መጽሐፈ ኢዮብ 6
6
1ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
2ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ!
መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በተደረገ ኖሮ!
3ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፥
ስለዚህ ቃሌ ደፋር ሆኖአል።
4ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥
መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፥
የእግዚአብሔር ድንጋጤ በላዬ ተሰልፎአል።
5በውኑ የሜዳ አህያ ሣር ሳለው ይጮኻልን?
ወይስ በሬ ገለባ ሳለው ይጮኻልን?
6የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን?
ወይስ የእንቍላል ውኃ ይጥማልን?
7ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፥
እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ።
8ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ!
እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ!
9እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ
እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ!
10መጽናናት በሆነልኝ ነበር፥
በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥
የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና።
11እጠብቅ ዘንድ ጕልበቴ ምንድር ነው?
እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድር ነው?
12ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን?
ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን?
13በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ
ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን?
14ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራት
ለሚተው፥ ለመዛል ለቀረበው ስንኳ
ወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል።
15ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥
እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ።
16ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥
አመዳይም ተሰወረባቸው፥
17ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፥
በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ።
18በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፥
ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ።
19የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥
የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው።
20ተስፋ አድርገዋቸው ነበርና አፈሩ፥
ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው።
21አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፥
መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ።
22በውኑ፦ አንዳች ነገር አምጡልኝ፥
ወይስ፦ ከብልጥግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፥
23ወይስ፦ ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፥
ወይስ፦ ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን?
24አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፥
የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ።
25የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው!
የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል?
26ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና
ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን?
27በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፥
ለወዳጆቻችሁም ጕድጓድ ትቈፍራላችሁ።
28አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፥
በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም።
29እባካችሁ፥ ተመለሱ፥ በደል አይሁን፥
ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ።
30በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን?
አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 6: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ