ኦሪት ዘሌዋውያን 16
16
የስርየት ቀን
1በእግዚአብሔር ፊት ሌላ እሳትን ስላመጡ የሞቱ ሁለቱ የአሮን ልጆች ከሞቱ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ተናገረው። 2እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመናው ውስጥ እታያለሁና እንዳይሞት በመጋረጃው ውስጥ በምስክሩ ታቦት ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ሁልጊዜ እንዳይገባ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው። 3እንዲሁ አሮን ለኀጢአት መሥዋዕት ከላሞች ወይፈን፥ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አውራ በግ ይዞ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ይግባ። 4የተቀደሰውንም የተልባ እግር ቀሚስ ይልበስ፤ የተልባ እግርም ሱሪ በገላው ላይ ይሁን፤ የተልባ እግር መታጠቂያ ይታጠቅ፤ የተልባ እግር አክሊልም በራሱ ላይ ያድርግ፤ እነዚህ የተቀደሱ ልብሶች ናቸው፤ ገላውንም በውኃ ታጥቦ ይልበሳቸው። 5ከእስራኤልም ልጆች ማኅበር ለኀጢአት መሥዋዕት ሁለት የፍየል ጠቦቶች፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ።
6“አሮንም የኀጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያቀርባል፤ ለራሱም፥ ለቤተሰቡም ያስተሰርያል። 7ሁለቱንም የፍየል ጠቦቶች ወስዶ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያቆማቸዋል። 8አሮንም በሁለቱ የፍየል ጠቦቶች ላይ ዕጣ ይጥልባቸዋል፤ አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር፥ ሌላውንም ዕጣ ለሚለቀቅ። 9አሮንም የእግዚአባሔር ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያቀርባል፤ ስለ ኀጢአትም መሥዋዕት ያደርገዋል። 10የመለቀቅም ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያስተሰርይበት ዘንድ፥ ለመለቀቅም ወደ ምድረ በዳ ይሰድደው ዘንድ በሕይወቱ በእግዚአብሔር ፊት ያቆመዋል።
11“አሮንም ስለ ራሱ ኀጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ወይፈኑን ያቀርባል፤ ለራሱም ለቤተሰቡም ያስተሰርያል፤ ስለ ኀጢአቱ የእርሱን መሥዋዕት ወይፈኑን ያርዳል። 12በእግዚአብሔርም ፊት ከአለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል፤ ከተወቀጠውም ልቅምና ደቃቅ ዕጣን እጁን ሙሉ ይወስዳል፤ ወደ መጋረጃውም ውስጥ ያመጣዋል። 13እንዳይሞትም የጢሱ ደመና በምስክሩ ታቦት ላይ ያለውን መክደኛ ይሸፍን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል። 14ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ላይ ወደ ምሥራቅ በጣቱ ይረጨዋል፤ ከደሙም በመክደኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጫል።
15“ስለ ሕዝቡም ኀጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛው ላይና በመክደኛው ፊት ይረጨዋል። 16ከእስራኤል ልጆች ርኩስነት፥ ከመተላለፋቸውም፥ ከኀጢአታቸውም የተነሣ ለመቅደሱ ያስተሰርይለታል፤ እንዲሁም በርኩስነታቸው መካከል ከእነርሱ ጋር ለኖረች ለምስክሩ ድንኳን ያደርጋል። 17እርሱ ለማስተስረይ ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተሰቡም፥ ለእስራኤል ጉባኤ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ማንም አይኖርም። 18በእግዚአብሔርም ፊት ወዳለው ወደ መሠዊያው ወጥቶ ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑም ደም፥ ከፍየሉም ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ቀንዶች ያስነካል። 19ከደሙም በእርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል፤ ከእስራኤልም ልጆች ርኩስነት ያነጻዋል፤ ይቀድሰውማል።
የሕዝቡን ኀጢአት ተሸክሞ ወደ በረሃ ስለሚለቀቀው የፍየል ጠቦት
20“ስለመቅደሱ፥ስለ ምስክሩም ድንኳን፥ ስለ መሠዊያውም ማስተስረያና ስለ ካህናትም ማንጻት ከፈጸመ በኋላ ደኅነኛውን ፍየል ያቀርባል። 21አሮንም ሁለቱን እጆቹን በደኅነኛው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፤ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ፥ መተላለፋቸውን ሁሉ፥ ኀጢአታቸውንም ሁሉ ያስተሰርያል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፤ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል። 22ፍየሉም ኀጢአታቸውን ሁሉ ወደ በረሃ ይሸከማል፤ ፍየሉንም ዛፍ በሌለበት በምድረ በዳ ውስጥ ይለቅቀዋል።
23“አሮንም ወደ ምስክሩ ድንኳን ይገባል፤ ወደ መቅደሱም በገባ ጊዜ የለበሰውን የተልባ እግር ልብስ ያወልቃል፤ በዚያም ይተወዋል። 24በተቀደሰውም ስፍራ ገላውን በውኃ ይታጠባል፤ ሌላውንም ልብስ ለብሶ ይወጣል፤ የእርሱንም የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ለካህናቱ እንዳስተሰረየ ለራሱም፥ ለሕዝቡም ያስተሰርያል። 25የኀጢአቱንም መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 26ለመለቀቅ የሚሆነውን ፍየል የወሰደ ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል። 27ለማስተስረያም እንዲሆን ደማቸው ወደ መቅደስ የገባውን የኀጢአቱን መሥዋዕት ወይፈንና የኀጢአቱን መሥዋዕት ፍየል ከሰፈሩ ወደ ውጭ ያወጡአቸዋል፤ ቍርበታቸውንም፥ ሥጋቸውንም፥ ፈርሳቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። 28ያቃጠላቸውም ሰው ልብሱን ያጥባል፤ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል።
29“ይህም የዘለዓለም ሥርዐት ይሁንላችሁ። 30በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተስረያ ይሆንላችኋልና በሰባተኛው ወር ከወሩም በዐሥረኛው ቀን ራሳችሁን አስጨንቋት፤ የሀገር ልጅም፥ በእናንተም መካከል የተቀመጠ እንግዳ ሥራን ሁሉ አትሥሩበት፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከኀጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ። 31ታላቅ ሰንበት ይሆንላችኋል፤ ራሳችሁንም ታዋርዳላችሁ፤ የዘለዓለም ሥርዐት ነው። 32የሚቀባውም፥ በአባቱም ፋንታ ካህን ሊሆን የሚካነው ካህን ያስተስርይ፤ የተቀደሰውንም የተልባ እግር ልብስ ይልበስ። 33ለቅድስተ ቅዱሳንም ያስተስርይ፤ ለምስክሩ ድንኳን፥ ለመሠዊያውም ያስተስርይ፤ ለካህናቱም፥ ለጉባኤውም ሕዝብ ሁሉ ያስተስርይ። 34ይህም አንድ ጊዜ በዓመት ለእስራኤል ልጆች ስለ ኀጢአታቸው ሁሉ ያስተሰርይ ዘንድ የዘለዓለም ሥርዐት ይሁንላችሁ።” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 16: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ