ኢዮብ 6:1-30

ኢዮብ 6:1-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢዮ​ብም መለሰ፥ እን​ዲ​ህም አለ፦ “ከእ​ና​ንተ አንዱ መቅ​ሠ​ፍ​ቴን ምነው በመ​ዘነ ኖሮ! መከ​ራ​ዬ​ንም በአ​ን​ድ​ነት ምነው በሚ​ዛን ላይ ባኖ​ረው ኖሮ! ከባ​ሕር አሸዋ ይልቅ ይከ​ብድ ነበ​ርና፤ ነገር ግን ቃሌ ሐሰ​ትን ይመ​ስ​ላል። እነሆ፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፍላጻ በሥ​ጋዬ ላይ ነው፤ መር​ዙም ደሜን ይመ​ጥ​ጣል። ለመ​ና​ገር ስጀ​ም​ርም ይወ​ጋ​ኛል። በውኑ የሜዳ አህያ ሣር እያ​ለው በከ​ንቱ ይጮ​ኻ​ልን? የሚ​በ​ላ​ውን ፈልጎ አይ​ደ​ለ​ምን? ወይስ በሬ በበ​ረት ውስጥ ገለባ ሳለው ይጮ​ኻ​ልን? ምግብ ያለ ጨው ይበ​ላ​ልን? የጎ​መን ዘር ጭማ​ቂስ ይጣ​ፍ​ጣ​ልን? ወይስ ለከ​ንቱ ጣዕም አለ​ውን? ሰው​ነቴ ማረፍ አል​ቻ​ለ​ችም፤ የሥ​ጋ​ዬን ክር​ፋት እንደ አን​በሳ ክር​ፋት እመ​ለ​ከ​ተ​ዋ​ለ​ሁና። ልመ​ናዬ ምነው በደ​ረ​ሰ​ልኝ! እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ተስ​ፋ​ዬን ምነው በሰ​ጠኝ! እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ያቈ​ስ​ለኝ ዘንድ ጀመረ፥ ነገር ግን እስከ መጨ​ረ​ሻው አላ​ጠ​ፋ​ኝም። መቃ​ብሬ በግ​ንቡ የም​መ​ላ​ለ​ስ​በት ከተ​ማዬ ይሁን፥ ከእ​ር​ሱም ፈቀቅ አል​ልም የአ​ም​ላ​ኬን ቅዱስ ቃል አል​ካ​ድ​ሁ​ምና። እታ​ገሥ ዘንድ ጕል​በቴ ምን​ድን ነው? ነፍ​ሴም ትጽ​ናና ዘንድ ዘመኔ ምን​ድን ነው? ጕል​በቴ የድ​ን​ጋይ ጉል​በት ነውን? በውኑ ሥጋ​ዬስ እንደ ናስ ነውን? በእ​ርሱ የታ​መ​ንሁ አይ​ደ​ለ​ሁ​ምን? ረድ​ኤቱ ከእኔ ለምን ራቀ? ምሕ​ረቱ ቸል አለኝ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አል​ጐ​በ​ኘ​ኝም አል​ተ​መ​ለ​ከ​ተ​ኝም። “ወን​ድ​ሞ​ቼም እንደ ደረቅ ወንዝ፥ እንደ አለፈ ማዕ​በ​ልም አላ​ወ​ቁ​ኝም። ያከ​ብ​ሩኝ የነ​በሩ እነ​ዚያ፥ አሁን እንደ በረ​ዶና እንደ ረጋ አመ​ዳይ ሆኑ​ብኝ፤ ወደ ሙቀት ሲቀ​ርብ በቀ​ለጠ ጊዜ ምን እንደ ነበረ አይ​ታ​ወ​ቅም። እን​ደ​ዚ​ሁም እኔ ከሁሉ ተለ​ይቼ ጠፋሁ፥ ከቤ​ቴም ወጥቼ የተ​ጣ​ልሁ ሆንሁ። የቴ​ማ​ና​ው​ያ​ንን መን​ገ​ዶች፥ የሳ​ባ​ው​ያ​ንን ክፋ​ትና ቸል​ተ​ኝ​ነት ተመ​ል​ከቱ። በከ​ተ​ሞ​ችና በገ​ን​ዘ​ቦች የሚ​ታ​መኑ ያፍ​ራሉ። አሁ​ንም እና​ንተ ያለ ምሕ​ረት መጣ​ችሁ፤ ቍስ​ሌ​ንም አይ​ታ​ችሁ ፈራ​ችሁ። ለምን? በውኑ፦ ከእ​ና​ንተ አን​ዳች ነገር ጠየ​ቅ​ሁን? ወይስ፦ ከእ​ና​ንተ ኀይ​ልን ተመ​ኘ​ሁን? ወይስ ከጠ​ላ​ቶች እጅ ታስ​ጥ​ሉኝ ዘንድ ከኀ​ይ​ለ​ኞ​ችም እጅ ታድ​ኑኝ ዘንድ። “አስ​ተ​ም​ሩኝ፥ እኔም አዳ​ም​ጣ​ች​ኋ​ለሁ፤ የተ​ሳ​ሳ​ት​ሁ​ትም ካለ አስ​ረ​ዱኝ። የእ​ው​ነ​ተኛ ሰው ቃል ሐሰ​ትን ይመ​ስ​ላል፥ ከእ​ና​ንተ ዘንድ ኀይ​ልን የም​ጠ​ይቅ አይ​ደ​ለ​ምና። የን​ግ​ግ​ራ​ች​ሁም ማጽ​ና​ናት ዕረ​ፍ​ትን አይ​ሰ​ጠ​ኝም፤ የአ​ን​ደ​በ​ታ​ች​ሁም ቅል​ጥ​ፍና ደስ አያ​ሰ​ኘ​ኝም። በድሃ አደጉ ላይ ትስ​ቃ​ላ​ች​ሁና፥ ወዳ​ጃ​ች​ሁ​ንም ትሰ​ድ​ባ​ላ​ች​ሁና። አሁ​ንም፥ ፊታ​ች​ሁን አይቼ ሐሰት አል​ና​ገ​ርም። አሁ​ንም ተቀ​መጡ፤ በደ​ልም አይ​ኑር፤ ዳግ​መ​ኛም ከጻ​ድቁ ጋር አንድ ሁኑ። በአ​ን​ደ​በቴ በደል የለ​ምና አፌ ጕሮ​ሮ​ዬም ጥበ​ብን ይና​ገ​ራል።

ኢዮብ 6:1-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ምነው ሐዘኔ በተመዘነ! መከራዬም ሚዛን ላይ በተቀመጠ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ በከበደ፣ ኀይለ ቃሌም ባላስገረመ ነበር! ሁሉን ቻይ አምላክ ፍላጻ በውስጤ ነው፤ መንፈሴም መርዙን ትጠጣለች፤ የእግዚአብሔር ማስደንገጥ ተሰልፎብኛል። የሜዳ አህያ ሣር እያለው፣ በሬስ ድርቆሽ እያለው፣ ይጮኻልን? የማይጣፍጥ ምግብ ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የዕንቍላል ውሃ ጣዕም አለውን? እንዲህ ዐይነቱን ምግብ እጸየፋለሁ፤ ለመንካትም አልፈልግም። “ምነው ልመናዬ በተመለሰልኝ፤ እግዚአብሔር የምመኘውን በሰጠኝ፤ እግዚአብሔር አድቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ፣ ምነው እጁ በተፈታ! ፋታ በማይሰጥ ሕመም ውስጥ እየተደሰትሁ፣ ይህ መጽናኛ በሆነልኝ ነበር፤ የቅዱሱን ትእዛዝ አልጣስሁምና። “አሁንም ተስፋ አደርግ ዘንድ ብርታቴ፣ እታገሥስ ዘንድ አለኝታዬ ምንድን ነው? የድንጋይ ጕልበት አለኝን? ሥጋዬስ ናስ ነውን? ያልተሳካልኝ ሰው ነኝና፣ ራሴን ለመርዳት ምን ጕልበት አለኝ? “ለወዳጁ በጎነት የማያሳይ ሰው፣ ሁሉን ቻዩን አምላክ መፍራት ትቷል። ወንድሞቼ ግን እንደማያዛልቅ ጅረት፣ ለጊዜው ሞልቶ እንደሚፈስስ ወንዝ የማይታመኑ ናቸው፤ በረዶ በሟሟ ጊዜ ወንዙ ይደፈርሳል፤ ዐመዳይም በቀለጠ ጊዜ ይሞላል፤ በበጋ ወራት ግን ይጠፋል፤ በሙቀትም ጊዜ መፋሰሻው ላይ አይገኝም። ሲራራ ነጋዴዎች ውሃ አጥተው መንገዳቸውን ይቀይራሉ፤ ወደ በረሓም ገብተው ይጠፋሉ። የቴማን ነጋዴዎች ውሃ ይፈልጋሉ፤ የሳባ መንገደኞችም ተስፋ ያደርጋሉ። ርግጠኞች ሆነው ስለ ነበር ተሰቀቁ፤ እዚያ ደረሱ፣ ግን ዐፈሩ። አሁንም እናንተ እንደዚያ ሆናችሁብኝ፤ መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ። ለመሆኑ፣ ‘ስለ እኔ ሆናችሁ አንድ ነገር ስጡልኝ፣ በዕዳ የተያዘብኝንም በሀብታችሁ አስለቅቁልኝ!’ ብያለሁን? ወይስ፣ ‘ከጠላት አስጥሉኝ፣ ከጨካኝም እጅ ተቤዡኝ’ አልኋችሁን? “አስተምሩኝ፤ እኔም ዝም እላለሁ፤ ምኑ ላይ እንደ ተሳሳትሁ ጠቍሙኝ። የቅንነት ቃል ምንኛ ኀያል ነው! የእናንተ ክርክር ግን ምን ፋይዳ አለው? የተናገርሁትን ለማረም፣ ተስፋ የቈረጠውንም ሰው ቃል እንደ ነፋስ ለመቍጠር ታስባላችሁን? በድኻ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁን? ወይስ ወዳጃችሁን ትሸጣላችሁን? “አሁን ግን ፈቃዳችሁ ቢሆን ወደ እኔ ተመልከቱ፤ ፊት ለፊት እዋሻችኋለሁን? መለስ በሉ፤ ፍርደ ገምድል አትሁኑ፤ ጽድቄ ጸንታ ቆማለችና መለስ ብላችሁ አስተውሉ። ክፋት በአንደበቴ አለን? አፌስ ተንኰልን መለየት አይችልምን?

ኢዮብ 6:1-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦ ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በተደረገ ኖሮ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፥ ስለዚህ ቃሌ ደፋር ሆኖአል። ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥ መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፥ የእግዚአብሔር ድንጋጤ በላዬ ተሰልፎአል። በውኑ የሜዳ አህያ ሣር ሳለው ይጮኻልን? ወይስ በሬ ገለባ ሳለው ይጮኻልን? የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የእንቍላል ውኃ ይጥማልን? ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፥ እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ። ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ! እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ! መጽናናት በሆነልኝ ነበር፥ በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥ የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና። እጠብቅ ዘንድ ጕልበቴ ምንድር ነው? እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድር ነው? ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን? ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን? በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን? ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራት ለሚተው፥ ለመዛል ለቀረበው ስንኳ ወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል። ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥ እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ። ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥ አመዳይም ተሰወረባቸው፥ ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፥ በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ። በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፥ ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ። የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥ የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው። ተስፋ አድርገዋቸው ነበርና አፈሩ፥ ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው። አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፥ መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ። በውኑ፦ አንዳች ነገር አምጡልኝ፥ ወይስ፦ ከብልጥግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፥ ወይስ፦ ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፥ ወይስ፦ ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን? አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፥ የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ። የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው! የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል? ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን? በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፥ ለወዳጆቻችሁም ጕድጓድ ትቈፍራላችሁ። አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፥ በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም። እባካችሁ፥ ተመለሱ፥ በደል አይሁን፥ ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ። በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን? አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?

ኢዮብ 6:1-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በታየ ኖሮ! ከባሕር ዳር አሸዋ ይበልጥ በከበደ ነበር፤ ስለዚህ ትዕግሥት የጐደለው ንግግሬ ሊያስገርምህ አይገባም። ሁሉን የሚችል አምላክ በፍላጻዎቹ ወግቶኛል፤ መርዛቸውም በሰውነቴ ተሠራጭቶአል፤ የሚያስደነግጥ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ዙሪያዬን ከቦኛል። በውኑ የሜዳ አህያ ለምለም ሣር ካገኘ በሬም ድርቆሽ ካገኘ ይጮኻልን? ጨው ያልገባበት ጣዕም ያጣ ምግብ ይበላልን? የእንቊላልስ ውሃ ይጣፍጣልን? ለዚህ ዐይነቱ ምግብ ፍላጎት የለኝም፤ ብበላውም እንኳ ጤና ይነሣኛል። “ምነው እግዚአብሔር የምመኘውን በሰጠኝ! ምነው ጸሎቴንስ በሰማኝ! ከዚህ ሁሉ ምነው ፈቃዱ ሆኖ ቢሰባብረኝ! እጁንም ሰንዝሮ ቢያጠፋኝ! ይህ ለእኔ መጽናናትን በሰጠኝ ነበር። የቅዱሱን ቃል ምንጊዜም ስላልካድኩ፥ ምንም እንኳ ሥቃይ ቢበዛብኝ በደስታ በዘለልኩ ነበር። በሕይወት ለመኖር የሚያበቃ ምን ብርታት አለኝ? ተስፋ ከሌለኝስ ለምን እኖራለሁ? እኔ እንደ ድንጋይ ጠንካራ ነኝን? ሰውነቴስ እንደ ናስ ጠንካራ ነውን? ራሴን ለመርዳት ምንም ኀይል የለኝም፤ ያለኝ ኀይል ሁሉ ተወስዶብኛል። “ለወዳጁ ያለውን ታማኝነት የሚነሣ ሰው እግዚአብሔርን መፍራቱን የተወ ነው። ወንድሞቼ ግን ጐርፉ ከወረደ በኋላ እንደሚደርቁና እንደማያስተማምኑ ወንዞች አታላዮች ናቸው። ወንዞቹ በክረምት ወራት በበረዶ ተሞልተው ይሸፈናሉ። በበጋ ወራት ግን ተነው ይጠፋሉ። ወንዞቹም ባዶና ደረቅ ይሆናሉ። የጭነት ከብቶችን እየነዱ የሚሄዱ መንገደኞች ከመንገድ ወጥተው ውሃ ፍለጋ ወደ በረሓ ገብተው ባዝነው ይጠፋሉ። የቴማ መንገደኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ የሳባ ነጋዴዎችም ውሃ ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ። የተማመኑበትን ወንዝ ደርቆ ሲያገኙ ተስፋ ይቈርጣሉ፤ ወደ ቦታውም ሲደርሱ ይበሳጫሉ። እናንተም ለእኔ እንደ እነዚያ ደረቅ ወንዞች ናቸሁ። የደረሰብኝን መከራ አይታችሁ ወደ ኋላ አፈገፈጋችሁ። ለመሆኑ ይህን ወይም ያንን ስጡኝ፥ ወይም በሀብታችሁ ታደጉኝ ብያችኋለሁን? ወይስ ከጠላት እጅ አድኑኝ፤ ወይም ከጨቋኞች እጅ ታደጉኝ ብያችኋለሁን? “አስተምሩኝ፤ እኔም ዝም እላለሁ፤ ስሕተቴንም አስረዱኝ። እውነተኛ ቃል መራራ ቢሆንም ተቀባይነት አለው፤ የእናንተ ትችት ግን ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የእኔን ንግግር እንደ ነፋስ ባዶ አድርጋችሁ ትቈጥሩታላችሁ፤ ታዲያ፥ ተስፋ ለቈረጥሁት ለእኔ መልስ መስጠት ለምን ትፈልጋላችሁ? በሙት ልጅ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤ ወዳጆቻችሁን ለመሸጥ የዋጋ ክርክር ታደርጋላችሁ! እባካችሁ ፊቴን ተመልከቱ፤ በፊታችሁ እዋሻለሁን? በደል እንዳይሆንባችሁ ተመለሱ፤ አሁንም ተመለሱ፤ እኔ ትክክለኛ ነኝ። በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን? አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?

ኢዮብ 6:1-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “ትካዜዬ ምነው በተመዘነ! መከራዬም በሚዛን ላይ ምነው በተቀመጠ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ በከበደ ነበርና፥ ለዚህም ነው ቃሌ ደፋር የሆነው። ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥ መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፥ የእግዚአብሔር ሽብሮች በኔ ላይ ተሰልፈዋል። በውኑ የሜዳ አህያ ሣር እያለው ይጮኻልን? ወይስ በሬ ገለባ እያለው ይጮኻልን? የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን? ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፥ እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ። ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ! እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ፥ እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ! መጽናናት በሆነልኝ ነበር፥ በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥ የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና። እጠብቅ ዘንድ ጉልበቴ ምንድነው? እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድነው? ጉልበቴ የድንጋይ ጉልበት ነውን? ሥጋዬስ ነሐስ ነውን? በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን?” “ቸርነትን ለወዳጁ የሚነፍግ፥ ሁሉን ቻይ አምላክን መፍራት የተወ ነው። ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥ እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ። ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥ አመዳይም ተሰወረባቸው፥ ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፥ በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ። በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፥ ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ። የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥ የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው። ተስፋ አድርገውባቸው ነበርና አፈሩ፥ ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው። አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፥ መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ። በውኑ፦ አንዳች ነገር አምጡልኝ፥ ወይስ፦ ከብልጽግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፥ ወይስ፦ ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፥ ወይስ፦ ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን? አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፥ የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ። የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው! የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል? ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን? በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፥ ለወዳጆቻችሁም ጉድጓድ ትቈፍራላችሁ። አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፥ በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም። እባካችሁ፥ ተመለሱ፥ በደል አይሁን፥ ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ። በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን? ምላሴ የተንኰልን ቃና መለየት አይችልምን?”