ኢዮብም መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ “ከእናንተ አንዱ መቅሠፍቴን ምነው በመዘነ ኖሮ! መከራዬንም በአንድነት ምነው በሚዛን ላይ ባኖረው ኖሮ! ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፤ ነገር ግን ቃሌ ሐሰትን ይመስላል። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ፍላጻ በሥጋዬ ላይ ነው፤ መርዙም ደሜን ይመጥጣል። ለመናገር ስጀምርም ይወጋኛል። በውኑ የሜዳ አህያ ሣር እያለው በከንቱ ይጮኻልን? የሚበላውን ፈልጎ አይደለምን? ወይስ በሬ በበረት ውስጥ ገለባ ሳለው ይጮኻልን? ምግብ ያለ ጨው ይበላልን? የጎመን ዘር ጭማቂስ ይጣፍጣልን? ወይስ ለከንቱ ጣዕም አለውን? ሰውነቴ ማረፍ አልቻለችም፤ የሥጋዬን ክርፋት እንደ አንበሳ ክርፋት እመለከተዋለሁና። ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ተስፋዬን ምነው በሰጠኝ! እግዚአብሔርም ያቈስለኝ ዘንድ ጀመረ፥ ነገር ግን እስከ መጨረሻው አላጠፋኝም። መቃብሬ በግንቡ የምመላለስበት ከተማዬ ይሁን፥ ከእርሱም ፈቀቅ አልልም የአምላኬን ቅዱስ ቃል አልካድሁምና። እታገሥ ዘንድ ጕልበቴ ምንድን ነው? ነፍሴም ትጽናና ዘንድ ዘመኔ ምንድን ነው? ጕልበቴ የድንጋይ ጉልበት ነውን? በውኑ ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን? በእርሱ የታመንሁ አይደለሁምን? ረድኤቱ ከእኔ ለምን ራቀ? ምሕረቱ ቸል አለኝ፥ እግዚአብሔር አልጐበኘኝም አልተመለከተኝም።
መጽሐፈ ኢዮብ 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 6:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos