መጽሐፈ ኢዮብ 6:1-30

መጽሐፈ ኢዮብ 6:1-30 አማ05

ከዚህ በኋላ ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በታየ ኖሮ! ከባሕር ዳር አሸዋ ይበልጥ በከበደ ነበር፤ ስለዚህ ትዕግሥት የጐደለው ንግግሬ ሊያስገርምህ አይገባም። ሁሉን የሚችል አምላክ በፍላጻዎቹ ወግቶኛል፤ መርዛቸውም በሰውነቴ ተሠራጭቶአል፤ የሚያስደነግጥ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ዙሪያዬን ከቦኛል። በውኑ የሜዳ አህያ ለምለም ሣር ካገኘ በሬም ድርቆሽ ካገኘ ይጮኻልን? ጨው ያልገባበት ጣዕም ያጣ ምግብ ይበላልን? የእንቊላልስ ውሃ ይጣፍጣልን? ለዚህ ዐይነቱ ምግብ ፍላጎት የለኝም፤ ብበላውም እንኳ ጤና ይነሣኛል። “ምነው እግዚአብሔር የምመኘውን በሰጠኝ! ምነው ጸሎቴንስ በሰማኝ! ከዚህ ሁሉ ምነው ፈቃዱ ሆኖ ቢሰባብረኝ! እጁንም ሰንዝሮ ቢያጠፋኝ! ይህ ለእኔ መጽናናትን በሰጠኝ ነበር። የቅዱሱን ቃል ምንጊዜም ስላልካድኩ፥ ምንም እንኳ ሥቃይ ቢበዛብኝ በደስታ በዘለልኩ ነበር። በሕይወት ለመኖር የሚያበቃ ምን ብርታት አለኝ? ተስፋ ከሌለኝስ ለምን እኖራለሁ? እኔ እንደ ድንጋይ ጠንካራ ነኝን? ሰውነቴስ እንደ ናስ ጠንካራ ነውን? ራሴን ለመርዳት ምንም ኀይል የለኝም፤ ያለኝ ኀይል ሁሉ ተወስዶብኛል። “ለወዳጁ ያለውን ታማኝነት የሚነሣ ሰው እግዚአብሔርን መፍራቱን የተወ ነው። ወንድሞቼ ግን ጐርፉ ከወረደ በኋላ እንደሚደርቁና እንደማያስተማምኑ ወንዞች አታላዮች ናቸው። ወንዞቹ በክረምት ወራት በበረዶ ተሞልተው ይሸፈናሉ። በበጋ ወራት ግን ተነው ይጠፋሉ። ወንዞቹም ባዶና ደረቅ ይሆናሉ። የጭነት ከብቶችን እየነዱ የሚሄዱ መንገደኞች ከመንገድ ወጥተው ውሃ ፍለጋ ወደ በረሓ ገብተው ባዝነው ይጠፋሉ። የቴማ መንገደኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ የሳባ ነጋዴዎችም ውሃ ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ። የተማመኑበትን ወንዝ ደርቆ ሲያገኙ ተስፋ ይቈርጣሉ፤ ወደ ቦታውም ሲደርሱ ይበሳጫሉ። እናንተም ለእኔ እንደ እነዚያ ደረቅ ወንዞች ናቸሁ። የደረሰብኝን መከራ አይታችሁ ወደ ኋላ አፈገፈጋችሁ። ለመሆኑ ይህን ወይም ያንን ስጡኝ፥ ወይም በሀብታችሁ ታደጉኝ ብያችኋለሁን? ወይስ ከጠላት እጅ አድኑኝ፤ ወይም ከጨቋኞች እጅ ታደጉኝ ብያችኋለሁን? “አስተምሩኝ፤ እኔም ዝም እላለሁ፤ ስሕተቴንም አስረዱኝ። እውነተኛ ቃል መራራ ቢሆንም ተቀባይነት አለው፤ የእናንተ ትችት ግን ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የእኔን ንግግር እንደ ነፋስ ባዶ አድርጋችሁ ትቈጥሩታላችሁ፤ ታዲያ፥ ተስፋ ለቈረጥሁት ለእኔ መልስ መስጠት ለምን ትፈልጋላችሁ? በሙት ልጅ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤ ወዳጆቻችሁን ለመሸጥ የዋጋ ክርክር ታደርጋላችሁ! እባካችሁ ፊቴን ተመልከቱ፤ በፊታችሁ እዋሻለሁን? በደል እንዳይሆንባችሁ ተመለሱ፤ አሁንም ተመለሱ፤ እኔ ትክክለኛ ነኝ። በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን? አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?