ኢዮብ 19:23-29
ኢዮብ 19:23-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ቃሌን ማን በጻፈው! ማንስ በመጽሐፍ ውስጥ ለዘለዓለም ባተመው! ማን በብረት ብርዕና በእርሳስ፥ በዓለት ላይ በቀረፀው! እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ ይህ ቍርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያ ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፤ ዐይኖቼም ይመለከቱታል፤ ከእኔም ሌላ አይደለም። ሁሉም በብብቴ ተፈጸመ። “በፊቱ ምን እንናገራለን? የነገሩ ሥርም በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥ እናንተ ሐሣርን ፍሩአት፥ ቍጣ በኃጥኣን ላይ ይመጣልና፤ ያንጊዜም ክፋታቸው ከየት እንደ ሆነ ያውቃሉ።”
ኢዮብ 19:23-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ምነው ቃሌ በተጻፈ ኖሮ! በመጽሐፍም በታተመ! ምነው በብረትና በእርሳስ በተጻፈ ኖሮ! በዐለትም ላይ በተቀረጸ! የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፣ በመጨረሻም በምድር ላይ እንደሚቆም ዐውቃለሁ። ቈዳዬ ቢጠፋም፣ ከሥጋዬ ብለይም፣ እግዚአብሔርን አየዋለሁ፤ ሌላ ሳይሆን እኔው በገዛ ዐይኔ፣ እኔ ራሴ አየዋለሁ፤ ልቤ በውስጤ ምንኛ በጉጉት ዛለ! “ ‘የችግሩ መንሥኤ በውስጡ አለ፤ እኛ እንዴት እናሳድደዋለን?’ ብትሉ፣ ቍጣ በሰይፍ መቀጣትን ያስከትላልና፣ ራሳችሁ ሰይፍን ፍሩ፤ በዚያ ጊዜ ፍርድ እንዳለ ታውቃላችሁ።”
ኢዮብ 19:23-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም! ምነው በብረት ብርና በእርሳስ በዓለቱ ላይ ለዘላለም ቢቀረጽ! እኔን ግን የሚቤዥኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል። በእውነት፦ እንዴት እናሳድደዋለን? የነገሩ ሥር በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥ ፍርድ እንዳለ ታውቁ ዘንድ ቍጣ የሰይፍን ቅጣት ያመጣልና ከሰይፍ ፍሩ።
ኢዮብ 19:23-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“እስከ አሁን የተናገርኩትን ቃል የሚያስታውስና በመጽሐፍ የሚመዘግበው ሰው ቢገኝ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር! ምነው በብረት መሣሪያና በእርሳስ ተጽፈው ወይም በድንጋይ ላይ ተቀርጸው ለዘለዓለም እንዲኖሩ ቢደረግ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር! ነገር ግን አዳኜ ሕያው እንደ ሆነና፥ በመጨረሻ ጊዜም እኔን ለመታደግ በምድር ላይ እንደሚቆም ዐውቃለሁ። ቆዳዬ ተበልቶ ቢያልቅም፥ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንደማየው ዐውቃለሁ። እርሱም እኔው ራሴ የማየው ነው፤ ዐይኖቼ ያዩታል፤ ሌላም አይደለም፤ ልቤም ያችን ዕለት በጣም ይናፍቃል። “ወዳጆቼ ሆይ! እኔን ወቅሳችሁ ለማሠቃየት፥ የችግሩን ምክንያት እርሱ ራሱ ነው በማለት ትናገራላችሁ። የእግዚአብሔር ቊጣ የሰይፍን ቅጣት ስለሚያስከትል ሰይፍ እንዳይበላችሁ ተጠንቀቁ። የእግዚአብሔር ፍርድ መኖሩንም ዕወቁ።”
ኢዮብ 19:23-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም! ምነው በብረት ብርና በእርሳስ በዓለቱ ላይ ለዘለዓለም ቢቀረጽ! እኔን ግን የሚቤዥኝ ሕያው እንደሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንደሚቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንደማይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዐይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል። በእውነት፦ እንዴት እናሳድደዋለን? የነገሩ ሥር በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥ ፍርድ እንዳለ ታውቁ ዘንድ ቁጣ የሰይፍን ቅጣት ያመጣልና ከሰይፍ ፍሩ።”