ኦሪት ዘሌዋውያን 16:11-19

ኦሪት ዘሌዋውያን 16:11-19 አማ54

አሮንም ስለ ራሱ ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ወይፈኑን ያቀርባል፤ ለራሱም ለቤተ ሰቡም ያስተሰርያል፤ ስለ ኃጢአቱ የእርሱን መሥዋዕት ወይፈኑን ያርዳል። በእግዚአብሔርም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል፥ ከተወቀጠውም ከጣፋጭ ዕጣን እጁን ሙሉን ይወስዳል፤ ወደ መጋረጃውም ውስጥ ያመጣዋል። እንዳይሞትም የጢሱ ደመና በምስክሩ ላይ ያለውን መክደኛ ይሸፍን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል። ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ላይ ወደ ምሥራቅ በጣቱ ይረጨዋል፤ ከደሙም በመክደኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጫል። ስለ ሕዝቡም ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፥ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛውም ላይና በመክደኛውም ፊት ይረጨዋል። ከእስራኤል ልጆች ርኩስነት ከመተላለፋቸውም ከኃጢአታቸውም የተነሣ ለመቅደሱ ያስተሰርይለታል፤ እንዲሁም በርኩስነታቸው መካከል ከእነርሱ ጋር ለኖረች ለመገናኛው ድንኳን ያደርጋል። እርሱም ለማስተስረይ ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተ ሰቡም፥ ለእስራኤል ጉባዔ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማንም አይኖርም። በእግዚአብሔርም ፊት ወዳለው ወደ መሠዊያ ወጥቶ ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑም ደም ከፍየሉም ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ቀንዶች ያስነካል። ከደሙም በእርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል፥ ከእስራኤልም ልጆች ርኩስነት ያነጻዋል፥ ይቀድሰውማል።