መጽሐፈ ኢዮብ 5
5
1“ኢዮብ ሆይ! መልስ የሚሰጥህ ሰው ብታገኝ እስቲ ተጣራ፤
ርዳታ ይሰጥህ ዘንድ
ከመላእክቱ ወደ ማንኛው ትመለከታለህ?
2ቊጣ ሞኝን ይገድለዋል፤
ቅናትም ሰውን ያጠፋል።
3ሞኝ ደርጅቶ ሲኖር አየሁ፤
በእግዚአብሔር ቊጣ በድንገት መኖሪያው ፈራረሰ።
4ልጆቹም የኑሮ ዋስትና አያገኙም፤
በአደባባይም የሚከራከርላቸው ስለማያገኙ
ጥቃት ይደርስባቸዋል።
5ሰብሉንም የተራቡ ሰዎች ይበሉታል፤
በእሾኽ መካከል የበቀለውን እንኳ አይተውለትም፤
የተጠሙ ሰዎችም ሀብቱን ለመውሰድ ይጐመዣሉ።
6ችግር ከዐፈር አይነሣም፤
መከራም ከመሬት አይበቅልም።
7የእሳት ፍንጣሪ ከፍም ላይ ተነሥቶ ወደ ዐየር እንደሚበር፥
እንደዚሁም ሰው ለመከራ ይወለዳል። #5፥7 የእሳት ፍንጣሪ፦ ወይም የአሞራ ጫጩት።
8“እኔ አንተን ብሆን ኖሮ ወደ እግዚአብሔር እማጠን ነበር፤
ችግሬን ሁሉ እገልጥለት ነበር።
9እርሱ የማይቈጠረውን ተአምራት፦
የማይመረመረውን ታላቅ ነገር ያደርጋል።
10በምድር ላይ ዝናብን ያዘንባል፤
እርሻዎችንም በውሃ ያረሰርሳል።
11የተዋረዱትን በክብር ከፍ ያደርጋቸዋል፤
ያዘኑትንም በማጽናናት ደስ ያሰኛቸዋል።
12ሥራቸው እንዳይሳካ የተንኰለኞችን ዕቅድ ከንቱ ያደርጋል።
13ጥበበኞችን የራሳቸው ተንኰል ወጥመድ ሆኖ እንዲይዛቸው ያደርጋል
የተንኰለኞችም ዕቅድ በፍጥነት ይጠፋል። #1ቆሮ. 3፥19።
14ቀኑ ጨለማ ይሆንባቸዋል፤
ገና በእኩለ ቀን፥ በሌሊት ጨለማ ውስጥ እንዳሉ ሆነው ይደናበሩ።
15ድኾችን ከጠላቶቻቸው ሰይፍ ያድናቸዋል፤
ችግረኞችንም ከጨቋኞች እጅ ነጻ ያወጣቸዋል።
16ለድኾች ተስፋ ይሰጣል፤
ዐመፅንም ከምድረ ገጽ ያጠፋል።
17“እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው የተባረከ ነው!
ስለዚህ የልዑል እግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ። #ምሳ. 3፥11፤ ዕብ. 12፥5-6።
18እግዚአብሔር ቢያቈስልህም መልሶ ይጠግንሃል፤
በአንድ እጁ ቢጐዳህ በሌላ እጁ ይፈውስሃል። #ሆሴዕ 6፥1።
19ከስድስት ዐይነት የመቅሠፍት አደጋዎች ይታደግሃል፤
በሰባተኛውም ምንም ጒዳት አይደርስብህም።
20በራብ ዘመን በሕይወት ያኖርሃል።
በጦርነትም ጊዜ ከሞት ያድንሃል።
21እግዚአብሔር ከክፉ ምላስ ይጠብቅሃል፤
ጥፋት ቢመጣብህም አትፈራም።
22የኀያላን አጥቂነትና ራብ አያስደነግጡህም፤
የምድርንም አራዊት አትፈራም።
23በምታርሰው መሬት ላይ ድንጋይ አያውክህም፤
ከአራዊትም ጋር በሰላም ትኖራለህ።
24በድንኳንህ ሰላም እንደሚሰፍን ታረጋግጣለህ፤
የበጎችህንም በረት ስትጐበኝ ሁሉን በደኅና ታገኛቸዋለህ።
25ትውልድህ እንደሚበዛ ታውቃለህ፤
ዘርህም እንደ መስክ ሣር ይበዛል።
26የስንዴ እሸት እስኪጐመራ በማሳ ላይ እንደሚቈይ
አንተም በዕድሜ እስከምትሸመግል ትኖራለህ።
27እኛ ይህን ሁሉ መርምረን እውነት መሆኑን ዐውቀናል
አንተም አስተውለህ ተግባራዊ አድርገው።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997