ ሕዝቡም ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፥ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛውም ላይና በመክደኛውም ፊት ይረጨዋል። ከእስራኤል ልጆች ርኩስነት ከመተላለፋቸውም ከኃጢአታቸውም የተነሣ ለመቅደሱ ያስተሰርይለታል፤ እንዲሁም በርኩስነታቸው መካከል ከእነርሱ ጋር ለኖረች ለመገናኛው ድንኳን ያደርጋል። እርሱም ለማስተስረይ ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተ ሰቡም፥ ለእስራኤል ጉባዔ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማንም አይኖርም። በእግዚአብሔርም ፊት ወዳለው ወደ መሠዊያ ወጥቶ ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑም ደም ከፍየሉም ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ቀንዶች ያስነካል። ከደሙም በእርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል፥ ከእስራኤልም ልጆች ርኩስነት ያነጻዋል፥ ይቀድሰውማል።

ዘሌዋውያን 16:11-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አሮንም ኰርማውን ስለ ራሱና ስለ ቤተሰቡ የኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት በማድረግ ይረደው፤ ከመሠዊያው የሚቃጠል የእሳት ፍም በጥናው ሞልቶም ሁለት እፍኝ ጣፋጭ ሽታ ያለውን የተወቀጠ ደቃቅ ዕጣን በመውሰድ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያግባ፤ እዚያም በእግዚአብሔር ፊት በእሳቱ ላይ ዕጣን ይጨምርበት፤ እርሱም አይቶ እንዳይሞት የዕጣኑ ጢስ የስርየት መክደኛውን ይሸፍነው። ከኰርማውም ደም ጥቂት ወስዶ በጣቱ እየነከረ በስርየት መክደኛው ላይ ከፊት ለፊት በኩል ይርጭ፤ እንዲሁም ከእርሱ ጥቂቱን በኪዳኑ ታቦት ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። ከዚህም በኋላ ለሕዝቡ የኃጢአት ማስተስረያ የሆነውን ፍየል ይረድ፤ ደሙንም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አስገብቶ በኰርማው ደም ባደረገው ዐይነት፥ በስርየት መክደኛው ላይ፥ እንዲሁም በኪዳኑ ታቦት ፊት ይርጨው። በዚህም ዐይነት ቅድስተ ቅዱሳኑን ከእስራኤል ሕዝብ ርኲሰትና ከኃጢአታቸውም ሁሉ ለማጥራት የማንጻትን ሥርዓት ይፈጽማል፤ ንጹሕ ባልሆነ ሰፈር መካከል ስለሚገኝ ድንኳኑንም ለማንጻት እንዲሁ ያደርጋል። አሮን ለማስተሰረይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተሰቡ፥ ለእስራኤል ጉባኤ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ ድንኳን ውስጥ ማንም አይኑር፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ወዳለው መሠዊያ ወጥቶ መሠዊያውን ያንጻው፤ ከኰርማውና ከፍየሉ ጥቂት ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ጒጦች ይቀባ፤ ከደሙም ጥቂቱን ወስዶ በጣቱ እየነከረ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ይርጭ፤ በዚህም ዐይነት ከእስራኤል ሕዝብ ርኲሰትን በማንጻት መሠዊያውን የተቀደሰ ያደርገዋል።

ዘሌዋውያን 16:11-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“አሮንም ለእርሱ የሆነውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያቀርባል፤ ለራሱም ለቤተሰቡም ያስተሰርያል፤ ለእርሱ የሆነውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያርዳል። በጌታም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ ያለውን የእሳት ፍም በጥናው ሞልቶ ያመጣል፥ ከተወቀጠውም ከመዐዛው ያማረ ዕጣን በሁለቱ የእጁ መዳፎች ሙሉ ዘግኖ ይወስዳል፤ ወደ መጋረጃውም ውስጥ ያመጣዋል። እንዳይሞትም የጢሱ ደመና በምስክሩ ላይ ያለውን የስርየት መክደኛ እንዲሸፍን በጌታ ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል። ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ትይዩ በምሥራቅ በኩል በጣቱ ይረጨዋል፤ እንዲሁም ከደሙ በስርየቱ መክደኛ ፊት ለፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጫል። “ለሕዝቡም የሆነውን የኃጢአት መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፥ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ እንዲሁ በፍየሉ ደም ላይ ያደርጋል፤ በስርየቱ መክደኛም ላይና በስርየቱ መክደኛም ፊት ለፈት ይረጨዋል። ከእስራኤል ልጆች ርኩስነት፥ ከመተላለፋቸውም፥ ከኃጢአታቸውም ሁሉ የተነሣ ለተቀደሰው ስፍራ ያስተሰርይለታል፤ በርኩስነታቸውም መካከል ከእነርሱ ጋር ላለው ለመገናኛው ድንኳን እንዲሁ ያደርጋል። አሮንም ለማስተስረይ ወደተቀደሰው ስፍራ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተሰቡም፥ ለእስራኤል ጉባዔ ሁሉ አስተስርዮ እስኪ ወጣ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማንም ሰው አይገኝ። ከዚያም በኋላ በጌታ ፊት ወዳለው ወደ መሠዊያው ይወጣል፤ ለእርሱም ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑም ደም ከፍየሉም ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ቀንዶች ያስነካል። ከደሙም በእርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል፥ ከእስራኤልም ልጆች ርኩስነት ያነጻዋል፥ ይቀድሰዋልም።