የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 19

19
ኢዮብ
1ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“እስከ መቼ ድረስ ታሠቃዩኛላችሁ?
እስከ መቼስ በነገር ቅስሜን ትሰብሩታላችሁ?
3እነሆ ዐሥር ጊዜ ትሰድቡኛላችሁ፤
ስታዋርዱኝም አታፍሩም።
4በእርግጥ ተሳስቼ ከሆነ፥
ስሕተቱ የሚጐዳው ራሴን ብቻ ነው።
5በእውነት እናንተ ራሳችሁን ከፍ ከፍ አድርጋችሁ፥
የእኔን መዋረድ የመከራከሪያ ነጥብ ታደርጉታላችሁ
6ነገር ግን ይህን ሁሉ መከራ ያደረሰብኝና
መረብ ውስጥም የጣለኝ እግዚአብሔር መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ።
7ተበደልኩ ብዬ ብጮኽ የሚሰማኝ አላገኘሁም፤
ድምፄን ከፍ አድርጌ አቤቱታ ባሰማም ፍትሕ አላገኘሁም።
8እግዚአብሔር መንገዴን ሁሉ ስለ ዘጋው
መተላለፊያ የለኝም፤
መሄጃዬንም በጨለማ ጋርዶታል።
9ክብሬን ከራሴ ላይ ገፎ አዋረደኝ።
10ሰውነቴን በየአቅጣጫው በመቀጥቀጥ
ጨርሶ አፈራረሰው፤
የነበረኝንም ተስፋ ሥሩ ተነቃቅሎ እንደሚወድቅ ዛፍ አደረገው።
11እግዚአብሔር ተቈጥቶ መዓቱን አፈሰሰብኝ፤
እንደ ጠላትም ቈጠረኝ።
12እኔን ለማጥፋት ሠራዊቱን ላከ፤
በድንኳኔም ዙሪያ ምሽግ ሠርተው ከበቡኝ።
13“እግዚአብሔር ወንድሞቼ ከእኔ እንዲርቁ አደረገ፤
የሚያውቁኝም ሰዎች ሁሉ ባይተዋር አደረጉኝ።
14ዘመዶቼ ራቁኝ፤
ወዳጆቼም ረሱኝ።
15በእንግድነት በቤቴ ተቀብዬ
ያስተናገድኳቸው ሁሉ ረሱኝ፤
ገረዶቼ ሁሉ እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፤
እንደ ባዕድም ተመለከቱኝ።
16አገልጋዬን ስጠራው መልስ አይሰጠኝም
እባክህ እርዳኝ ብዬ ስለምነውም እንኳ እሺ አይለኝም።
17ሚስቴ ጠረኔን ጠላችው፤
የገዛ ወንድሞቼም ተጸየፉኝ።
18ሕፃናት እንኳ ይንቁኛል፤
እኔንም በሚያዩበት ጊዜ ያፌዙብኛል።
19የቅርብ ወዳጆቼ ተጸየፉኝ፤
በጣም የምወዳቸው ሰዎች በጠላትነት ተነሡብኝ።
20ሥጋዬ አልቆ ቆዳዬ በአጥንቴ ላይ ተጣበቀ፤
ድድ ብቻ ቀርቶልኝ ተረፍኩ።
21“ወዳጆቼ ሆይ! የእግዚአብሔር እጅ ስለ መታኝ
እባካችሁ እናንተ እዘኑልኝ! ራሩልኝም!
22እግዚአብሔር እንዳሳደደኝ
እናንተ ደግሞ ለምን ታሳድዱኛላችሁ?
እስካሁንስ ያሠቃያችሁኝ አይበቃችሁምን?
23“እስከ አሁን የተናገርኩትን ቃል የሚያስታውስና
በመጽሐፍ የሚመዘግበው ሰው ቢገኝ
እንዴት ደስ ባለኝ ነበር!
24ምነው በብረት መሣሪያና በእርሳስ ተጽፈው
ወይም በድንጋይ ላይ ተቀርጸው
ለዘለዓለም እንዲኖሩ ቢደረግ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር!
25ነገር ግን አዳኜ ሕያው እንደ ሆነና፥
በመጨረሻ ጊዜም እኔን ለመታደግ
በምድር ላይ እንደሚቆም ዐውቃለሁ።
26ቆዳዬ ተበልቶ ቢያልቅም፥
ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንደማየው ዐውቃለሁ።
27እርሱም እኔው ራሴ የማየው ነው፤
ዐይኖቼ ያዩታል፤ ሌላም አይደለም፤
ልቤም ያችን ዕለት በጣም ይናፍቃል።
28“ወዳጆቼ ሆይ! እኔን ወቅሳችሁ ለማሠቃየት፥
የችግሩን ምክንያት እርሱ ራሱ ነው በማለት ትናገራላችሁ።
29የእግዚአብሔር ቊጣ የሰይፍን ቅጣት ስለሚያስከትል
ሰይፍ እንዳይበላችሁ ተጠንቀቁ።
የእግዚአብሔር ፍርድ መኖሩንም ዕወቁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ