መጽሐፈ ኢዮብ 6
6
ኢዮብ
1ከዚህ በኋላ ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ!
መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በታየ ኖሮ!
3ከባሕር ዳር አሸዋ ይበልጥ በከበደ ነበር፤
ስለዚህ ትዕግሥት የጐደለው ንግግሬ ሊያስገርምህ አይገባም።
4ሁሉን የሚችል አምላክ በፍላጻዎቹ ወግቶኛል፤
መርዛቸውም በሰውነቴ ተሠራጭቶአል፤
የሚያስደነግጥ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ዙሪያዬን ከቦኛል።
5በውኑ የሜዳ አህያ ለምለም ሣር ካገኘ
በሬም ድርቆሽ ካገኘ ይጮኻልን?
6ጨው ያልገባበት ጣዕም ያጣ ምግብ ይበላልን?
የእንቊላልስ ውሃ ይጣፍጣልን?
7ለዚህ ዐይነቱ ምግብ ፍላጎት የለኝም፤
ብበላውም እንኳ ጤና ይነሣኛል።
8“ምነው እግዚአብሔር የምመኘውን በሰጠኝ!
ምነው ጸሎቴንስ በሰማኝ!
9ከዚህ ሁሉ ምነው ፈቃዱ ሆኖ ቢሰባብረኝ!
እጁንም ሰንዝሮ ቢያጠፋኝ!
ይህ ለእኔ መጽናናትን በሰጠኝ ነበር።
10የቅዱሱን ቃል ምንጊዜም ስላልካድኩ፥
ምንም እንኳ ሥቃይ ቢበዛብኝ
በደስታ በዘለልኩ ነበር።
11በሕይወት ለመኖር የሚያበቃ ምን ብርታት አለኝ?
ተስፋ ከሌለኝስ ለምን እኖራለሁ?
12እኔ እንደ ድንጋይ ጠንካራ ነኝን?
ሰውነቴስ እንደ ናስ ጠንካራ ነውን?
13ራሴን ለመርዳት ምንም ኀይል የለኝም፤
ያለኝ ኀይል ሁሉ ተወስዶብኛል።
14“ለወዳጁ ያለውን ታማኝነት የሚነሣ ሰው
እግዚአብሔርን መፍራቱን የተወ ነው።
15ወንድሞቼ ግን ጐርፉ ከወረደ በኋላ እንደሚደርቁና
እንደማያስተማምኑ ወንዞች አታላዮች ናቸው።
16ወንዞቹ በክረምት ወራት
በበረዶ ተሞልተው ይሸፈናሉ።
17በበጋ ወራት ግን ተነው ይጠፋሉ።
ወንዞቹም ባዶና ደረቅ ይሆናሉ።
18የጭነት ከብቶችን እየነዱ የሚሄዱ መንገደኞች
ከመንገድ ወጥተው ውሃ ፍለጋ ወደ በረሓ ገብተው ባዝነው ይጠፋሉ።
19የቴማ መንገደኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤
የሳባ ነጋዴዎችም ውሃ ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ።
20የተማመኑበትን ወንዝ ደርቆ ሲያገኙ ተስፋ ይቈርጣሉ፤
ወደ ቦታውም ሲደርሱ ይበሳጫሉ።
21እናንተም ለእኔ እንደ እነዚያ ደረቅ ወንዞች ናቸሁ።
የደረሰብኝን መከራ አይታችሁ ወደ ኋላ አፈገፈጋችሁ።
22ለመሆኑ ይህን ወይም ያንን ስጡኝ፥
ወይም በሀብታችሁ ታደጉኝ ብያችኋለሁን?
23ወይስ ከጠላት እጅ አድኑኝ፤
ወይም ከጨቋኞች እጅ ታደጉኝ ብያችኋለሁን?
24“አስተምሩኝ፤ እኔም ዝም እላለሁ፤
ስሕተቴንም አስረዱኝ።
25እውነተኛ ቃል መራራ ቢሆንም ተቀባይነት አለው፤
የእናንተ ትችት ግን ለምንም አይጠቅምም።
26እናንተ የእኔን ንግግር እንደ ነፋስ ባዶ አድርጋችሁ ትቈጥሩታላችሁ፤
ታዲያ፥ ተስፋ ለቈረጥሁት ለእኔ መልስ መስጠት ለምን ትፈልጋላችሁ?
27በሙት ልጅ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤
ወዳጆቻችሁን ለመሸጥ የዋጋ ክርክር ታደርጋላችሁ!
28እባካችሁ ፊቴን ተመልከቱ፤
በፊታችሁ እዋሻለሁን?
29በደል እንዳይሆንባችሁ ተመለሱ፤
አሁንም ተመለሱ፤ እኔ ትክክለኛ ነኝ።
30በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን?
አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997