ኢዮብ 6:1-14
ኢዮብ 6:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢዮብም መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ “ከእናንተ አንዱ መቅሠፍቴን ምነው በመዘነ ኖሮ! መከራዬንም በአንድነት ምነው በሚዛን ላይ ባኖረው ኖሮ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፤ ነገር ግን ቃሌ ሐሰትን ይመስላል። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ፍላጻ በሥጋዬ ላይ ነው፤ መርዙም ደሜን ይመጥጣል። ለመናገር ስጀምርም ይወጋኛል። በውኑ የሜዳ አህያ ሣር እያለው በከንቱ ይጮኻልን? የሚበላውን ፈልጎ አይደለምን? ወይስ በሬ በበረት ውስጥ ገለባ ሳለው ይጮኻልን? ምግብ ያለ ጨው ይበላልን? የጎመን ዘር ጭማቂስ ይጣፍጣልን? ወይስ ለከንቱ ጣዕም አለውን? ሰውነቴ ማረፍ አልቻለችም፤ የሥጋዬን ክርፋት እንደ አንበሳ ክርፋት እመለከተዋለሁና። ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ተስፋዬን ምነው በሰጠኝ! እግዚአብሔርም ያቈስለኝ ዘንድ ጀመረ፥ ነገር ግን እስከ መጨረሻው አላጠፋኝም። መቃብሬ በግንቡ የምመላለስበት ከተማዬ ይሁን፥ ከእርሱም ፈቀቅ አልልም የአምላኬን ቅዱስ ቃል አልካድሁምና። እታገሥ ዘንድ ጕልበቴ ምንድን ነው? ነፍሴም ትጽናና ዘንድ ዘመኔ ምንድን ነው? ጕልበቴ የድንጋይ ጉልበት ነውን? በውኑ ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን? በእርሱ የታመንሁ አይደለሁምን? ረድኤቱ ከእኔ ለምን ራቀ? ምሕረቱ ቸል አለኝ፥ እግዚአብሔር አልጐበኘኝም አልተመለከተኝም።
ኢዮብ 6:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ምነው ሐዘኔ በተመዘነ! መከራዬም ሚዛን ላይ በተቀመጠ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ በከበደ፣ ኀይለ ቃሌም ባላስገረመ ነበር! ሁሉን የሚችል አምላክ ፍላጻ በውስጤ ነው፤ መንፈሴም መርዙን ትጠጣለች፤ የእግዚአብሔር ማስደንገጥ ተሰልፎብኛል። የሜዳ አህያ ሣር እያለው፣ በሬስ ድርቆሽ እያለው፣ ይጮኻልን? የማይጣፍጥ ምግብ ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የዕንቍላል ውሃ ጣዕም አለውን? እንዲህ ዐይነቱን ምግብ እጸየፋለሁ፤ ለመንካትም አልፈልግም። “ምነው ልመናዬ በተመለሰልኝ፤ እግዚአብሔር የምመኘውን በሰጠኝ፤ እግዚአብሔር አድቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ፣ ምነው እጁ በተፈታ! ፋታ በማይሰጥ ሕመም ውስጥ እየተደሰትሁ፣ ይህ መጽናኛ በሆነልኝ ነበር፤ የቅዱሱን ትእዛዝ አልጣስሁምና። “አሁንም ተስፋ አደርግ ዘንድ ብርታቴ፣ እታገሥስ ዘንድ አለኝታዬ ምንድን ነው? የድንጋይ ጕልበት አለኝን? ሥጋዬስ ናስ ነውን? ያልተሳካልኝ ሰው ነኝና፣ ራሴን ለመርዳት ምን ጕልበት አለኝ? “ለወዳጁ በጎነት የማያሳይ ሰው፣ ሁሉን የሚችለውን አምላክ መፍራት ትቷል።
ኢዮብ 6:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦ ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በተደረገ ኖሮ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፥ ስለዚህ ቃሌ ደፋር ሆኖአል። ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥ መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፥ የእግዚአብሔር ድንጋጤ በላዬ ተሰልፎአል። በውኑ የሜዳ አህያ ሣር ሳለው ይጮኻልን? ወይስ በሬ ገለባ ሳለው ይጮኻልን? የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የእንቍላል ውኃ ይጥማልን? ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፥ እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ። ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ! እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ! መጽናናት በሆነልኝ ነበር፥ በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥ የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና። እጠብቅ ዘንድ ጕልበቴ ምንድር ነው? እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድር ነው? ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን? ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን? በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን? ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራት ለሚተው፥ ለመዛል ለቀረበው ስንኳ ወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል።
ኢዮብ 6:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በታየ ኖሮ! ከባሕር ዳር አሸዋ ይበልጥ በከበደ ነበር፤ ስለዚህ ትዕግሥት የጐደለው ንግግሬ ሊያስገርምህ አይገባም። ሁሉን የሚችል አምላክ በፍላጻዎቹ ወግቶኛል፤ መርዛቸውም በሰውነቴ ተሠራጭቶአል፤ የሚያስደነግጥ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ዙሪያዬን ከቦኛል። በውኑ የሜዳ አህያ ለምለም ሣር ካገኘ በሬም ድርቆሽ ካገኘ ይጮኻልን? ጨው ያልገባበት ጣዕም ያጣ ምግብ ይበላልን? የእንቊላልስ ውሃ ይጣፍጣልን? ለዚህ ዐይነቱ ምግብ ፍላጎት የለኝም፤ ብበላውም እንኳ ጤና ይነሣኛል። “ምነው እግዚአብሔር የምመኘውን በሰጠኝ! ምነው ጸሎቴንስ በሰማኝ! ከዚህ ሁሉ ምነው ፈቃዱ ሆኖ ቢሰባብረኝ! እጁንም ሰንዝሮ ቢያጠፋኝ! ይህ ለእኔ መጽናናትን በሰጠኝ ነበር። የቅዱሱን ቃል ምንጊዜም ስላልካድኩ፥ ምንም እንኳ ሥቃይ ቢበዛብኝ በደስታ በዘለልኩ ነበር። በሕይወት ለመኖር የሚያበቃ ምን ብርታት አለኝ? ተስፋ ከሌለኝስ ለምን እኖራለሁ? እኔ እንደ ድንጋይ ጠንካራ ነኝን? ሰውነቴስ እንደ ናስ ጠንካራ ነውን? ራሴን ለመርዳት ምንም ኀይል የለኝም፤ ያለኝ ኀይል ሁሉ ተወስዶብኛል። “ለወዳጁ ያለውን ታማኝነት የሚነሣ ሰው እግዚአብሔርን መፍራቱን የተወ ነው።
ኢዮብ 6:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦ “ትካዜዬ ምነው በተመዘነ! መከራዬም በሚዛን ላይ ምነው በተቀመጠ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ በከበደ ነበርና፥ ለዚህም ነው ቃሌ ደፋር የሆነው። ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥ መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፥ የእግዚአብሔር ሽብሮች በኔ ላይ ተሰልፈዋል። በውኑ የሜዳ አህያ ሣር እያለው ይጮኻልን? ወይስ በሬ ገለባ እያለው ይጮኻልን? የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን? ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፥ እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ። ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ! እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ፥ እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ! መጽናናት በሆነልኝ ነበር፥ በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥ የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና። እጠብቅ ዘንድ ጉልበቴ ምንድነው? እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድነው? ጉልበቴ የድንጋይ ጉልበት ነውን? ሥጋዬስ ነሐስ ነውን? በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን?” “ቸርነትን ለወዳጁ የሚነፍግ፥ ሁሉን ቻይ አምላክን መፍራት የተወ ነው።