ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ምነው ሐዘኔ በተመዘነ! መከራዬም ሚዛን ላይ በተቀመጠ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ በከበደ፣ ኀይለ ቃሌም ባላስገረመ ነበር! ሁሉን ቻይ አምላክ ፍላጻ በውስጤ ነው፤ መንፈሴም መርዙን ትጠጣለች፤ የእግዚአብሔር ማስደንገጥ ተሰልፎብኛል። የሜዳ አህያ ሣር እያለው፣ በሬስ ድርቆሽ እያለው፣ ይጮኻልን? የማይጣፍጥ ምግብ ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የዕንቍላል ውሃ ጣዕም አለውን? እንዲህ ዐይነቱን ምግብ እጸየፋለሁ፤ ለመንካትም አልፈልግም። “ምነው ልመናዬ በተመለሰልኝ፤ እግዚአብሔር የምመኘውን በሰጠኝ፤ እግዚአብሔር አድቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ፣ ምነው እጁ በተፈታ! ፋታ በማይሰጥ ሕመም ውስጥ እየተደሰትሁ፣ ይህ መጽናኛ በሆነልኝ ነበር፤ የቅዱሱን ትእዛዝ አልጣስሁምና። “አሁንም ተስፋ አደርግ ዘንድ ብርታቴ፣ እታገሥስ ዘንድ አለኝታዬ ምንድን ነው? የድንጋይ ጕልበት አለኝን? ሥጋዬስ ናስ ነውን? ያልተሳካልኝ ሰው ነኝና፣ ራሴን ለመርዳት ምን ጕልበት አለኝ? “ለወዳጁ በጎነት የማያሳይ ሰው፣ ሁሉን ቻዩን አምላክ መፍራት ትቷል። ወንድሞቼ ግን እንደማያዛልቅ ጅረት፣ ለጊዜው ሞልቶ እንደሚፈስስ ወንዝ የማይታመኑ ናቸው፤ በረዶ በሟሟ ጊዜ ወንዙ ይደፈርሳል፤ ዐመዳይም በቀለጠ ጊዜ ይሞላል፤ በበጋ ወራት ግን ይጠፋል፤ በሙቀትም ጊዜ መፋሰሻው ላይ አይገኝም። ሲራራ ነጋዴዎች ውሃ አጥተው መንገዳቸውን ይቀይራሉ፤ ወደ በረሓም ገብተው ይጠፋሉ። የቴማን ነጋዴዎች ውሃ ይፈልጋሉ፤ የሳባ መንገደኞችም ተስፋ ያደርጋሉ። ርግጠኞች ሆነው ስለ ነበር ተሰቀቁ፤ እዚያ ደረሱ፣ ግን ዐፈሩ። አሁንም እናንተ እንደዚያ ሆናችሁብኝ፤ መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ። ለመሆኑ፣ ‘ስለ እኔ ሆናችሁ አንድ ነገር ስጡልኝ፣ በዕዳ የተያዘብኝንም በሀብታችሁ አስለቅቁልኝ!’ ብያለሁን? ወይስ፣ ‘ከጠላት አስጥሉኝ፣ ከጨካኝም እጅ ተቤዡኝ’ አልኋችሁን? “አስተምሩኝ፤ እኔም ዝም እላለሁ፤ ምኑ ላይ እንደ ተሳሳትሁ ጠቍሙኝ። የቅንነት ቃል ምንኛ ኀያል ነው! የእናንተ ክርክር ግን ምን ፋይዳ አለው? የተናገርሁትን ለማረም፣ ተስፋ የቈረጠውንም ሰው ቃል እንደ ነፋስ ለመቍጠር ታስባላችሁን? በድኻ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁን? ወይስ ወዳጃችሁን ትሸጣላችሁን? “አሁን ግን ፈቃዳችሁ ቢሆን ወደ እኔ ተመልከቱ፤ ፊት ለፊት እዋሻችኋለሁን? መለስ በሉ፤ ፍርደ ገምድል አትሁኑ፤ ጽድቄ ጸንታ ቆማለችና መለስ ብላችሁ አስተውሉ። ክፋት በአንደበቴ አለን? አፌስ ተንኰልን መለየት አይችልምን?
ኢዮብ 6 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢዮብ 6
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢዮብ 6:1-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos