ዘሌዋውያን 16:11-19

ዘሌዋውያን 16:11-19 NASV

“አሮን ለራሱና ለቤተ ሰቡ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ወይፈኑን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ስለ ራሱ ያቅርብ፤ ወይፈኑንም ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረድ። በእግዚአብሔር ፊት ካለው መሠዊያ ፍም ተወስዶ የተሞላበትን ጥና ይያዝ፤ ሁለት እጅ ሙሉ መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን ይውሰድ፤ እነዚህንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ይዞ ይግባ። እንዳይሞትም የዕጣኑ ጢስ በምስክሩ ላይ ያለውን ስርየት መክደኛ ይሸፍነው ዘንድ፣ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ይጨምረው። ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ፊተኛው ወገን ላይ በጣቱ ይርጭ፤ ደግሞም በስርየቱ መክደኛ ትይዩ በጣቱ ሰባት ጊዜ ይርጭ። “ፍየሉንም ለሕዝቡ የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረደው፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ወስዶ በወይፈኑ ደም እንዳደረገው በዚህኛው ያድርግ፤ ደሙን በስርየቱ መክደኛ ላይ፣ እንዲሁም በመክደኛው ትይዩ ይርጭ። ከእስራኤላውያን ርኩሰትና ዐመፅ፣ ከየትኛውም ኀጢአታቸው ይነጻ ዘንድ በዚህ ሁኔታ ለቅድስተ ቅዱሳኑ ያስተሰርይለታል፤ በርኩሰታቸው መካከል በእነርሱ ዘንድ ላለችውም የመገናኛዋ ድንኳን እንደዚሁ ያደርጋል። አሮን ለማስተስረይ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለራሱ፣ ለቤተ ሰቡና ለእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ ማንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አይገኝ። “ከዚያም መጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ወዳለው መሠዊያ ይምጣ፤ ለመሠዊያውም ያስተስርይለት፤ ከወይፈኑና ከፍየሉ ደም ወስዶ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ያስነካ፤ ከእስራኤላውያንም ርኩሰት መሠዊያውን ለማንጻትና ለመቀደስ ከደሙ ወስዶ በጣቱ ሰባት ጊዜ ይርጭበት።